ጦርነቱ በመደበኛና በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ ያስከተለው ውጤት

የውጭ መገናኛ ብዙኃንን ዘገባ በመቃወም ከተካሄዱ ሰልፎች አንዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የውጭ መገናኛ ብዙኃንን ዘገባ በመቃወም ከተካሄዱ ሰልፎች አንዱ
    • ፀሐፊ, በቢቢሲ
    • የሥራ ድርሻ, ሞኒተሪንግ

በሰሜን ኢትዮጵያ እተካሄደ ስላለው የእርስ በርስ ጦርነት በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ከሚነገረው ባሻገር ማኅበራዊ ሚዲያውም ሌላው መድረክ ሆኗል።

ጥላቻን የሚሰብኩ፣ የብሔር ክፍፍልን የሚያባብሱ ጽሑፎች ይሰራጫሉ። ማኅበራዊ ሚዲያው ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ ያለው ምልከታ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደርና ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችን ለመድረስም ውሏል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ዓመት አለፈው።

እንደ አውሮፓውያኑ በጥቅምት 30 የኢትዮጵያ መንግሥት ትዊተር እና የውጭ አገር መገናኛ ብዙኃን "የመንግሥት ለውጥን እየደገፉ" እንደሆነና "በህወሓት ወገንተኞች ጥቅም ላይ እንደዋሉ" ተናግሯል።

የመንግሥት ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም "በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በመገናኛ ብዙኃን እና በምሁራን ዘንድ ኢትዮጵያን የሚደግፉ ድምጾች እየታፈኑ ነው" ብለዋል።

"ከዚህ በተቃራኒው ስለ መንግሥት ለውጥ የሚያወሩና ህወሓትን የሚደግፉ ድምጾች እንዲጎሉ ተደርጓል" ሲሉም አክለዋል።

ትዊተር "የህወሓትን ጭካኔና ውሸት የሚያጋልጡ፣ ኢትዮጵያን የሚደግፉ ድምጾችን" ኢላማ አድርጓል ብለው እንደሚያምኑ ቃል አቀባዩዋ መናገራቸው ይታወሳል።

ትዊተር ጥቅምት 30 #NoMore [ከእንግዲህ ይብቃ] የሚለውን ሀሽታግ ሲያስተዋውቁ የነበሩ በርካታ ታዋቂ ገጾችን አግዷል።

ይህ ንቅናቄ የኢትዮጵያን እና ኤርትራን መንግሥት የሚደግፍ ነው።

ሐሰተኛ ዜና ዘገባዎች ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረ?

በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተደራሽነት ከ20 በመቶ ያንሳል።

ሆኖም ግን ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች ማኅበራዊ ሚዲያን ድምጻቸውን ለማስተጋባት ይጠቀሙበታል።

ህወሓት እና የኦሮሞ ነጻነት ጦርን "አሸባሪ" የሚሉ በርካታ የመንግሥት ገጾች አሉ።

የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ የተባለው የመንግሥት የትዊተር ገጽ ላይ የውጭ መገናኛ ብዙኃንን ዘገባዎች በተደጋጋሚ ይተቻሉ።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚጻፉ መልዕክቶች ብዙ ተከታታይ አላቸው።

ጥቅምት 4 በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ የነበረ ጽሑፍ መሰረዙ ይታወሳል።

ጽሑፉ የኢትዮጵያ ሕዝብ "እንዲታጠቅ" እና "ህወሓትን እንዲቀብር" የሚያሳስብ ነበር።

ኢትዮጵያውያን ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፎችም ብዙ ተከታታይ አላቸው። አስተያየትም ይሰጥባቸዋል።

በበይነ መረብ ስለ ጦርነቱ የሚደረገው ንግግር በፖለቲከኞች እና ምሁራንም ይዘወራል።

በሁለቱም ወገን ያሉ ቡድኖች ያልተረጋገጡ አልያም ጊዜ ያለፈባቸው ምስሎች፣ ቪድዮዎች፣ ጽሑፎች ያጋራሉ። ይህም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን አባብሶታል።

ነውጥ የሚያነሳሱ ወይም ግጭት የሚያጭሩ ጽሑፎችን በመቆጣጠር ረገድ ፌስቡክ ኃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም ተብሎ ይወቀሳል።

ፌስቡክ በበኩሉ ሰኔ ላይ፤ 65 አካውንቶችን፣ 52 ገጾችን፣ 27 ቡድኖችን ከፌስቡክ ላይ እና 32 አካውንቶችን ከቴሌግራም መሰረዙን ይፋ አድረጓል።

እነዚህ ገጾች ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ሲሠሩ የነበሩና የድርጅቱን መርህ የጣሱ መሆናቸው ተገልጿል።

ገጾቹ መነሻቸውን ያደረጉትና ያነጣጠሩትም በኢትዮጵያውያን ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል ጥቅምት 6 ትዊተር በብዙኃን ዘንድ መነጋጋሪያ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን ወደ ፊት ገጹ የሚያመጣበት (ትሬንድስ) አሠራር በጊዜያዊነት ከኢትዮጵያ ማገዱን አስታውቋል።

"ሰዎችን ለአካላዊ ጉዳት የሚያጋልጡ" ጽሑፎች በገጹ መሰራጨታቸውን ነው ትዊተር ለውሳኔው ምክንያት ያደረገው።

መገናኛ ብዙኃን ለምን ይወቀሳሉ?

ገለልተኛ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እና የውጭ መገናኛ ብዙኃን "ሐሰተኛ መረጃ አሰራጭተዋል" የሚል ክስ ይሰነዘርባቸዋል።

ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን የሚደርስባቸው ጫና፣ በትግራይ ክልል ካለው የመገናኛ መሠረተ ልማት በቋረጥ ጋር ተደምሮ ስለ ጦርነቱ መዘገብን ፈታኝ አድርጎታል።

ጥቅምት 10 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፤ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ሮይተርስ እና ኤፒ "ጥላቻን በማስተጋባትና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመዳፈር" ኮንኗል።

ይህ መግለጫ የወጣው አማጽያኑ ቡድኖች ድል አስመዝግበው ወደ አዲስ አበባ እያመሩ መሆኑ ከተዘገበ በኋላ ነበር።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አማጽያኑ "የትግራይ መከላከያ ሠራዊት" ተብለው እንዳይጠሩ ማስጠንቀቂያ መስጠቱም ይታወሳል።

አዲስ ስታንዳርድ "የአሸባሪው ህወሓትን አጀንዳ በማስፈጸም" በሚል ክስ ለጥቂት ቀናት ታግዶ እንደነበርም አይዘነጋም።

በቀድሞዋ የሴቶች እና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ የተመሠረተው ነበድ የቴሌቭዥን ጣቢያ ስለ ጦርነቱ ከመንግሥት ትርክት የወጣ ዘገባ በመሥራቱ ታግዷል።

የቀድሞዋ ሚኒስትር በጦርነቱ ወቅት የደረሱ ወሲባዊ ጥቃቶች እንደሚያሰጓቸው መጋቢት ላይ ተናግረው ነበር።

ከዚያም "ሕሊና እና ሥነ ምግባር" የሚነካ ብለው ከኃላፊነታቸው ለቀዋል።

ከሳምንታት በፊት መንግሥት ወታደራዊ መረጃዎች እንዲሰጡ ከተፈቀደላቸው አካሎች ውጭ ስለ ጦር ሜዳ ውሎ ወይም ድል መዘገብን ከልክሏል።