የአማራ ክልል በህወሓት ተይዘው በቆዩ አካባቢዎች የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ቡድን ማሰማራቱን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, FANA
የአማራ ክልል የህወሓት አማጺያን ይዘዋቸው በነበሩ አካባቢዎች በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ቡድን ማሰማራቱን አስታወቀ።
ጥናቱን የሚያስተባብረው የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንሙት በለጠ፤ ከክልሉ መሥሪያ ቤቶች ብቻ 120 የሚጠጉ ባለሙያዎች የተሳተፉበትና የተለያዩ የሙያ ስብጥሮች ያሉት ቡድን በክልሉ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት ለማጥናት መሰማራት መጀመራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ጥናቱ የሚከናወነውም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከአማጺው ኃይል በማስለቀቅ በተቆጣጠሯቸው በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ወሎ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በሰሜን ጎንደርና በደቡብ ጎንደር ዞኖችና ሁለት ከተሞች ነው።
"የጥናቱ ዋና ዓላማ በህወሓት አማጺያን ተይዘው በነበሩ የክልሉ ዞኖችና ከተሞች በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ትክክለኛ የጉዳት መጠን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማጥናት ነው" ያሉት አቶ አንሙት፤ ጥናቱ መልሶ ለማቋቋም፣ ታማኝና ተጨባጭ ማስረጃን በማደራጀት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ እንዲሁም አጥፊውን ተጠያቂ ለማድረግ የሚውል እንደሆነ አብራርተዋል።
ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ የህወሓት ኃይሎች በርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ቆይተዋል።
አማጺያኑ ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን በመስፋፋት ወደ አዲስ አበባ ለመጠጋት የሞከሩ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጦሩን ለመምራት ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተከትሎ በአጭር ጊዜ በርካታ ከተሞች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ከአራት ወራት በላይ በአማጺያኑ ሥር የቆየችው የወልዲያ ከተማን ጨምሮ የሰሜን ወሎ ዞን በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መግባታቸው የተገለጸውም ባሳለፍነው ቅዳሜ ነበር።
የህወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረው በቆዩባቸው አካባቢዎች በሰዎች፣ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በአየር ማረፊያ፣ በሙዚየምና ታሪካዊ ቦታዎች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በሌሎች የመንግሥት ተቋማትና መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተዘግቧል።
አቶ አንሙት እንደተናገሩት፤ በክልሉ የደረሰውን ውድመት የሚያጠናው ቡድኑ ጤና፣ ግብርናና ትምህርትን ጨምሮ 16 መሥሪያ ቤቶችን፣ 10 ዩኒቨርስቲዎችን እንዲሁም የፌደራል ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን ያሳተፈ ነው።
ኤጀንሲው በጥናት ቡድኑ የተካተተው ቤት ለቤት ያለውን የጉዳት መጠን ለማጥናት ሲሆን፤ ባለሙያዎቹ ከባድ ጥፋት የደረሰባቸው ከተሞች ላይ እንደሚሰማሩ ኃላፊው ገልጸዋል።
ለዚህም ወደ 200 የሚጠጉ የኤጀንሲው ሠራተኞች በጥናት ቡድኑ ውስጥ መካተታቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።
ከአስሩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ባለሙያዎችም በእያንዳንዱ የጥናት ቡድን ውስጥ ተካተዋል።
በዚህም የባህር ዳርና ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች በደቡብ ጎንደር፣ የደባርቅ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች በዋግ ኽምራ እና በሰሜን ጎንደር፣ የደብረ ማርቆስ እና የእንጂባራ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ወልዲያን ጨምሮ በወሎ ግንባር፣ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች በሰሜን ሸዋ፣ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ብሔረሰብ አስተዳደር እንደሚሰማሩ አቶ አንሙት አስረድተዋል።
የጥናት ቡድኑ ጦርነት በተካሄደባቸው ስድስት አቅጣጫዎች ተከፋፍሎ የሚሰማራ ሲሆን እያንዳንዱ ቡድን 16 ባለሙያዎችን ያካተተ ነው ተብሏል።
አንዱ ቡድን በውስጡ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መሠረተ ልማት፣ ማሕበራዊ፣ ኮሚዩኒኬሽንና ትምህርት የሚያጠኑ አራት የባለሙያዎች ቡድኖችን መያዙንም አቶ አንሙት ገልጸዋል።
ከአንድ ወር በፊት የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ የደሴ እና ኮምቦልቻ አካባቢዎችን እንዲሁም ሰሜን ሸዋን ሳያካትት በህወሓት ኃይሎች ተይዘው በተለቀቁና ተይዘው በነበሩ የክልሉ ዞኖች ውስጥ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ለቢቢሲ ማስታወቁ ይታወሳል።
የቢሮው ኃላፊው አቶ አንሙት እንዳሉት፤ በአምስቱ ዞኖች ማለትም በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎንደር፣ በዋግ ኽምራ እና በደቡብ ወሎ በከፊል በሚገኙ 45 ወረዳዎች ውስጥ 280 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ዘረፋና ውድመት በአማጺያኑ ተፈጽሟል ብለዋል።
በክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ከተለያዩ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ጋር በጥምረት የተሠራው ይህ የዳሰሳ ጥናት በተለይ በግብርናው ዘርፍ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ማመላከቱን ኃላፊው መናገራቸው ይታወሳል።















