የህወሓት ኃይሎች ከአማራና ከአፋር ክልሎች የወጡት ተሸንፈው ነው - መንግሥት

ቢልለኔ

የፎቶው ባለመብት, Pmo/screen grab

የኢትዮጵያ ሠራዊትና አጋሮቹ ከከባድ ውጊያ በኋላ የህወሓት ኃይሎችን አሸንፈው ከአፋርና ከአማራ ክልል ማስወጣታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ተናገሩ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ማክሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአፋር እና የአማራ ክልል ኃይሎች በጋራ ባካሄዱት ዘመቻ ከፍተኛ ድል በማግኘት የህወሓት ኃይሎችን ከክልሎቹ ማስወጣታቸውን ጠቅሰዋል።

ቢልለኔ ይህንን ያሉት ከቀናት በፊት የህወሓት አመራሮች ከአማራና ከአፋር ክልል ኃይሎቻቸውን በፈቃዳቸው በማስወጣት ወደ ትግራይ እንዲመለሱ ማድረጋቸውን እና ለሰላም ዝግጁ መሆናቸውን በተመለከተ አስተያየታቸውን በተጠየቁበት ጊዜ ነው።

ባለፈው እሁድ ታኅሣሥ 10/2014 ዓ.ም. የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ላኩት በተባለው ደብዳቤ ላይ ኃይሎቻቸው ከትግራይ ክልል ውጪ ከነበሩባቸው አጎራባች ክልሎች "ለሰላም ዕድል ለመስጠት" ለቅቀው እንዲወጡ ማዘዛቸውን አመልክተው ነበር።

ይህንን በተመለከተ ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው የተናገሩት ቢልለኔ፣ ህወሓት ህገወጥ ቡድን ከመሆኑ አንጻር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደብዳቤ የመጻፉን ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ ከተውታል።

ጦርነቱ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ መንግሥት ሁልጊዜም ሰላማዊ አማራጭን አጽንኦት ሰጥቶ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ከግጭቱ መጀመር በኋላም በርካታ የሰላም ጥረቶች ቢያደርግም ተቀባይነት አላገኘም ብለዋል።

ቢልለኔ በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት በጦር ግንባሮች ሽንፈት ገጥሞት ከአማራና ከአፋር ክልሎች መውጣቱን በተመለከተ ባለፉት ሳምንታት የተካሄዱት ዘመቻዎች ምስክሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

"የተገኙት ድሎች ባለፉት ሳምንታት በተካሄዱ ከባድ ውጊያዎች አማካኝነት ነው። በቅርቡ የተደረገውና ወልድያን ጨምሮ የሰሜን ወሎ ዞንን ከህወሓት ነጻ የሆነበት ዘመቻም የዚሁ አካል ነው ብለዋል" ቢልለኔ።

ቃል አቀባይዋ ጨምረውም የአገሪቱ ሠራዊት አሁንም ከአንዳንድ የአፋርና የአማራ ክልሎች ውስጥ የህወሓት ኃይሎች የማጽዳት ሥራ እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሽብርተኝነት የሰየመው ቡድን ህወሓት መሪ የሆኑት ደብረጽዮን (ዶ/ር) በደብዳቤያቸው ኃይሎቻቸውን በማስወጣት ተኩስ አቁም ተደርጎ ድርድር እንዲጀመር ፍላጎት እንዳላቸው አመልከተዋል።

መንግሥት ቀደም ሲል ተኩስ ማቆሙን ያመለከቱት ቢልለኔ በወቅቱ "ቀልድ" ተብሎ መጣጣሉን ጠቅሰው፣ የፌደራል መንግሥቱ የአገሪቱን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት ይህም በአገር መከላከያ ሠራዊት የሚረጋገጥ ሲሆን "ህወሓት ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ስጋት አይሆንም" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ላይ ተጀምሮ ትግራይ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ሰኔ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ሲያስወጣ፣ ህወሓት ተኩስ ለማቆም ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ወደ አጎራባች ክልሎች ተዋጊዎቹን ማስማራቱ ይታወሳል።

የህወሓት ኃይሎች በአማራ እና አፋር ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር እስከ ሰሜን ሸዋ ለመድረስ ችለው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በኅዳር ወር የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት፣ ከአፋርና ከአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ሚሊሻዎች ጋር በመቀናጀት ባካሄዱት የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የህወሓት ኃይሎችን ከአፋር ክልል ሙሉ ለሙሉ እንዲሁም ከአብዛኛው የአማራ ክልል ለማስወጣት ችለዋል።

ካለፈው ሳምንት ወዲህ የህወሓት ባለሥልጣናት 'በስልታዊ ውሳኔ' ይዘዋቸው ከነበሩ ቦታዎች መውጣታቸውን ሲገልጹ የቆዩ ሲሆን ከቀናት በፊት ደግሞ ለድርድር በር ለመክፈት ኃይሎቻቸው ከሁለቱ አጎራባች ክልሎች እንዲወጡ ማድረጋቸውን እየገለጹ ነው።

ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነት እንዲያበቃ በርካታ አገራት፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ድርድር እንዲጀመር በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቢቆዩም እስካሁን ምንም አይነት ውጤት አልታየም።