ታጣቂዎች አፋር ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት 5 ኤርትራውያን ስደተኞች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታጣቂዎች በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ የአፋር ክልል ውስጥ በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ አምስት ኤርትራውያን መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት አርብ ዕለት እንዳስታወቀው ከአንድ ሳምንት በፊት ታጣቂዎች በአፋር ክልል ውስጥ በሚገኝ ካምፕ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ አምስት ስደተኞችን ተገድለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ባወጣው መግለጫ ጥር 26/20122 ዓ.ም በታጣቂዎቹ በተፈጸመው ጥቃት ከግድያ በተጨማሪ በርካታ ስደተኛ ሴቶች በታጣቂዎቹ ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን በንብረት ላይ ዘረፋ ተፈጽሟል።
በታጣቂዎች የተፈጸመውን ጥቃት ተከተሎ በካምፑ ውስጥ ከነበሩት ስደተኞች መካከል ብዙዎች ከካምፑ ወጥተው የሸሹ በመሆናቸው ቤተሰቦች መጠፋፋታቸው ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ኤርትራውያን ስደተኞች በተጠለሉበት ካምፕ ላይ ጥቃቱን የፈፀመው ማን እንደሆነ ያለው ነገር የለም።
ነገር ግን ከጥቃቱ አምልጠው ሰመራ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ስደተኞችን በዚህ ሳምንት አናግሬያለው ያለው የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ፤ ግድያው የተፈጸመው በህወሓት እንደሆነ እንደሚያምኑ ገልጿል።
በተጨማሪም የአፋር ክልል አስተዳደርና የብሔራዊው የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ባለሥልጣናት ለጥቃቱ ህወሓትን ተጠያቂ አድርገዋል።
ይህንን ጥቃት በተመለከተ እስካሁን የህወሓት መሪዎች ያሉት ነገር የለም።
ጥቃቱ የተፈጸመበት የስደተኞች መጠለያ የሚገኝበት ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰነው የአፋር ክልል ከሳምንታት በፊት ጀምሮ በአማጺያኑ የህወሓት እና የክልሉ ኃይሎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ከአንድ ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲቀሰቀስ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች በትግራይና በአፋር ክልል ውስጥ ተጠልለው ይገኙ የነበረ ሲሆን፣ በጦርነቱ ምክንያት ከመካከላቸው በርካቶች የት እንዳሉ አይታወቅም።
ስደተኞቹ በፖለቲካዊ ነጻነት እጦትና የግዴታ ወታደራዊ አገልግሎት ምክንያት ከአገራቸው በመሸሽ ወደ ጎረቤት ኢትዮጵያ ገብተው ለበርካታ ዓመታት ተጠልለው መቆየታቸው ይታወቃል።
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ በትግራይና በአፋር ክልሎች ውስጥ የቆዩት በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች በጦርነቱ መካከል ለአደጋ ተጋልጠው ቆይተዋል።
በትግራይ ውስጥ የሚገኙት ስደተኞች በተደጋጋሚ በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑት በሁሉም ኃይሎች የጥቃት ኢላማ ሆነው መቆየታቸው በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል።
ከተወሰኑ ወራት ወዲህ በመንግሥትና በአማጺው የህወሓት ኃይሎች መካከል ሲካሄድ የቆየው ውጊያ በከፍተኛ ደረጃ ጋብ ያለ ቢሆንም በአፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ባለሥልጣናት ሲገልጹ ቆይተዋል።
በዚህ ውጊያ የህወሓት ኃይሎች ወደ አፋር ገብተው አምስት አካባቢዎችን እንደተቆጣጠሩና ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ ባለሥልጣናት ከሳምንት በፊት የገለጹ ሲሆን በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንም ገልጸዋል።
በአፋር ክልል ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በተመለከተ ህወሓት ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ የክልሉ ኃይሎች ለፈጸሙት ተደጋጋሚ ጥቃት "ጠንካራ ወታደራዊ እርምጃ" መውሰዱን መገልጹ ይታወሳል።
በክልሉ ለሳምንታት ስለዘለቀው ውጊያ እስካሁን የፌደራሉ መንግሥት በይፋ ያለው ነገር የለም።
የህወሓት ኃይሎች በጥቅምት እና በኅዳር ወራት ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻን ወደ አማራና አፋር ክልሎች አድርገው በርካታ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር ችለው የነበረ ሲሆን ወደ አዲስ አበባም እንደሚያቀኑ ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ያካሄደውን ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ማስለቀቅ በመቻሉ፣ በአሁኑ ጊዜ ወታደራዊው ፍጥጫ የአፋርና የአማራ ክልሎች ከትግራይ ጋር በሚዋሰኑባቸው ቦታዎች ላይ ሆኗል።












