የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ለድርድር የሰጡት ምላሽና የነበሩ ሂደቶች

ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትን ያስከተለውና አስራ አምስት ወራት ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማስቆም የተለያዩ ወገኖች ጥረት እያደረጉ መሆኑ ይሰማል።
የአፍሪካ ሕብረት፣ አሜሪካ እና ኬንያ በኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ክልልን ተቆጣጥሮ በሚገኘው ህወሓት መካከል ንግግር ተካሂዶ ግጭቶች እንዲቆሙ እንዲሁም ሰብአዊ እርዳታ በችግር ላይ ላሉ ሰዎች እንዲደርስ ጥረት እያደረጉ ቢቆዩም ይህ ነው የሚባል ውጤት አልተገኘም።
ጦርነቱ ተፋፍሞ በቀጠለባቸው የተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የህወሓት መሪዎች አንዳቸው አንዳቸውን አሸንፈው ድልን መቀዳጀት እንጂ በጠረጴዛ ዙሪያ የመቀመጥ ፍላጎት እንደሌላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
ባለፈው ዓመት ጦርነቱ ተጀምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመንግሥት ሠራዊት ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ ምዕራባውያን ድርድር እንዲደረግ ጥያቄ ቢያቀርቡም መንግሥት ሽብርተኛ ካለው ቡድን ጋር የመደራደር ፍላጎት እንደሌለው በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል።
ከስምንት ወራት በኋላ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ሲያስወጣ፣ ህወሓት ሙሉ ለሙሉ ትግራይን በመቆጣጠር ወደ አፋርና አማራ የጥቃት አድማሳቸውን አስፋፍተው ነበር።
ይህም የህወሓት ግስጋሴ ተጠናክሮ ሰሜን ሸዋ ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ አማፂያኑ ቀጣይ መዳረሻቸው አዲስ አበባ መሆኑን ገልፀው የህወሓት ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች ተዋጊዎቻቸው ጦርነቱን እያጠናቀቁ በመሆኑ የድርድር አስፈላጊነት እንዳበቃለት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተደምጠዋል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ የነበሩት ጄፍሪ ፌልትማን እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት ተወካዩ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ አዲስ አበባ፣ መቀለ እና ናይሮቢ እየተመላለሱ ለማሸማገል ጥረት እያደረጉ ነበር።
ኅዳር ወር ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የመንግሥት ኃይሎች በህወሓት ላይ ጥቃት ከፍተው የአማጺው ግስጋሴ ከተገታ በኋላ ለሰላም አዲስ በር የተከፈተ መሰለ።
በዚህ ጊዜ መንግሥት በህወሓት ተይዘው የነበሩ የአማራና የአፋር አካባቢዎችን በአሸናፊነት መልሶ መቆጣጠሩን ይፋ ሲያደርግ፣ የህወሓት መሪዎች ደግሞ ለሰላም እድል ለመስጠት በሚል ተዋጊዎቻቸውን ወደ ትግራይ እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
ይህንን ተከትሎም ፌልትማንና ተተኪያቸው ዴቪድ ሳተርፊልድ እንዲሁም ኦባሳንጆ ጥረታቸውን ቀጥለው በመንግሥትና በህወሓት በኩል ድርድር ሊጀመር ይችላል ቢባልም በግልጽ የሚታይና ውጤት ያስገኘ ነገር ሳይገኝ እስካሁን ቀጥሏል።
ቢሆንም ግን በሁለቱ ወገኖች በኩል ውይይት የማድረግና ጦርነቱን የማስቆም ተስፋ እንዳለ ኦባሳንጆ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ መግለጻቸው መዘገቡ ይታወሳል።
የድርድር ጭምጭምታ
ከህወሓት በኩል ጦርነቱ በድርድር እንዲያበቃ ዝግጁነት እንዳለ በተለያየ አጋጣሚ የተገለጸ ሲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በኩል ግን ይህ ነው የሚባል የድርድር ፍላጎት ስለመኖሩ ሳይሰማ ቆይቷል።
ጥር ወር አጋማሽ ላይ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ከአማጺው ህወሓት ጋር ንግግር የማድረግ ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ዜና በአሜሪካው የዜና ወኪል ኤፒ በኩል ተዘገበ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ውይይት ያደረጉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ቡድን አባልን ጠቅሶ ነበር አሶሺየትድ ፕሬስ የዘገበው።
የአሜሪካውያን - ኢትዮጵያውያን የሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌይርስ ኮሚቲ) ሊቀመንበር የሆኑት መስፍን ተገኑ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ "ጦርነቱን ለማቆም ጽኑ ፍላጎት አለ . . . በእርግጥ ይህ እንዲሆን ሌላኛው ወገንም ፈቃደኛ መሆን አለበት" ብለዋል።
በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "ድርድር ይኖራል። የአገሪቱን ጥቅም የሚያስቀድም ምክንያታዊ ድርድር ይኖራል" ስለማለታቸው ኤፒ ሊቀመንበሩን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ይህ ዜና ከተነገረ በኋላ የሚያስተባብልም ሆነ የሚያረጋግጥ መረጃ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ሳይወጣ ነገሩ ተድበስብሶ ቢቆይም፣ አንዳች አይነት ጥረት እየተደረጉ መሆናቸውን በተመለከተ ያልተጨበጡ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል።
ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር
በመንግሥትና በህወሓት መካከል እየተካሄደ ነው ሲባል ስለቆየው ድርድርን በተመለከተ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ከዋነኞቹ አሸማጋዮች ኦባሳንጆና ሳተርፊልድ ተደጋጋሚ የምልልስ ጉዞዎችና ተስፋ ውጪ ከሁለቱም ወገን በይፋ የተሰጠ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባባያ አልነበረም።
ከዚህ አንጻር ዋነኛው ጉልህ የሚባል ዜና የተሰማው ጥር 21/2014 ዓ.ም የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሪ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ከቢቢሲ ኒውስ አወር ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ ላይ ነበር።
በዚህም ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እያደረገ መሆኑንና በሂደቱም የተወሰነ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየታየ መሆኑን ገልጸው ነበር።
ደብረጽዮን (ዶ/ር) ጨምረውም ይህ የንግግር ጥረት በአፍሪካ ሕብረት፣ በተባበሩት መንግሥታት እና በኬንያ አማካይነት በተዘዋዋሪ የሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ይህንን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም።
በተጨማሪም ዜናው ከተሰማ ከሦስት ሳምንታት በላይ ቢሆንም ከዚህ ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር በይፋ የተነገረ ውጤት አልተሰማም።
'የህወሓት ቅድመ ሁኔታዎች'
ስለድርድርና ሽምግልና ግልጽ ያሉ መረጃዎች ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ህወሓት የተመሰረተበትን ዕለት ምክንያት በማድረግ የድርጅቱ ሊቀመንበር ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በሰጡት መግለጫ ላይ ቅድመ ሁኔታዎች የሚመስሉ ነጥቦችን አንስተዋል።
ጦርነቱ በድርድር መፍትሔ እንዲያገኝ የተለያዩ ወገኖች ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን በመግለጽ፤ የአፍሪካ ሕብረትን በመወከል የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት፣ በተመሳሳይ የኬንያው ፕሬዚዳንት፣ የአሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ልዑካን የበኩላቸውን እየሞከሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ነገር ግን እየተደረገ ባለው የሰላም ጥረት ውስጥ ለድርድር በማይቀርቡት ያሏቸውን "በሠራዊታቸው ላይ፣ በትግራይ ክልል ወሰን ጉዳይ፣ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ መውጣት፣ የትግራይ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት ጉዳይ እና በትግራይ ሕዝብ ላይ በደል የፈፀሙ ግለሰቦች ተጠያቂነት" ላይ ድርድርና ሰጥቶ መቀበል እንደማይኖር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ግልጽ አድርገዋል።
ከእነዚህ ነጥቦች ባሻገር ባሉ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር እንደሚቻል ህወሓት በሊቀመንበሩ በኩል የገለጸ ሲሆን፣ በእርግጥ ድርድር የሚካሄድ ከሆነ በተመሳሳይ ከሌላኛው ወገን የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ንግግሩን የተራዘመና የተወሳሰበ ሊያደርገው እንደሚችል ይገመታል።
ድርድር አልተካሄደም
በተለያዩ ወገኖች የሚደረጉ ጥረቶችን ተከትሎ ከሚሰሙ ዜናዎችና ከህወሓት መሪ የተነገሩ የንግግር ጅማሬዎችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግልጽ ምላሽ የተሰማው የካቲት 15/2014 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኩል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ድርድርን በተመለከተ በስፋት የሚነገሩትን ጉዳዮች በማንሳት የምክር ቤት አባላት ጥያቄ አቅርበዋል።
ለቀረበላቸው ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት በኩል ከህወሓት ጋር እስካሁን የተጀመረ ምንም አይነት ድርድር አለመኖሩን በግልጽ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት በኩል ከህወሓት ጋር የተደረገ ድርድር እንደሌለ ነገር ግን "ድርድር አልተደረገም ማለት ድርድር አያስፈልግም" ማለት እንዳልሆነ በመግለጽ የንግግር እድል እንዳለ ጠቁመዋል።
ጨምረውም የሚካሄድ ጦርነትም ሆነ ድርድር ዓላማው ኢትዮጵያን ማፅናት እንደሆነ በመጥቀስ "አገርን በሚያፈርስ በማንኛውም መንገድ ድርድር አይደረግም" በማለት "የአገሪቱን ሉዓላዊነትና ህልውና በማይፈታተን ሁኔታ ድርድር ሊኖር እንደሚችል" ጠቆም አድርገዋል።
እንግዲህ የቀጠለውን ጦርነት ሰላማዊ መቋጫ እንዲያገኝ የሚያስችለው የተለያዩ ወገኖች የሽምግልና ጥረት ውጤት ሳያስገኝ አሁን ላይ ደርሷል።
ድርድር የማድረግ ፍላጎቱ ብዙም ሳይታወቅ የቆየው መንግሥት አሁን የአገሪቱን ጥቅም በሚያስጠብቅ ሁኔታ የመነጋገር ፍላጎት እንዳለው ፍንጭ የሰጠ ይመስላል።
ቢሆንም ግን በድርድሩ ሂደት በሁለቱም ወገኖች የሚቀርቡ ፍላጎቶችን አጣጥሞ ሰላም የማምጣቱ ሂደት ደግሞ ሌላ ከፍ ያለ ጥረትንና ጊዜን የሚጠይቅ መሆኑ አይቀሬ ነው።
















