በአፋር ክልል ከ60 በላይ የጤና ተቋማት በህወሓት ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, AMHARA COMMUNICATION
የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ውስጥ በቆዩባቸው ጊዜያት ከ60 በላይ የጤና ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ ለቢቢሲ ገለጹ።
"ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አንድ ሆስፒታል እና ወደ 62 የጤና ተቋማትም ወድመዋል" ሲሉ የተከሰተውን አስረድተዋል።
ጉዳት የደረሰው በ17 የጤና ጣቢያዎች፣ በአንድ ሆስፒታል እና በ42 የጤና ኬላዎች ላይ እንደሆነ እና ጉዳቱም የተቋሙ ግንባታ መሰባበር እና የመድኃኒት ዘረፋን እንሚጨምር አቶ ያሲን ተናግረዋል።
በክልሉ ያለውን የጤና ሥርዓት "አንኮታኩተው ነው የሄዱት። የደረሰው ጉዳት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ይደርሳል" ሲሉም አክለዋል።
የጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ እስከሚካሄድ ድረስ ተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድን በመላክ ለሕዝቡ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነም ኃላፊው አስረድተዋል።
"ከዚህ በፊት ወደ 20 ቡድን ነበረን። አሁን ከ5 እስከ 10 የሚደርስ ተጨማሪ ተንቀሳቃሽና ጊዜያዊ እርዳታ ሰጪ ቡድን አሰማርተናል። ለመርዳት አስቸጋሪ የሆኑ አካባቢዎች ላይ አብዳ የሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት እየሠራ ነው" ብለዋል።
እነዚህ ቡድኖች ክትባት መስጠት እና ማዋለድን ጨምሮ የመጀመሪያ ሕክምና አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል። በተለይም ወደ ጤና ጣቢያ ሪፈር በማድረግ እና ሰዎችን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ረገድ ሚናቸው የጎላ እንደሆነም አክለዋል።
ሆኖም ግን ይህ አገልግሎት መደበኛ የጤና ተቋም አገልግሎትን ሊተካ ስለማይችል ክፍተት እንደተፈጠረ ጠቁመዋል።
በተለይም ዞን 2 እና ዞን 4 እንዲሁም ዞን 5 በተባሉት አካባቢዎች የጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል ብለዋል።
ለረዥም ጊዜ ሕክምና ሳያገኙ የቆዩ የገጠር ነዋሪዎች አሁን ላይ የሕክምና ተቋማቱ አገልግሎት ይሰጣሉ ብለው አስበው ቢሄዱም ሕክምና ለመስጠት እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
የአፋር የጤና ሥርዓትን ለማቋቋም እና መሣሪያ ለማሟላት ከ20 ዓመት በላይ እንደወሰደ በመጥቀስ፤ "ይህን ሁሉ ጊዜ ባለሙያ የለፋበት ነበር። አርብቶ አደሩም ወደ ጤና ተቋም እየመጣ በአግባቡ እየተጠቀመ ባለበት ሰዓት ነው ውድመቱ የደረሰው" ብለዋል።
በጭፍራ ከተማ ከሚኖሩ ተፈናቃዮች መካከል ሦስት መንትዮች አርግዛ የነበረች ነፍሰ ጡር ሴት "ዛፍ ስር ነው የተገላገለችው" ሲሉ አቶ ያሲን ማኅበረሰቡ የገጠመውን ችግር አስረድተዋል።
ሕጻናት በከፍተኛ ሁኔታ ለአልሚ ምግብ እጥረት እንደተጋለጡም አያይዘው ጠቅሰዋል።
ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በአጠቃላይ አንድ ቦታ ላይ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገው ተናግረዋል።
በተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ካሉ ሰዎች ውጪ ለተቀረው ማኅበረሰብ ክትባት ማቅረብ ስላልተቻለ ተቋርጦ እንደቆየም ገልጸዋል።
"የተወሰኑ አጋሮች ክትባት ለመስጠት እየሞከሩ ነው። ግን እሱም ከባድ ነው" ሲሉ አክለዋል።
በሌላ በኩል ተከታታይ መድኃኒት የሚያስፈልጋቸው የስኳር፣ የኤችአይቪ፣ የቲቢ እና ሌሎችም ታማሚዎች መድኃኒት እንደተቋረጠባቸው የጤና ቢሮ ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"እነዚህ ታማሚዎች ሸሽተዋል። እነሱን ለማግኘት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ቀን ከሌት እየተሯሯጡ ነው" በማለት እየተደረ ያለውን ጥረት ተናግረዋል።
አንዳንድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አብረዋቸው እየሠሩ ቢሆንም ውጊያውን ተከትሎ አካባቢውን ትተው የወጡ እንዳሉም ሳይናገሩ አላለፉም።
"ያሉትም ለደኅንነት ስለሚሰጉ ያላቸውን ኃይል ሙሉ በሙሉ እየተጠቀሙ አይደለም" በማለት ያለውን ክፍተት አስረድተዋል።
የወደመውን ሆስፒታል በተወሰነ ደረጃ እንዲሁም ወደ 5 ጤና ጣቢያዎችን መልሶ ሥራ ለማስጀምር ቁሳቁሶች እንደተላኩ ተናገሩት አቶ ያሲን፤ በአምስቱም የክልሉ ዞኖች የመልሶ ግንባታ ባለሙያዎች እንደተሰማሩ ጨምረው ገልጸዋል።
ከደረሰው ጉዳት አንጻር የጤና ሥርዓቱን ለመመለስ ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ ለመናገር እንደሚከብድ የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ ጠቁመዋል።
በመስከረም ወር ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ጦርነት ሳቢያ በአማራና አፋር ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማትና የጤና መሠረተ ልማቶች ከፍተኛ መሆናቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።
ሚኒስቴሩ በአማራና በአፋር ክልሎች የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የወደሙ ከአንድ ሺህ 500 በላይ የጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ብሎ ነበር።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዳለው በአማራ ክልል ብቻ 20 ሆስፒታሎች እና 277 ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት አቋርጠዋል፣ ከዚህ በተጨማሪ 14 ሆስፒታሎች እና 153 ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም 642 ጤና ኬላዎች ተዘርፈዋል።
በአፋር ክልል ደግሞ አንድ ሆስፒታል፣ 10 ጤና ጣቢያዎች እና 38 የጤና ኬላዎች ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል ብሎ ነበር።












