በመንግሥት ቅሬታ የቀረበበት ትዊተር በኢትዮጵያ ጉዳይ ገለልተኛ ነኝ አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚሰጡ ድምጾችን እያፈነ ነው ተብሎ ቅሬታ የቀረበበት ግዙፉ ማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረክ፣ ትዊተር በኢትዮጵያ ጉዳይ ገለልተኛ ነኝ አለ።
ትናንት ማክሰኞ 21/2014 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ትዊተር "ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚሰጡ ድምጾች እያፈነ ነው" ማለታቸውን ተከትሎ ተቋሙ "በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ገለልተኛ ነኝ" ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ቢልለኔ ስዩም በመግለጫቸው በትዊተር "ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚሰጡ ድምጾች እየታፈኑ ነው" በአንጻሩ፤ ህወሓትን የሚደግፉና የመንግሥት ለውጥ እንዲካሄድ የሚቀሰቅሱ ሃሳቦች እንዲንጸባረቁ ይፈቅዳሉ ብለው ነበር።
ቢልለኔ በትዊተር ውስጥ የህወሓት ደጋፊዎች ስለመግባታቸው ለተቋሙ የፖሊሲ ቡድን ማሳወቃቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያው ትዊተር ቃል አቀባይ ይዘቶችን እና አካውንቶች በተመለከተ የተቋሙ መመሪያዎች በሁሉም ላይ ያለ ልዩነት ተፈጻሚ እየሆኑ ነው ብለዋል።
ማኅበራዊ ሚዲያው ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ደኅንነት ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ የትዊተር መመሪያና ደንቦችን ጥሰው የተገኙ በርካታ አካውንቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ስለመውሰዱ ቃል አቀባይዋ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ትዊተር እርምጃ የተወሰደባቸው አካውንቶች 'ፕላትፎርም ማኒፒዩሌሽን' እና 'ስፓም ፖሊሲን' በመተላለፋቸው ነውም ብሏል።
ከትዊተር አሰራር በተለየ መልኩ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም አሳሳች የሆኑ መልዕክቶችን በአንድ ጊዜ በርካታ ተጠቃሚዎችን ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ትዊተር 'ፕላትፎርም ማኒፒዩሌሽን' ሲል ይገልጸዋል።
ትዊተር ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ማለቱ ይታወሳል። ግዙፉ ማኅበራዊ ሚዲያ ግጭት ቀስቃሽ እና ሰዎችን ዝቅ የሚያደርጉ ይዘቶችን እንደማያስተናግድ ገልጾ ነበር።
ትዊተር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ በተለይ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን የበርካቶችን ትኩረት ያገኙ ርዕሶችን ወይም 'ትሬንዶች' ማሳየት አቁሟል።
ማኅበራዊ ሚዲያው ለቢቢሲ በኢሜይል በሰጠው መልስ፤ "ከገጼ ላይ ያስወገድኳቸው ሐሰተኛ እንዲሁም ተመሳሳይ ይዘቶችን መልሶ ለመለጠፍ እና ሐሰተኛ ተሳትፎዎችን ለመፍጠር የተከፈቱ አካውንቶች ናቸው" ብሏል።
የትዊተር ቃል አባይ "በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን ሁኔታ በቅርብ መከታተላችንን እንቀጥላለን" ካሉ በኋላ መንግሥትን ጭምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር እየተገናኙ መሆኑን አመልክተዋል።
"ከፖለቲካዊ ማንነት እና ከየትኛውም ርዕዮት ዓለም ገለልተኛ ሆነን እንቀጥላለን" የሚሉት የትዊተር ቃል አባይ፤ ግጭት ቀስቃሽ ወይም ጉዳት የሚያስከትል መረጃ በትዊተር አማካኝነት እንዳይሰራጭ ገደብ ማድረግ አላማቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ትዊተር የሚደርሱትን ቅሬታዎችን ወይም ይግባኝ ለመመልከት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን የትዊተር ቃል አቀባይ ጨምረው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ትዊተር በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ የመጣ ተጠቃሚ ካላቸው የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረኮች አንዱ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ ወገኖች በወገንተኝነት ትችት ይቀርብበታል።















