ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት በትግራይ በሚያደርገው ምርመራ ሂደት ላይ ቅሬታዋን ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia
በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር ተያይዞ ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ምርመራ የሚያደረግ ቡድንን ለመሰየም የአፍሪካ ሕብረት "በተናጠል" መወሰኑ እንዳሳዘነው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ የአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን "የመርማሪ ኮሚሽን ማቋቋምን በተመለከተ በተናጠል ማስታወቁ ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት ከቀረበለት ግብዣ የወጣና ሕጋዊ መሠረት የጎደለው ነው" ብሏል።
ጨምሮም የአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ለምርመራው አስፈላጊውን ሁኔታ የሚያመቻቸውን ትክክለኛ አካሄድ አልተከተለም በማለት ቅሬታውን ገልጿል።
ትናንት ረቡዕ የአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል ስለተባሉት የመብት ጥሰቶች የሚያደርገውን ምርመራ ሐሙስ እንደሚጀምር በመጥቀስ የሚመለከታቸው በሙሉ ትብብር እንዲያደርጉለት ጥሪውን አቅርቦ ነበር።
ይህንን ተከትሎም ኢትዮጵያ ባለፈው መጋቢት ወር በትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ሁኔታ ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኝነቷን ገልጻ እንደነበር አመልክታለች።
በተከታይነት ከተደረገ ውይይት በኋላ ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ በጋራ ምርመራ ለማድረግ ያቀረበችውን ሐሳብ መቀበሉን የሚገልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መጻፉን መግለጫው አስታውሷል።
ነገር ግን ኮሚሽኑ አሁን እየወሰደ ያለው የተናጠል እርምጃ ምርመራውን ወጥ በሆነ የአሰራር ለማከናወን ፍላጎት ያለውን የኢትዮጵያ መንግሥትን "የትብብር መንፈስን የሚጎዳ ነው" ብሏል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ በርካታ ሪፖርቶች ሲወጡ ቆይተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገራት በተፈጸሙት በደሎች ዙሪያ ምርመራ ተደርጎ አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በእራሱ ተቋማትና ከአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመተባበር በጋራ ምርመራ ለማድረግ መስማማቱ አይዘነጋም።












