ኤርትራ 'ተጨባጭ ያልሆኑ ተደጋጋሚ ክሶች' ቀርበውብኛል ስትል ተቃወመች

በተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ ተወካይ

የፎቶው ባለመብት, @ERITREA_UN

የምስሉ መግለጫ, በተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ ተወካይ

ኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤትና የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ "ተጨባጭ ያልሆኑ ተደጋጋሚ ክሶችን" አቅርበውብኛል ስትል ተቃወመች።

ኒው ዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ ወኪል እንዳለው የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በሚወያይበት ጊዜ እንዲገኙ ወይም አስተያየት እንዲሰጡ እንዳልተጋበዙ አመልክቶ "የኤርትራን ገጽታ ለማበላሸት ተገቢ ያልሆነና ግልጽነት የሌለው" ያለውን ዘዴ ተቃውሞታል።

ማክሰኞ ዕለት ተደረገው የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ በሰሜን ኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ሁኔታ ከታሰበው በላይ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረው ነበር።

"ሴቶችንና ታዳጊዎችን በተቀናጀ ሁኔታ በመድፈር ሽብርና ስቃይ እየተፈጸመ ነው። የኤርትራ ወታደሮች ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀሙበት ነው። የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች ይከበባሉ፣ ይደበደባሉ እንዲሁም ማስፈራሪያዎች ይደርሳቸዋል" ሲሉም ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎ ኤርትራ የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣን ለምክር ቤቱ የኤርትራ ወታደሮች ይፈጽሙታል ያሉትን ድርጊት አስተባብላለች።

በተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ ወኪል ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ "ኤርትራ በትግራይ ክልል ውስጥ ፈጽሞ የሰብአዊ እርዳታ እንዳይደረስ እገዳ አላደረገችም። ኤርታራ "ምግብን እንደ ጦር መሳሪያ" ፈጽሞ አልተጠቀመችም፤ እንኳን አሁንና ከኢትዮጵያ ጋር የነጻነት ትግል በሚደረግበትና በድንበር ጦርነቱ ጊዜ እንኳን እንዲህ አይነት ነገር አልተፈጸመም" ብሏል።

በዝግ በተካሄደው የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባለሥልጣኑ ማርክ ሎውኮክ በትግራይ ክልል የኤርትራ ወታደሮች በሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ሰዎች ለረሃብ እየተጋለጡ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።

ጨምረውም ጦርነቱ ከቀጠለና የኤርትራ ወታደሮች የማይወጡ ከሆነ በ1977 የተከሰተው አይነት አሰቃቂ ረሃብ ሲከሰት "ማንም ሰው ሊደነግጥ አይገባም" በማለት ሎውኮክ አስጠንቅቀዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ግዛት "በቅርቡ ይወጣሉ" በማለት ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ጨምረውም የኤርትራ ወታደሮች መውጣትን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ቁርጠኛ እንደሆነና በኤርትራ በኩልም ግልጽነት እንዳለ ጠቅሰው የቀረው ነገር "አንዳንድ ቴክኒካዊና የአፈጻጸም ጉዳዮች ናቸው" ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የኤርትራ መንግሥት ግን የሚቀርበው ይህ ክስ ጸረ ኤርትራ ኃይሎች ለፖለቲካ ዓላማቸው ሲሉ የፈጠሩት ነው በማለት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑትን ማርክ ሎውኮክ ክሱን በመጠቀም "እራሳቸው ብቻ በሚያውቁት ምክንያት ኤርትራን ለመጉዳት" ተነስተዋል ብሏል።

የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ የነበረው የህወሓት ኃይሎች በአገሪቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት በክልሉ ከባድ ሰብአዊ ቀውስ መከሰቱን የረድኤት ድርጀክቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ገልጸዋል።

በግጭቱ ሳቢያ አስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ በትክክል ባይታወቅም በሺዎች የሚቆጠሩ ሳእሆን እንደማይቀር ይገመታል።

በጦርነቱ ሳቢያ 1.7 ሚሊዮን ክልሉ ነዋሪዎች ከቤታቸው መፈናቀላቸው የተነገረ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩት ድግሞ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ከተለያዩ ወገኖች የሚወጣው መረጃ ያመለክታል።