በአማራና አፋር ክልሎች ከ1500 በላይ ጤና ተቋማት መውደማቸውና መዘረፋቸው ተነገረ

በአማራ ክልል ጉዳት ከደረሰባቸው የህክምና ተቋማት አንዱ

የፎቶው ባለመብት, AMHARA COMMUNICATION

የምስሉ መግለጫ, በአማራ ክልል ጉዳት ከደረሰባቸው የህክምና ተቋማት አንዱ

በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ጦርነት ሳቢያ በአማራና አፋር ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማትና የጤና መሠረተ ልማቶች ከፍተኛ መሆናቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በአማራና በአፋር ክልሎች የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የወደሙ የጤና ተቋማትን በተመለከተ እንዳስታወቀው በድምሩ ከአንድ ሺህ 500 በላይ የጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዚህ ጦርነት በአማራ ክልል ብቻ 20 ሆስፒታሎች እና 277 ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት አቋርጠዋል።

ከዚህ በተጨማሪ 14 ሆስፒታሎች እና 153 ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም 642 ጤና ኬላዎች ተዘርፈዋል። ይህ አሐዝ በአማራ ክልል ብቻ የተከሰተ ነው።

በአፋር ክልል ደግሞ አንድ ሆስፒታል፣ 10 ጤና ጣቢያዎች እና 38 የጤና ኬላዎች ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል ሲሉ ሚኒስትሯ ታናግረዋል።

በዚህም ሳቢያ በአካባቢዎቹ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከመሠረታዊ አስከ ከፍተኛ የጤና አገልግሎቶች እንዳያገኙ እንቅፋት መፈጠሩ ተገልጿል።

ዶ/ር ሊያ ታደሠ እነዚህን ውድመትና ዘረፋ የደረሰባቸውን ጤና ተቋማት ወደ አገልግሎት ለመመለስ ከፍተኛ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።

በዚህ ጦርነት ድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አምቡላንሶችም ላይ ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በሁለቱ ክልሎች ማለትም በአማራና በአፋር ክልል በነበረው ጦርነት በድምሩ 21 ሆስፒታሎች፣ 287 ጤና ጣቢያዎች እና 1ሺህ 200 ጤና ኬላዎች በድምሩ ከ1ሺህ 508 በላይ ጤና ተቋማት ላይ ዘረፋና ውድመት ደርሶባቸዋል ብለዋል ዶ/ር ሊያ።

የጤና ሚኒስቴር በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ለተፈናቀሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የጤና ድጋፍና መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ተብራርቷል።

በጦርነቱ ምክንያት ከተፈናቀሉት ሰዎች መካከል 71ሺህ የሚሆኑት ነፍሰ ጡር እና ጡት የሚያጠቡ እናቶች እንደሆኑ ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት ምክንያት ከጤና ተቋማት ባሻገር በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ በትምህርት የትምህርት ተቋማት ላይ ጭምር ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ማሳወቁ ይታወሳል።

በአማራ ክልል ጉዳት ከደረሰባቸው የህክምና ተቋማት አንዱ

የፎቶው ባለመብት, AMHARA COMMUNICATION