በኢትዮጵያ 23 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ

የአፋር ክልል ተፈናቃዮች ለቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኛ ሠራተኛ መረጃ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, IFRC

የምስሉ መግለጫ, የአፋር ክልል ተፈናቃዮች ለቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኛ ሠራተኛ መረጃ ሲሰጡ

በመላው ኢትዮጵያ ወደ 23 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ማኅበራት ፌደሬሽን እንዲሁም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በጋራ ገለጹ።

አንድ ዓመት ያለፈው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ኑሮ እና መተዳደሪያ እንዳመሰቃቀለው የጋራ መግለጫለው ላይ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ ጌታቸው ጠሀ፤ ከሰሜኑ ጦርነት በተጨማሪ ድርቅ፣ የምግብ እጥረት፣ ወረርሽኞች፣ የሰብል በሽታዎች እንዲሁም የዜጎች መፈናቀል ለአደጋ ተጋላጭነትን አባብሰውታል።

ጨምረውም "በአፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ የሚሊዮኖች ሕይወት አደጋ ላይ ሊወድ ይችላል። . . . በኢትዮጵያ ወደ 23 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል" ሲሉ የችግሩን አንገብጋቢነት አስረድተዋል።

መግለጫው የተራድኦ ድርጅቱ አሁን ላይ አሳሳቢ ሰብአዊ ቀውስ እንደገጠመው ዋና ጸሐፊው አቶ ጌታቸው "ከዚህ ቀደም በነበሩ ችግሮች ላይ ጦርነቱ ተጨምሮ ሰብአዊ ቀውሱን አብሶታል" ማለታቸውን አመልክቷል።

ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በአንበጣ ወረርሽኝ፣ በዝናብ እጥረት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲሁም በሌሎች ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ መሰናክሎች የምትፈተን አገር ከመሆኗ አንጻር የጦርነቱ መጨመር የእርዳታ ጠባቂ ዜጎችን ቁጥር እናዳናረው ተገልጿል።

የምግብ እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ ሌሎችም ሰብአዊ እርዳታዎች የግድ ያስፈልጋሉ።

ምግብ፣ ውሃ፣ ገንዘብ፣ የጤና አገልግሎት፣ መጠለያ፣ መሠረታዊ የቤት ቁሳቁሶች፣ ንጽህና መጠበቂያ፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ እና የደኅንነት ጥበቃ በአስቸኳይ እንደሚያስፈልጉ ተገልጿል።

የሰብአዊ እርዳታ ተቋሙ የአስቸኳይ ጊዜ የሚያደርገውን ድጋፍ ከፍ እንዳደረገ በመግለጽ ይህም ለ660,000 ዜጎች ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ ገንዘብ፣ የጤና አቅርቦት እና ንጽህና መጠበቂያ እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።

"በአፋጣኝ እርዳታ የሚሹ ተለይተው በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታው ይካተታሉ" ይላል የተቋሙ መግለጫ።

የተቋሙ የአፍሪካ ኃላፊ መሐመድ ሙክታር "ቡድናችን ከአጋራቹ ጋር በመተባበር እርዳታ ለመስጠት የተቻለውን ጥረት እያደረገ ቢሆንም ካለው ፍላጎት አንጻር በቂ የእርዳታ ግብአት የለንም" ብለዋል።

እየጨመረ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ለማዳረስ ወደ 27 ሚሊዮን የስዊዝ ፍራንክ እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን የምግብ፣ መጠለያ እና ገንዘብ ድጎማ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን እና ጂቡቲ የተሰደዱ ሰዎችም ከቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ድጋፍ ተሰጥቷቸዋል።

መፈናቀልና የእርዳታ አቅርቦት

በተያያዥ ዜና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አሁንም ከምዕራብ ትግራይ፣ ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች ሰዎች እየተፈናቀሉ መሆኑን ትላንት ባወጣው ሪፖርት ጠቁሟል።

ከአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ከሸዋ ሮቢት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደ አጎራባች አፋር ክልል ገብተዋል።

በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከወልዲያ እና ላሊበላም ተፈናቅለዋል።

ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሰሜን ምዕራብ ዞኖች ተጠልለው ይገኛሉ።

ትግራይ ክልል

በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ 44 እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች በአፋር በኩል የትግራይ መዲና መቀለ መግባታቸው በድርጅቱ ድረ ገጽ ሰፍሯል።

"ከዚያ ሳምንት በፊት 157 እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ተልከዋል። በትግራይ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት ለማሟላት በቀን ከሚያስፈልገው 100 እርዳታ ጫኝ መኪና አንጻር፤ የተላከው በቂ አይደለም" ብሏል ኦቻ።

ከሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ወራት በልዩ ሁኔታ የተወሰኑ መድኃኒቶች በሰብአዊ እርዳታ በረራ አማካይነት ከመላካቸው ውጪ ከነሐሴ ጀምሮ ወደ ትግራይ ነዳጅ፣ መድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያ እንዳልተላከ ገልጿል።

ከጥቅምት 25 እስከ ኅዳር 1 ድረስ በትግራይ ክልል ለ43,000 ሰዎች እርዳታ እንደተደረገ እና ይህም አዲስ የተፈናቀሉ 10,000 ዜጎችን እንደሚጨምር ኦቻ አስታውቋል።

አማራ ክልል

"በደሴ እና ኮምቦልቻ በቅርቡ የተደረገው ቅኝት እንደሚጠቁመው የጤና ተቋማትን እና ምግብ ማከማቻን ጨምሮ የሕዝብ አገልግሎት መስጫዎች ተዘርፈዋል" ይላል ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ።

ከጥቅምት ወዲህ በአማራ ክልል ለ947,000 ዜጎች እርዳታ ተደርጓል። ይህም ባለፈው ሳምንት ለ370,000 የተሰጠውን እርዳታ ይጨምራል።

በተጨማሪም ለሦስት ሆስፒታሎች እና ለ19 የጤና ተቋማት የጤና ተቋማት ድጋፍ መስጠት ተጀምሯል። 26 ተንቀሳቃሽ የጤና እና ምግብ ሰጭ ቡድኖችም እየሠሩ እንደሆነ ተገልጿል።

አፋር ክልል

ባለፈው ሳምንት ወደ 16,000 የሚጠጉ ዜጎች በአፋር ክልል እርዳታ እንደተሰጣቸው ኦቻ ገልጿል።

ከ26,000 በላይ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ውሃ እና ንጽህና መጠበቂያን ጨምሮ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

በተጨማሪም በክልሉ 30 ተንቀሳቃሽ የጤና እና ምግብ ቡድኖች እየሠሩ ይገኛሉ።