የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ጦር ግንባር መዝመትና ውጤቱ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጦር ግንባር

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Prime Minister's Office

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጦር ግንባር
    • ፀሐፊ, በፋሩክ ቾቲያ
    • የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ኒውስ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ከሥልጣናቸው እናወርዳለን ብለው የዛቱትን የትግራይ አማጽያን ላይ አስደናቂ ውጊያ ለመምራት ወደ ጦር ግንባር የዘመቱ ሲሆን፤ በዚህም ቀደም ሲል የነበሩ የአገሪቱን ነገሥታትን ትዝታ ቀስቅሰዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኖቤል የሰላም ሽልማት 100ኛ አሸናፊ ተብለው የተሰየሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የወታደራዊ መለዮ ለብሰው፣ በቁጥቋጦና በተራራማ አካባቢዎች ሲዘዋወሩ፣ አድማሱን በጦር ሜዳ መነጽር እየቃኙና ወታደሮችን በዛፍ ጥላ ስር ሆነው ሲያናግሩ የሚያሳዩ ምስሎችና ቪዲዮዎች ወጥተዋል።

"ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለአገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ" ብለው ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ከማምራታቸው በፊት ባስተላለፉት መልዕክት።

በኖርዌይ የኦስሎ ኒው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የግጭት ጥናት ፕሮፌሰር ሸትል ትሮንቮል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ውሳኔ ከህወሓት ጋር በሚደረገው ጦርነት ላይ ለውጥ ለማምጣት እንደረዳ ምንም ጥርጥር የለውም ይላሉ።

"ፎቶዎቹ እንደሚጠቁሙት በጦር ሜዳው እየተዋጉ ሳይሆን ከጦር ሜዳው ቅርበት ላይ እንደነበሩ ቢያሳዩም ውሳኔው ፍሬያማ ነው" ይላሉ።

"የጄኔራሎቹን ሞራል ከፍ ያደረገ፣ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን ያጠናከረ፣ እንደ ኃይሌ ገብረሥላሴ ያሉ የአገር ጀግኖች ጦርነቱን ደግፈው እንዲወጡ፣ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጦር ሠራዊቱን እና የአማራ ሚሊሻዎችን ለመቀላቀል እንዲሰለፉ አድርጓል" በማለት ያክላሉ።

የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃቶች

ህወሓት የገጠመው ውድቀት ታላቅ ነበር። ተዋጊዎቹ ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በደብረ ብርሃን ከተማ ዙሪያ የነበሩ ቢሆንም በዚህ ወቅት ወደ ወልዲያ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንዲመለሱ ተገደዋል።

ይህ ማለት አማፂያኑ ትግራይን ከፌደራል መንግሥት የሥልጣን መቀመጫ ጋር የሚያገናኙ ቁልፍ ከተሞችን አጥተዋል።

በመቀለ ከተማ የተፈጸመ የድሮን ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, AC

የምስሉ መግለጫ, በመቀለ ከተማ የተፈጸመ የድሮን ጥቃት

ፕሮፌሰር ትሮንቮል እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደሮቻቸውን መሬት ላይ ባለው ውጊያ ላይ በማሰባሰብ እንዲሁም ከቻይና፣ ከቱርክ እና ከኢራን እንደተገኙ የሚነገርላቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖች ህወሓትን ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

"የቻይና ዊንግ ሎንግ II ድሮን ከፍተኛ ወታደራዊ አቅም እንዳለው የሚገለፅ ሲሆን ታንኮችን፣ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ማውደም እንዲሁም በእግረኛ ወታደሮች ላይ ገላጣ በሆነ ቦታ ቦምብ ይጥላል።"

ከዚሁ ጎን ለጎን መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ግፊትን በመቋቋም፣ ምዕራባውያን ኃይሎችን የህወሓት አጋር አድርጎ እየሳለም ነበር። ይህንን አስተያየትም ታላቁ ሯጭ ኃይሌ ገብረሥላሴም እንደሚጋራው ተናግሮታል።

"ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ የመን እና ሊቢያ እንዴት እንደወደሙ ወይም እንደተበታተኑ አይተናል። ኢትዮጵያ ግን ከ120 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት አገር ነች። ስለዚህ ይህችን አገር ለማተራመስ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት በእነሱ ላይ ጥፋት ሊያመጣ ይችላል" በማለት ኃይሌ ለመንግሥት ሚዲያ አስተያየቱን ሰጥቷል።

አክሎም "አፍሪካውያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንደሚረዱን አውቃለሁ። ለዘመናት ቅኝ አገዛዝን በጋራ ስንዋጋ ቆይተናል" ብሏል።

ፕሮፌሰር ትሮንቮል እንደሚሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ መንግሥታትን እና ሌሎች የምዕራቡ ዓለም ተቀናቃኝ የነበሩ አገራትን ድጋፍ ለማግኘት ትርክቶችን አዘጋጅተው በእንደዚሁ ቃና መናገር ጀመሩ።

"የጦርነቱ ጅማሮ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጁንታ ሲሉ የጠሩት ህወሓት ላይ ሕግ የማስከበር ሥራ እየተሰራ እንደነበር ተናገሩ፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የፓን አፍሪካዊነትን ትርክት በማካሄድ ህወሓትን የኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ተላላኪ ብሎ በመጥራት ለኢትዮጵያ ክብር ሲል እንደ ጥንቶቹ ነገሥታት እየታገልኩ ነው አሉ።"

ዝናቸው ናኘ

ጥቅምት መጨረሻ ላይ ህወሓት መንግሥታቸውን ለመጣል ያደረገውን ሙከራ ከጣልያን ወራሪዎች ጋር አመሳስለውታል። የጣልያን ቅኝ ገዢዎች በ1888 በአድዋ ጦርነት ላይ ከአማራ ብሔር የወጡትና የዘመናዊ ኢትዮጵያ መስራች ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጦር መሸነፋቸው ይታወሳል።

ለሠራዊቱ ድጋፍ ሰልፍ የወጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለሠራዊቱ ድጋፍ ሰልፍ የወጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

"በአገርም ውስጥም ሆነ በዲያስፖራ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እውነትን ለዓለም በመንገር ያደረጋችሁት ሚና የሚመሰገን ነው። ይህች ጥንታዊት አገር በሩቅ እና በቅርብ ኃይሎች የተጋረጠባትን የህልውና ስጋት በአንድነት ልንወጣ እንችላለን። እንደ የአድዋ ልጆችም ኢትዮጵያን ወደፊት እናሻግራለን" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

ህወሓት ለዓመታት ያህል በሽምቅ ተዋጊነት ከቆየ በኋላ በኢትዮጵያ ሥልጣን የተቆጣጠረው በ1983 ዓ.ም ነበር። አፋኙን አገዛዝ በመቃወም ታላቅ ተቃውሞን ተከትሎ የመጡትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን እስከያዙበት ጊዜ ድረስ በሥልጣን ላይ የበላይነቱን ይዞ ቆይቷል።

በመቀጠልም መቀመጫው ወደሆነው ትግራይ ክልል ያቀና ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካደረጉት ማሻሻያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ቅሬታ የተከሰተውን ከፍተኛ ፍጥጫ ተከትሎ ህወሓት አመፅ አስነስቷል።

መቀመጫቸውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረጉት የአፍሪቃ ቀንድ ተንታኝ አብዱራህማን ሰይድ እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ጦር ግንር በመሄድ ጦሩን በመምራት የብዙ ኢትዮጵያውያንን ክብር አትርፈዋል። አማፂያኑ እየገፉ በሄዱበት ወቅት ድጋፋቸው እየቀነሰ መጥቶ ነበር ይላሉ።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያቸውንና ትተው ወደ ጦር ሠራዊታቸው መቀላቀላቸው አስፈላጊ ከሆነ ለኢትዮጵያ ለመሞት መዘጋጀታቸውን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል" ይላሉ።

አፄ ምኒልክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አፄ ምኒልክ

"እሳቸው የነገሥታትን ታሪክ ያለማሰለስ ይጠቅሳሉ በአንድ ወቅትም እናታቸው ሰባተኛ ንጉሥ እንደሚሆኑ እንደተነበዩላቸው ለታዳሚዎች ተናግረው ነበር። ነገሥታቱ ሠራዊታቸውን ወደ ጦርነት ይመሩ ነበር፣ እርሳቸውም ተመሳሳይ ነገር አድርገዋል" ይላሉ።

ለፕሮፌሰር ትሮንቮል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወሰዱት እርምጃ ለሰላም የኖቤል ተሸላሚ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው። የኖቤል ሽልማቱ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በጠላትነት ይተያዩ የነበሩትን የኢትዮጵያና የኤርትራ ውጥረት እንዲረግብና በኢትዮጵያ ከአስርት ዓመታት የመንግሥት ጭቆና በኋላ የፖለቲካ ማሻሻያዎችን በማድረግ የተሰጣቸው ክብር ነው።

"ባራክ ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ የኖቤል ሽልማት አሸንፈው በአፍጋኒስታን የድሮን ጦርነት አካሂደዋል። ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ በዋይት ሐውስ ውስጥ ተቀምጠው ነው ጦርነቱን ሲመሩ የነበሩት። በዚህም ወደ ጦር ግንባር የቀረቡ የመጀመርያው ኖቤል አሸናፊ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ናቸው" በማለት ያስረዳሉ።

ቁልፍ መንገዶችን ለመቆጣጠር የተደገ ጦርነት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፋር ክልል ልዩ ኃይሎች እና ታጣቂዎች ቀድሞውንም በህወሓት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ወዳደረሱበት ምሥራቅ ግንባር ያቀኑት መጀመሪያ በኅዳር ወር ላይ ነበር።

"አፋሮች የተጋሩ ጎረቤቶች ናቸው። በባህልም እንደ ጠንካራ ተዋጊዎች ይቆጠራሉ። ከ15 ዓመት በላይ የሆነ ሁሉም የአፋር ወንድ ማለት ይቻላል ጠመንጃ ይታጠቃል። በዚህ ጦርነት ላይ የአፋር ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉ ሲሆን በህወሓት ላይ ጠንካራ ትግልን አሳይተዋል" ይላሉ አብዱራህማን።

"የህወሓት ታጋዮች ከስድስት ወር በፊት በመጀመሪያ ትግራይን ለቀው ለመውጣት ሲሞክሩ በአፋር ላይ ለፈጸሙት ግፍና በደል የቁጣ ምላሽን ነው" በማለት ያስረዳሉ።

አብዱራህማን ይህንን ህወሓት ወደ ጅቡቲ ድንበር ለመድረስ ያደረገውን ሙከራን ያከሸፈ በመሆኑ፣ በጦርነቱ ወቅት እንደ ትልቅ ለውጥ ያዩታል፤ "ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት ናት፣ የጅቡቲ ወደብ ደግሞ የምጣኔ ሀብት ደም ስሯ ነው" ይላሉ።

"ህወሓት ወደ ድንበር የሚወስደውን መንገድ ቢቆጣጠር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይሽመደመድ ነበር፤ ምንም አይነት ሸቀጥ ወደ አዲስ አበባ አይደርስም፣ እንዲሁም ዋና ከተማዋ በትግራይ ተዋጊዎች እጅ የመውደቅ እድሏ ከፍተኛ ይሆን ነበር" ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ከጦር ግንባር የተመለሱ ቢሆንም በያዝነው ሳምንት በአማራ ክልል ተጨማሪ ግዛቶችን ለመቆጣጠርና ወታደሩን ለመምራት ወደ ግንባር መመለሳቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።

ህወሓት በበኩሉ ታሪካዊቷን የውቅር አብያተ ክርስቲያናት መገኛ የሆነችውን የላሊበላ ከተማን በድጋሚ መቆጣጠሩን አስታውቋል።

ለፕሮፌሰር ትሮንቮል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ቢችሉም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማቸውን አጠልሽተዋል።

"የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የመጨረሻ ግብ ሰላም መሆን አለበት፣ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ጥሪዎችን ውድቅ አድርገዋል። ወታደሮቻቸው መጠነ ሰፊ ጥሰቶችን ፈጽመዋል" ይላሉ።

አቶ አብዱራህማን በበኩላቸው ህወሓት በኃይል ስልጣኑን ለመያዝ ከመወሰኑ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከመታገል ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም ብለዋል።

"ይህ ጦርነት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቀጥል እና እንዴት እንደሚያበቃ አናውቅም። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደካማ እንዳልሆኑና ዝም ብለው የማይገፉ እንዳልሆኑ አሳይተዋል" በማለት አቶ አብዱራህማን ያጠቃልላሉ።