በትግራይ ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ውሏል- ተመድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ በትግራይ ያለው ሁኔታ ከታሰበው በላይ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
"ሴቶችንና ታዳጊዎችን በተቀናጀ ሁኔታ በመድፈር ለማሸበርና ለማሰቃየት እየተጠቀሙበት ነው። የኤርትራ ወታደሮች ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀሙበት ነው። የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች ይከበባሉ፣ ይደበደባሉ እንዲሁም ማስፈራሪያዎች ይደርሳቸዋል" ብለዋል።
ኃላፊው በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በትግራይ ላይ ባደረገው የዝግ ስብሰባ ላይ ነው ይህንን የተናሩት።
ቢቢሲ ኃላፊውን በምክር ቤቱ ውስጥ ያደረጉትን ንግግር ለማግኘት የቻለ ሲሆን በዚህም "በትግራይ በእርግጠኝነት ረሃብ አለ" ብለዋል።
በትግራይ ያለውን ቀውስ ረሃብ በማለት ለመፈረጅ አንዳንዶች ቢጠነቀቁም ኃላፊው ግን ያለ ምንም አሻሚ ቃል "ረሃብ አለ" ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ረሃብ አለ የሚለውን አይቀበለውም፤ በክልሉ ውስጥ በበቂ ሁኔታ እርዳታ እያከፋፈለ መሆኑንም ከሰሞኑ በተሰጠው መግለጫ ተጠቅሷል።
ኃላፊው በክልሉ ስላለው ሁኔታም ሲናገሩ "የእርዳታ ሠራተኞች ተገድለዋል፣ ተዋክበዋል፣ ተደብብድበዋል እንዲሁም በረሃብ ለሚሰቃዩ ሰዎች እርዳታ እንዳያደርሱ ከመታገዳቸው በተጨማሪ ተመልሰው እንዳይመጡም ተነግሯቸዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በምግብ እጦት የሞቱ ሰዎች እንዳሉ ሪፖርት አድርጓል" ብለዋል።
በቅርቡ የትግራይን የምግብ ሁኔታ የገመገመው ሪፖርት "ካታስሮፊ" በሚል ጉዳትን እንደሚያስከትል ቢፈርጅም ኃላፊው ግምገማው ያለውን የከፋ ሁኔታ አቅልሎ እንዳየም ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪም "ወጣትና ታዳጊ ወንዶች በአብዛኛው በምሽት እንደሚወሰዱና አንዳንድ ጊዜም እንደሚገደሉ" ተደጋጋሚ ሪፖርቶችን ዋቢ አድርገው ተናግረዋል።
"በአሁኑ ወቅት ግልፅ የሆነው ነገር በተጨባጭ ሁኔታ የኤርትራ መከላከያ ኃይል ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ ሕግጋት ጥሰዋል" ብለዋል።
ምንም እንኳን በክልሉ በተወሰነ መልኩ እርዳታ ማድረስ ቢቻልም ማርክ ሎውኮክ እንደሚሉት "በአስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሚሊዮኖች እርዳታ እያገኙ አይደሉም።"
በሚያስፈልገው ደረጃ ምላሽ እየተገኘ እንዳልሆነም በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።
ለብሔራዊ ምርጫ እየተዘጋጀች ባለችው ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች የቀድሞውን የክልሉን አስተዳዳሪ ታማኝ የሚሏቸውን ኃይሎች ለማጥፋት አዲስ ውጊያ መጀመራቸውን ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።












