'ህወሓት ለድርድር በማያቀርባቸው ጉዳዮች ላይ ሰጥቶ መቀበል አይሰራም' ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)

እየተደረገ ባለው የሰላም ጥረት ውስጥ ለድርድር በማይቀርቡት አምስት የትግራይ ሕዝብ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሰጥቶ መቀበል እንደማይኖር የህወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ተናገሩ።
ደብረ ጽዮን ህወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 47ኛ ዓመት በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ከመንግሥት ጋር በተለያዩ ወገኖች አማካይነት ንግግር እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፣ ነገር ግን ለድርድር የማይቀርቡ ጉዳዮች እንዳሉ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረታዊ የትግራይ ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው ያሏቸውን አምስት ጉዳዮችን ዘርዝረዋል። "በመጀመሪያ ደረጃ በሠራዊታችን ላይ አንደራደርም። አሁን ያለው ብቻ ሳይሆን ገና እንጨምርበታለን ስለዚህ በሠራዊታችን ጉዳይ ላይ አንደራደርም። ከዚህ በኋላም ኃይላችንን ይዘን ነው የምንኖረው" በማለት ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ ሕገ መንግሥት የታወቁ የትግራይ ክልል ወሰን ጉዳይ፣ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ መውጣት፣ የትግራይ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት ጉዳይ እና በትግራይ ሕዝብ ላይ በደል የፈፀሙ ግለሰቦች ተጠያቂነት ለድርድር አይቀርብም ብለዋል።
ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ጨምረውም እየተደረጉ ባሉት የድድርድ ጥረቶች ውስጥ እነዚህ አምስት ቅድመ ሁኔታዎች ዋነኞቹና ሊጣሱ የማይገቡ የድርድር ነጥቦች መሆናቸውን ጠቅሰው "ሰጥቶ መቀበል የሚባለው ጉዳይ እዚህ ላይ አይሰራም" ብለዋል።
ነገር ግን ጦርነቱ በድርድር መፍትሔ እንዲያገኝ የተለያዩ ወገኖች የማሸማገል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ የአፍሪካ ሕብረትን በመወከል የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት፣ በተመሳሳይ የኬንያው ፕሬዚዳንት፣ የአሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ልዑካን የበኩላቸውን እየሞከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"በእኛ በኩል አሁንም የሰብአዊ እርዳታ በሮችን ለማስከፈት፣ ተኩስ ቆሞ ባንኮች እንዲከፈቱ ገንዘብ፣ ነዳጅ እንዲሁም የተለያዩ አቅርቦቶች እንዲመጡ ተግተን እየሰራን ነው" በማለት የተስፋ ጭላንጭል አለ ብለዋል።
ነገር ግን ሰላም ለማምጣት አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳለ የገለጹት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ይህንን በመገንዘብ አስፈላጊውን ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ጊዜ እየነጎደ መሆኑን በመግለጫቸው ላይ የጠቀሱት የህወሓት ሊቀመንበር "ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባው ነገር በሮች ሁሉ ተዘግተውብን እና ከበባ ውስጥ ሆነን ብዙ ልንቆይ አንችልም። ተስፋውም ቢሆን በአጭር ጊዜ ዕውን የሚሆን ከሆነ እናያለን" ብለዋል።
ጨምረውም ሰለማዊ መፍትሔ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት በአጭር ጊዜ መቋጫ እንዲያገኝ ቀነ ገደብ ማስቀመጣቸውን ገልጸው" ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በከበባ ሥር ሆነን ብዙ ልንታገስ አንችልም" ንግግሩን በፍጥነት ከድምዳሜ እንዲደርስ ያላቸውን ፍላጎት ተናግረዋል።
ቢሆንም ግን የሰላም ጥረቱ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ እንዳለ ነገር ግን በፌዴራል መንግሥት በኩል ግን ይህን የድርድር ሂደት ጊዜ መግዣና ራሱን ለማጠናከር እያዋለው ነው ሲሉ ደብረ ጽዮን ወቅሰዋል።
"አቅም እያደራጁ ነው፣ ያላቸውን አቅም አሰባስበው እንችላለን በሚሉት ሰዓት ጥቃት መከፈታቸው አይቀርም። ስለዚህ ሰላም የሚሉት ነገር ጊዜያዊ ነው። ወታደራዊ አቅማቸውን በትጥቅ፣ በሰው ኃይል እና በአመራር እያደራጁ ነው።" ብለዋል።
ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) እንደሚሉት መንግሥት ከሁሉም አቅጣጫ የሰላም ጥሪ እየመጣ ስለሆነ እና ያለበትን ጫና ለማርገብ የሰላም ጥሪውን ተቀብሏል። "ለጊዜው ጊዜ መግዣ ብለው የተቀበሉት ስለሆነ ውጤትም ሙሉ እንደማይሆን ልናውቅ ይገባል። ይህንን አውቀን ነው ወደ ሰላም ጥረቱ የገባነው" ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።
በፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መካከል ጦርነቱን የሚያስቆም ውይይት እንዲደረግ የተለያዩ ወገኖች ባለፉት ወራት ጥረት እያደረጉ መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም እስካሁን በይፋ የተነገረ ጉዳይ የለም።
ከህወሓት በኩል ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር በአሸማጋዮች በኩል እየተደረገ መሆኑ ከሳምንታት በፊት የተነገረ ሲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እየተካሄደ ነው ስለተባለው ንግግር ምንም አይነት ማረጋገጫ አልተሰጠም።
ከቀናት በፊት የፌዴራል መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ ለቢቢሲ በሰጡት አጭር ምላሽ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር በይፋ የጀመረው የሰላም ውይይትም ሆነ ድርድር የለም ሲሉ ተናግረዋል።
አንድ ዓመት ተኩል ሊሆነው የተቃረበው በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት መዳረጉ የተነገረ ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉን የእርዳታ ድርጅቶች መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተጨማሪም በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ የሚገኙ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በጦርነቱ ምክንያት የሰብአዊ እርዳታን ለመጠበቅ መገደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
ይህንን ጦርነት ለማስቆም አሜሪካና የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ መድበው ለወራት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በአፋር ክልል ውስጥ ከባድ ጦርነት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ መንግሥትና የእርዳታ ድርጅቶች ተናግረዋል።















