የትግራይ ጦርነት፡ 'ለልጄ ሆስፒታል ለማግኘት ሦስት ቀናት በእግር ተጉዣለሁ'

አቶ ሰለሞን ተፈሪና ልጃቸው ጌትሽ
የምስሉ መግለጫ, አቶ ሰለሞን ተፈሪና ልጃቸው ጌትሽ

በተራራማዋ ትግራይ ክልል የሚኖሩ ሰዎች በጦርነት እና በረሃብ መካከል ይገኛሉ።

የመንግሥት ወታደሮች ከጎረቤት ኤርትራ ጦር ጋር ከክልሉ የሥልጣን መንበር ከተባረረው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር ከጠቅምት ወር ጀምሮ ጦርነት በመግጠማቸው የሰብዓዊ ቀውስ ተከትሏል።

የቢቢሲው ዘጋቢ ቃልኪዳን ይበልጣል ተደራሽነቱ አስቸጋሪ የሆነውን አካባቢ በድጋሚ ጎብኝቷል።

Short presentational grey line

የትግራይ መዲና መቀለ የመረጋጋት ስሜት ይታይባታል።

ብዙ የንግድ ቤቶች እና ቢሮዎች ተከፍተዋል። ካለፉት ወራት ጋር ሲነጻጸር ብዙ የሰዎች እንቅስቃሴ ሲኖር የሚታዩት ወታደሮች ቁጥር ደግሞ አነስተኛ ሆኗል።

መደበኛ ገጽታው ግን ሁሉንም አያሳይም።

መቀለ የሚገኘው አይደር ሆስፒታል በግጭቱ ከተጎዱ መንደሮች እና ከተሞች በመጡ ህሙማን ተጨናንቋል።

ከእነዚህም መካከል የ8 ዓመቱ ጌትሽ ሰለሞን ይገኝበታል። የልብ ህመምተኛ የሆነው ጌትሽ ግጭቱ ከጀመረ ወዲህ ችግሩ ተባብሶበታል።

ሀገረ ሰላም ከተማ ከወላጆቹና ከአምስቱ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር የሚኖረው ጌትሽ የአካባቢያቸው ጤና ጣቢያ በጦርነቱ በመጎዳቱ 50 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዞ መቀለ ለመድረስ ተገዷል።

"ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች እና ጥሩ ኢኮኖሚ ነበረን። የሆነ ነገር ከፈለግን ወደ እነሱ በፍጥነት እንሄድ ነበር" ብለዋል የ13 ዓመቱ ጌትሽ አባት አቶ ሰለሞን ተፈሪ።

አዘውትሮ ህክምና የሚፈልገው ጌትሽ ወደ ህክምና የሚደረገው ጉዞ ግን ሁሌም ቀላል አይደለም።

"[በአንድ ወቅት] መንገዶቹ ተዘግተው ስለነበር ለሦስት ቀናት ያህል በእግር መጓዝ ነበረብን" ይላሉ አቶ ሰለሞን።

ሁለት ሴቶች በመቀለ ከተማ
የምስሉ መግለጫ, መቀለ

ወደ ወታደራዊ ካምፕ የተቀየረው ክሊኒክ

ሀገረ ሰላም አቅራቢያ በሚገኝ መንደር ያለውን አለአሳ ጤና ጣቢያን ጎብኝቻለሁ። ክሊኒኩ እስካሁን ድረስ አገልግሎት እየሰጠ አይደልም። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ወታደሮች በአንድ ወቅት ካምፕ አድርገውት ነበር።

አሁን የእርዳታ ሠራተኞች የሚገኙበት ሲሆን ምግብ ለመቀበል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች [በአብዛኛው ሴቶች እና ሕጻናት] በቦታው ተሰብስበዋል።

ብዙዎቹ ግጭቱ ባየለበት ወቅት ቤታቸውን ጥለው በአቅራቢያው ባሉ ተራሮች ተደብቀዋል። ግጭቱ ከተነሳ ወዲህ ወደ 1.7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከትግራይ ክልል ተፈናቅለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም ሆኑ የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች የምግብ እጥረት እንዳለ ይናገራሉ። እየተሰራጨ ያለው እርዳታም በቂ አይደለም።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ ባለፈው ሳምንት ትግራይ ውስጥ ረሃብ አለ ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያም በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ ላይ ይህንኑ አስተያየት ደግመዋል።

በድብቅ ወጣው የሎውኮክ የንግግር ቅጂ ላይ "የእርዳታ ሠራተኞች ተገድለዋል፣ ምርመራ ይደረግባቸዋል፣ ተደብድበዋል፣ ለተራቡ እና ለተሰቃዩ ሰዎች እርዳታ እንዳይወስዱ ታግደዋል እናም እንዳይመለሱ ተነግሯቸዋል።"

የኢትዮጵያ መንግሥት ረሃብ መኖሩን ያስተባብላል። በክልሉ ሥርዓት ወደ ቀድሞ ሁኔታው እየተመለሰ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት እየተስፋፋ ነው ይላል።

የምግብ እርዳታ የሚቀበሉ ሰዎች
የምስሉ መግለጫ, የምግብ እርዳታ ሲከፋፈል

ካህናት ተገድለዋል

ግጭቱ ለተቸገሩም ሆነ ለተሰደዱት የመሸሸጊያ ስፍራ ሆነው ለረዥም ጊዜ ሲታዩ በነበሩት የሐይማኖት ተቋማት እና የቅርስ ቦታዎችም ተርፏል።

በምሥራቅ ትግራይ ተራራ አናት ላይ በምትገኘው ፍሬዳሹ መንደር የሚገኝን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ጎብኝቻለሁ።

የ32 ዓመቱ ቄስ አብርሃ የገና ዕለት ማለዳ ላይ ነበር በጥይት የተመቱት።

አባታቸው አቶ ተክለሐይማኖት ገብረአረጋዊ እንደተናገሩት ቤተክርስቲያኗን ሊከፍቱ ሲያመሩ በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን ተናግረዋል።

አቶ ተከለሐይማኖት በዚህ ምክንያት ብዙ ህመም ስለሚፈጠርባቸው ወደ ቤተክርስቲያን መሄድ ማቆማቸውን ተናግረዋል።

ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ100 የማያንሱ ካህናት፣ ዲያቆናት እና መዘምራን መገደላቸውን ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጽህፈት ቤት የተገኘ ሰነድ ያስረዳል።

ከኤርትራ ጋር በሚዋሰነው ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው አዲግራት ከተማ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ በቦንብ ከመጎዳቱ ባለፈ የትምህርት ቤቱ ቤተመጽህፍት እና የቀብር ቤቱ ተጎድቷል።

"ያለፉት ሰባት ወራት ለእኛ የቅዠት ያህል ነበሩ። ኅብረተሰቡ ከሁሉም አቅጣጫዎች በታጠቁ ኃይሎች ተጥለቅልቋል" ሲሉ የአካባቢው ካህን አቡነ ተስፋሥላሴ ገልጸዋል።

"ፍርስራሾቹ በቅርቡ እንደገና ሊገነቡ ይችላሉ። የሰው አእምሮ፣ የሰው ልብ፣ የቤተሰብ ግንኙነት፣ ማኅበረሰቦች እና ኅብረተሰቡ ከረጅም ጊዜ እሴቶቹ ጋር አብረው ተጨፍልቋል" ብለዋል።