የኤርትራ ወታደሮች 'በቅርቡ' እንደሚወጡ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜን ኢትዮጵያ የትግራይ ክልል በሚካሄደው ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት የኤርትራ ወታደሮች "በቅርቡ" እንደሚወጡ በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ አምባሳደር ተናገሩ።
አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ግዛት ለመውጣት የቀራቸው "አንዳንድ ቴክኒካዊና የአፈጻጸም ጉዳዮች ናቸው" ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ወታደሮቹ እንዲወጡ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ቁርጠኝነት እንዳለና "በኤርትራውያኑ በኩልም ሁሉ ነገር ግልጽ" መሆኑን እንደተናገሩ አሶሺየትድ ፕሬስ አምባሳደሩን ጠቅሶ ዘግቧል።
አምባሳደሩ ይህንን የገለጹት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ በጸጥታው ምክር ቤት ቀርበው "ግጭቱ እንዲቆም ተደርጎ የኤርትራ ወታደሮች ካልወጡ የ1977 አይነቱ የከፋ ረሃብ ተመልሶ ቢከሰት ማንም መደነቅ የለበትም" ብለው ከተናገሩ በኋላ ነው።
ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግሥታት የተደገፈው በትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሁኔታ የሚመለከት ትንተና ይፋ መደረጉን ተከትሎ ሎውኮክ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ረሃብ አለ ብለው ተናገረው ነበር።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ረሃብ ተከስቷል የሚለውን ዘገባ አስተባብሎ በተለይ በትግራይ ክልል ውስጥ ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ከሌሎች የረድኤት ድርጅቶች ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።
በህወሓት ኃይሎችና በመንግሥት ሠራዊት መካከል ባለፈው ጥቅምት ወር ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ ከባድ ሰብአዊ ቀውስ መከሰቱን የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሲገልጹ ቆይተዋል።
በግጭቱ ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል ተብሎ የታሰብ ሲሆን 1.7 ሚሊዮን ነዋሪዎች ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን በረድኤት ተቋማት በኩል የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ባለፉት ሰባት ወራት ትግራይ ውስጥ በተካሄደው ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች አስገድዶ መድፈርና ጅምላ ግድያን ጨምሮ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም ይከሰሳሉ።
የኤርትራ ወታደሮች የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰት ትግራይ ውስጥ ፈጽመዋል ተብለው በተደጋጋሚ ሲከሰሱ የቆዩ ሲሆን ከጥቂት ወራት በፊት የሁለቱ አገራት መሪዎች ወታደሮቹ እንዲወጡ መስማማታቸው ተገልጾ ነበር።
በተለያዩ ጊዜያትም ወታደሮቹ መውጣት መጀመራቸው የተገለጸ ሲሆን ይህ ሂደት አስከ መቼ ተጠናቆ እንደሚያበቃ የተገለጸ ጊዜ የለም።















