አሜሪካ በአማራና በአፋር በክልሎች በህወሓት ተፈጽመዋል የተባሉ በደሎች እጅጉን አሳስበውኛል አለች

የፎቶው ባለመብት, MANUEL BALCE CENETA
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በአማራ እና በአፋር ክልሎች በትግራይ ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የንብረት ውድመቶች በእጅግ አሳሳቢ መሆናቸውን ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ባወጡት መግለጫ፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በትግራይ ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ አስደንጋጭ የጭካኔ ድርጊቶችንና በሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ የተፈጸሙ ውድመቶችን በተመለከተ እየወጡ ያሉ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች አሜሪካንን አሳስቧታል ብለዋል።
የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ በንጹሃን ዜጎች ላይ የኃይል እርምጃዎችን ከመወሰድ መቆጠብ አለባቸው ሲሉ አክለዋል።
"የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት እነዚህን ሪፖርቶችን በመመርመር ትክክለኛነታቸውን እንዲያጣሩ እና ጥፋተኛ የሆኑትን ተጠያቂ ለማድረግ ሁሉን አካታች እና ግልጽ ሥርዓት እንዲከተሉ እንጠይቃለን" ብለዋል ኔድ ፕራይስ በመግለጫቸው።
መግለጫው አሜሪካ፤ ይህ ጦርነት እንዲቋጭ የምትሻው በዲሎማሲያዊ መንገድ ብቻ ነው፤ ለተጎጂዎች ያልተገደበ እርዳታ ሊደርስም ይገባል የሚል አቋም እንዳላት አንፀባርቋል።
ባለፈው ሳምንት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ለውጪ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የህወሓት አማጺያን ተቆጣጥረው በቆዩባቸው የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ብለው ነበር።
"በግል እና በሕዝብ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፤ የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል" ያሉት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፤ በጋሸና እና በሰሜን ሸዋ በምትገኘው አንጾኪያ ሕወሓት በንጹሃን ላይ የጅምላ ግድያዎች ስለመፈጸሙ ሪፖርቶች አሉ ብለው ነበር።
ከቀናት በፊት ሂዩማን ራይትስ ዋች የተባለው የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ ተቋም በአማራ ክልል ጭናና ቆቦ በተባሉ አካባቢዎች የህወሓት ኃይሎች ከ50 በላይ ሰላማዊ ሰዎችን በተለያዩ ቦታዎች በጅምላ መግደላቸውን ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
ይህንንም ተከትሎ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገለግሎት በአማራና አፋር ክልሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ በህወሓት ኃይሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ ውድመቶችን እና ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ገለልተኛ አጣሪ አካላት በወረራ ስር ወደነበሩ ቦታዎች በመግባት የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
ባለፈው ሳምንት ኔድ ፕራይስ በትግራዩ ጦርነት የመንግሥታቸውን አቋም፤ ግጭቱ በወታደራዊ እርምጃ መፍትሄው እንደማይመጣ አስታውሰው፤ "ዲፕሎማሲን የመጀመሪያው፤ የመጨረሻው እና ብቸኛው አማራጭ" ነው ብለው ነበር።
ጨምረውም ተዋጊ ኃይሎች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እንዲፈቅዱ ልዩነቶቻቸውን በውይይት ለመፍታት አሳታፊ የሆነ ብሔራዊ ውይይት ሊደረግ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ከዚህ ቀደም አሜሪካ የትግራዩ ጦርነት እንዳይቆም፣ እንዲቀጥል አልያም ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዳይደርስ ባደናቀፉ ግለሰቦች ላይ የቪዛ እቀባ መጣሏ ይታወሳል።
አንድ ዓመት ባስቆጠረው እና ከትግራይ ክልል ተሻግሮ አማራ እና አፋር ክልሎች በደረሰው ጦርነት፤ ተሳታፊ የሆኑ ተዋጊ ኃይሎች በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ክስ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የአማራ ክልል ኃይሎች በትግራይ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የሚል ክስ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
በእነዚህ አካላት ላይ ከሚቀርቡ ክሶች መካከል ሰዎችን ያለ ፍርድ መግደል፣ ጾታዊ ጥቃቶችን ማድረስ እና የሰብዓዊ እርዳታ ተጎጂዎች ጋር እንዳይደርስ መከልከል የሚሉት ይገኙበታል።















