ኢትዮጵያ ዩኔስኮንና የዓለም ጤና ድርጅትን በቸልተኝነት ወቀሰች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኢትዮጵያ መንግሥት ዩኔስኮና የዓለም ጤና ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች አደረሱት የተባለውን ጥፋት ለማውገዝ አለመድፈራቸው እንዳሳዘናት ገለጸች።
ኢትዮጵያ እንዳለችው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆኑት ዩኔስኮና የዓለም ጤና ድርጅት ለውድመቱ እስከ አሁንም ዝምታን መምረጣቸው የሚያስተዛዝብ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን መልሶ በተቆጣጠራቸውና ለወራት በትግራይ አማጺያን እጅ ወድቀው የነበሩ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋት መድረሱን ገልጧል።
ይሁን እንጂ ዩኔስኮም ሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ክስተቱን አላወገዙም ብሏል።
የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ከበደ ደሲሳ ትናንት ረቡዕ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የትግራይ ኃይሎች በሺህ የሚቆጠሩ ተቋማት ላይ ጥፋትና ውድመትን አድርሰዋል።
ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ከፍተኛ እሰጣገባ ውስጥ መቆየቱ ይታወሳል።
ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው በዚህ ጦርነት እጅግ ከፍተኛ የተባለ ሰብአዊ ቀውስ የተከሰተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ ከትግራይ ክልል አልፎ በአፋርና አማራ ክልሎች በርካቶች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።
ጦርነቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ባሉ ማኅበራዊ መገልገያዎች፣ መሠረተ ልማቶች፣ በመንግሥትና በግል ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰ ተዘግቧል።














