የወሎ ዩኒቨርስቲ ሙሉ ሥራውን ለመጀመር እስከ ሁለት ዓመት ሊያስፈልገው ይችላል ተባለ

ወሎ ዩኒቨርስቲ

የፎቶው ባለመብት, Wollo University

በህወሓት ኃይሎች ውድመትና ዝርፊያ እንደተፈጸመበት የተነገረው የወሎ ዩኒቨርስቲ አስፈላጊው ጥገናና ቁሳቁሶች ተሟልተውለት ሙሉ ለሙሉ ወደ ማስተማር ሥራው ለመመለስ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት እንደሚያስፈልገው ተገለጸ።

በዩኒቨርስቲው የተለያዩ ካምፓሶች ላይ በተፈጸመው በዚህ ጥፋት የመማር ማስተማር ሥራውን ያቆመው ዩኒቨርስቲው፤ የመማሪያ ክፍሎቹ፣ ቤተሙከራዎቹ፣ የመኝታ ክፍሎቹና ሌሎች ለዕለት ከዕለት ሥራው የሚያስፈልጉት ክፍሎቹ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት እንደደረሰባቸው ዶክተር አማረ ምትኩ፣ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በወሎ ዩኒቨርስቲ የደሴና የኮምቦልቻ ካምፓሶች ላይ ስለደረሰው ጉዳት መጠን ለቢቢሲ በዝርዝር የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ "የወደሙ ህንጻዎች አሉ፣ የላብራቶሪ ግብዓቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድተዋል፣ የወደሙም የተዘረፉም አሉ" በማለት ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙንና መዘረፉን ገልጸዋል።

እንደዚሁም በከፍተኛ ወጪ የተሰራ የመመረቂያ አዳራሽና የአስተዳደር ህንጻ መውደሙንም ጠቅሰው "የተለያዩ የመገልገያዎች እና ኮምፒውተሮች ሌሎችም እንዳሉ የተዘረፉ ወይንም ደግሞ ባሉበት የወደሙ" መኖራቸውን ገልጸው ንብረቶቹን መልሶ ለመተካት ባለው የገበያ ዋጋ ግምት "የራሱ የዩኒቨርሲቲው ብቻ፤ ከ10 ቢለዮን ብር በላይ ሊደርስ ይችላል" ሲሉ የጉዳቱን መጠን አመልክተዋል።

በዩኒቨርስቲው ካምፓሶች ላይ በህወሓት አማፂያን የደረሰው ውድመትና ዘረፋ በገንዘብ ሲተመን ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር አማረ ምትኩ፣ በትምህርት ተቋሙ የደረሰው ውድመት "በአጠቃላይ ዩኒቨርስቲው የለም ከሚባልበት ደረጃ ላይ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

ዶ/ር አማረ ምትኩ ከመንግሥት በኩል ዩኒቨርስቲው በአስቸኳይ ወደ ወደ መማር ማስተማር ሥራው እንዲገባ የሚያስችል ድጋፍ ከተደረገ በፍጥነት ሥራ የሚጀምርበት ዕድል እንዳለ አስታውቀው፣ ነገር ግን የደረሰው ውድመት "ከፍተኛ" መሆኑን ይናገራሉ።

ዩኒቨርስቲው ወደ መማር ማስተማሩ ሥራ መቼ እንደሚገባ የተጠየቁት ዶ/ር አማረ ምትኩ፣ ዩኒቨርስቲው አሁን ባለበት ሁኔታ ሁሉንም ተማሪዎች፣ ከሁሉም የትምህርት ዘርፍ መቀበል እንደማይቻል አመለክተዋል።

ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ ከተመረጡ የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎችን መቀበል እንደሚቻል ጠቅሰው፣ እነዚህም የማኅበረሰብ ሳይንስ እና ተመራቂ ተማሪዎችን፣ የዎርክሾፕ እና የላብራቶሪ ሥራቸውን የጨረሱ ተማሪዎች ትምህርት እንዲቀጥሉ ማድረግ፣ ብሎም ተመራቂ ተማሪዎችን ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል መኖሩን አብራርተዋል።

"ለምሳሌ ላይብረሪዎች ደህና ናቸው፤ መጽሐፍቱ ደህና ናቸው። የሃርድ ዲስክ ዝርፊያ የተፈጸመባቸውን ኮምፒውተሮች በቀላሉ ቀይሮ፤ የተጓደሉትን ማሟላት ቢቻል በተወሰነ ደረጃ ወደ ትምህርት ሂደቱ መመለስ ይቻላል።"

በተጨማሪም ከተማሪዎች ማደሪያ ክፍል ውስጥ አልጋዎች ቢኖሩም ፍራሾች መወሰዳቸውን የገለጹት ኃላፊው "ፍራሽ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ሆኖ በአጭር ጊዜ ተባብሮ ማሟላት የሚችልበት ዕድል ሊኖር ይችላል" ብለዋል።

አክለውም "እንደዚያ ካላደረግን ተጠግኖ ሁሉም ወደ ነበረበት እስኪመለስ ከጠበቅን ከዓመት እስከ ሁለት ዓመት ጊዜ ሊወስድ ይችላል" ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲው እስካሁን ድረስ ትምህርት ለመጀመር የወሰነው ውሳኔ አለመኖሩን የሚናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ ነገር ግን ያለውን ሁኔታ ለትምህርት ሚኒስቴር በማስታወቅ በተወሰነ ደረጃ ትምህርት የመጀመር ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል።

"ሶሻል ሳይንስ፣ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉ የቤተሙከራ ሥራ የሌላቸው የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎችን ተቀብለን ለማስተናገድ ይቻላል" በማለት ለምረቃ ጥቂት ወራት የቀራቸውንም ትምህርት ለማስጨረስ እንደሚቻል ገልጸዋል።

የመማር ማስተማሩን ሂደት ቀደም ሲል በነበረበት ሁኔታ ማስቀጠል አዳጋች መሆኑን የሚጠቅሱት ዶ/ር አማረ፣ በውድመቱ ያልተነካ የዩኒቨርስቲ ው ክፍል እንደሌለ ገልጸዋል። በዚህም የሁለት ኮሌጅ ቢሮዎች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን፣ መስተዋታቸው መሰባበሩንም ጨምረው አስረድተዋል።

ዶ/ር አማረ በዩኒቨርስቲው ሁለት ካምፓሶች ላይ እንዴት ጉዳት እንደደረሰ ሲያብራሩም የህወሓት ኃይሎች የዩኒቨርስቲው ካምፓሶቹን የማዘዣ እና የስልጠና ቦታቸው በማድረግ ሲገለገሉባቸው እንደነበር አብራርተዋል።

"የኮምቦልቻ ካምፓሱን ስልጠና ቦታቸው ነበር ያደረጉት፤ የደሴ ካምፓሱን ደግሞ የማዘዣ ጣቢያ አድርገው የስብሰባ ቦታቸውም ነበረ" በማለት አማጺያኑ ተቋሙን ሲገለገሉበት እንደነበር አመልክተዋል።

በዚህም ሳቢያ የጥቃት ኢላማ ሆኖ "በወገን ጦርም በድሮን የተመቱ ህንጻዎች" መኖራቸውን አመልክተው፣ አብዛኛው ጉዳትና ዝርፊያ በአማጺያኑ እንደተፈጸመ አክለው ገልፀዋል።

በዩኒቨርስቲው ላይ ከደረሰው ውድመትና ዘረፋ በተጨማሪ በተቋሙ ውስጥና በዙሪያው ሰዎች ተገድለው የተገኙ ሲሆን በአካባቢው ሕዝብ እንዲቀበሩ መደረጋቸውን ለዶ/ር አማረ ምትኩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በዩኒቨርስቲው በር ላይ እንዲሁም በውጪ በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ዙሪያ የተቀበሩ መኖራቸውን የጠቀሱት ዶ/ር አማረ "እሱን የማጽዳት ሥራ በቅርቡ የሚሰራ ይሆናል" ብለዋል።

በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ከወራት በፊት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተዛመተው ጦርነት ወደ ደቡብ ወሎ ተስፋፍቶ የህወሓት ኃይሎች ደሴንና ኮምቦልቻን ተቆጣጥረው ለአንድ ወር በቆዩበት ጊዜ ነበር በወሎ ዩኒቨርስቲ ላይ የተጠቀሰው ከባድ ጉዳት የደረሰው።

ደሴና ኮምቦልቻ ከተማ ከአማጺያኑ ቁጥጥር ስር ነጻ የወጡት ባለፈው ሳምንት ሲሆን በተመሳሳይ በተለያዩ የመንግሥትና የሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት በህወሓት ኃይሎች መፈጸሙን መንግሥት ገልጿል።