ከወልድያ ወደ መቀለ የሚወስደው አውራ ጎዳና እንደተቆረጠ ተገለጸ

የመከላከያ ሠራዊት አባላት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች ጥምረት ባደረጉት መጠነ ሰፊ ጥቃት ከወልድያ ወደ መቀለ የሚወስደውን አውራ ጎዳና መቁረጣቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በትናንትናው ዕለት ታህሳስ 2፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

መግለጫው ጥምር ኃይሉ ከወልድያ ወደ መቀለ የሚወስደውን አውራ ጎዳናን በመቁረጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ጠቀሜታ አላቸው የተባሉትን የድሬ ሮቃና የሶዶማ አካባቢዎችን በመቆጣጠር ወደ ሃራ ከተማም እያመራ ነው ብሏል።

በምስራቅ ግንባርም ስትራቴጂያዊ ብሎ መንግሥት የጠቀሳቸውን የዞብል ሰንሰለታማ ተራሮችን እንዲሁም የአርጆ ፎኪሳ እና ቦረን ከተሞችን መቆጣጠሩን አመልክቷል።

ጥምር ኃይሉ በውጫሌ ግንባር የአምባሰል ከፍተኛ ሠንሠለታማ ተራሮችን ጨምሮ የሮቢትና የጎልቦን፣ በወረባቦ ወረዳ የሚሌ ኮትቻን፣ በሐብሩ ወረዳ የኮልቦን፣ የመርካታና የፋጂን አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ ወደ መርሳ ከተማ እያቀና መሆኑንም መግለጫው አስፍሯል።

የህወሃት ኃይሎች የቆቦ- ወልድያ አውራ ጎዳና መንገድ እንደተዘጋባቸው የጠቀሰው መግለጫው በጋሸና ላሊበላ በኩል ለማምለጥ ሞክረዋል ብሏል።

የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው በጋሸና እና በላሊበላ መስመር፣ በኮን ጋሸና መስመር 11 መደበኛ ክፍለ ጦሮች የተሳተፉበትን ኃይል ማሸነፋቸውን በትግራይ ክልል ቴሌቪዥን በዛሬው ዕለት በወጣው መግለጫ አስታውቀዋል።

የህወሃት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ኃይሎቻቸው በአማራ ክልል ያጋጠማቸውን በጎ ምላሽ ባሰፈሩበት በትናንትናው ፅሁፋቸው በድፍኑ "ጋሸናና አምባሰል ዛሬ ስለሆነውና ስለሚቀጥለው ሌላ ጊዜ እንመለሳለን" ብለዋል።

በትግራይ ክልል ተከስቶ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተዛምቶ የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞች በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከገቡ በኋላ ወደ ሰሜን ሸዋ ተስፋፍቶ ቆይቷል።

ከሳምንታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ተብሎ በተጠራው ዘመቻ የጥምር ኃይሉን እየመሩ የነበሩ ሲሆን በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ በርካታ ስፍራዎችም በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተገልጿል።

ከነዚህም ውስጥ በሰሜን ሸዋ የሚገኙ ከተሞችን ጨምሮ የደቡብ ወሎዎቹን ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች፣ ታሪካዊቷ ላሊባላ እና ወታደራዊ ጠቀሜታ አላቸው የተባሉ በአፋር ክልል ጭፍራ በአማራ ክልል ደግሞ የጋሸና ከተሞች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተዘግቧል።

በህወሓት አመራሮች በኩል ኃይሎቻቸው እንዲወጡ የተደረገው "በስልታዊ ውሳኔ" መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ለቢቢሲ ህወሃት "ሽንፈት ገጥሞት" እንደወጣ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተዛምቶ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው።