በአማራ ክልል በህወሓት ኃይሎች ተፈጸመ ስለተባለው ዘረፋ እና ውድመት እስካሁን የሚታወቀው

የፎቶው ባለመብት, ENA
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት ከወራት በፊት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ የህወሓት አማጺያን የተወሰኑ የአፋር ክልል አካባቢዎችን እንዲሁም በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ቆይተዋል።
አሁን ላይ የአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ነጻ መውጣቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች በአማጺያኑ እጅ ይገኛሉ።
በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በነበሩና አሁን በተለቀቁ ከተሞች በተለያዩ የመንግሥትና የሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ዘረፋ እና ውድመት መፈፀሙን የየአካባቢዎቹ አስተዳደሮች ገልጸዋል።
እስካሁን በአማራ ክልል ዘረፋና ውድመት ከተፈፀመባቸው ተቋማት መካከል ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የጤና ተቋማት፣ ፋብሪካዎች፣ ቅርሶች እና ሌሎችም ይገኙበታል።
አማጺያኑ ተፈፀመ ስለተባለው ዘረፋ እና ውድመት በዝርዝር ያሉት ነገር ባይኖርም በተደጋጋሚ የሚቀርብባቸውን ክስ ሲያስተባብሉ ቆይተዋል።
ፋብሪካዎች
ለአንድ ወር ያህል በአማጺያኑ ቁጥጥር ሥር በነበሩት የንግድና የኢንዱስትሪ ከተሞች በደሴና በኮምቦልቻ ውስጥ በርካታ ፋብሪካዎች መውደማቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ሐሙስ ዕለት የደረሰ ጉዳትን በተመለከተ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በመጀመሪያ ደረጃ በተደረገ ጥናት በሁለቱ ከተሞች 40 ፋብሪካዎች ላይ ውድመትና ዘረፋ ተፈጽሟል።
ከእነዚህ መካከል ስምንቱ በአጭር ጊዜ ወደነበሩበት ሊመለሱ በማይችሉበት ሁኔታ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰባቸው ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
ሌሎች ስምንት ፋብሪካዎች መካከለኛ ጉዳት፣ ቀሪ 24 ፋብሪካዎች ደግሞ መጠነኛ ውድመት እንደደረሰባቸው ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል።
መጠነኛ ውድመት የደረሰባቸውን መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ጥረት እተደረገ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ሌሎቹ ግን ጊዜ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
ውድመት በደረሰባቸው 40 ፋብሪካዎች ውስጥ ከ11 ሺህ በላይ ዜጎች ይሰሩ እንደነበርና አሁን ላይ እነርሱም ሆነ የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦች ለችግር ተዳርገዋል ብለዋል።
ሚኒስትሩ አማጺያኑ በተቋማቱ ላይ የፈጸሙት ዘረፋ በባለሙያ የተደገፈ ነበር በማለትም "ንብረቶች በባለሙያዎች ተፈትተው መወሰዳቸውን ተረድተናል" ሲሉ አመልክተዋል።
አቶ መላኩ አለበል አክለውም አማጺያኑ ከእነርሱ የተረፈውን ንብረት "የአካባቢው ነዋሪዎችን አስገድደው በካሜራ እየቀረጹ እንዲዘረፍ አድርገዋል" ሲሉም ከስሰዋል። ይህም ድርጊቱን እነርሱ እንዳልፈፀሙት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳየት ያለመ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቶች
የህወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸው በነበሩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከ4 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ ዝርፊያ እና ውድመት መፈፀሙን የክልሉ የትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
በዚህም ከ1.9 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች፣ ከ116 ሺህ በላይ መምህራን ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል ብሏል።
የወደሙትን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባትም ከ11 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በተማሪዎችና በወላጆች ላይ የደረሰውን የሥነ ልቦና ቀውስንም ለመጠገን ከፍተኛ ሥራ እንደሚያስፈልግም ኃላፊው ጠቁመዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው በትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን አመልክተው፣ ትምህርት ቤቶቹ ተመልሰው ሲገነቡ በተሻለ ጥራት እንደሚሆን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Health
የጤና ተቋማት
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ በአማራ ክልል ብቻ 2159 የጤና ተቋማት መውደማቸውን ተናግረዋል።
ይህ እስካሁን ባለው ዳሰሳ የታወቁ መሆናቸውን የገለፁት ሚኒስትሯ ሌሎች ያልታዩ ቦታዎች እንደሚኖሩና አሁንም በአማጺያኑ ተይዘው በሚገኙ ቦታዎች ያሉ በመኖራቸው ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ ይችላል ብለዋል።
ዘረፋ እና ውድመት ከተፈፀመባቸው የጤና ተቋማት መካከል 1706 ጤና ኬላዎች፣ 418 ጤና ጣቢያዎች፣ እና 34 ሆስፒታሎች መሆናቸውን ሚኒስትሯ አስረድተዋል።
"አንዳንዶቹ ህንጻቸው የፈራረሰ፣ ብዙዎቹ የተዘረፉ፣ በተቋማቱ ውስጥ የነበሩት የህክምና ቁሳቁሶች መንቀሳቀስ ያልቻሉት የወደሙ ናቸው" ሲሉም ጉዳቱ ሰፊ መሆኑን አብራርተዋል።
"በየትኛውም ቦታ በጦርነት ውስጥ እንዲህ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች አይነኩም" ያሉት ሚኒስትሯ ይህ አማጺ ቡድኑ ለሕዝብ አዘኔታ እንደሌለው የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በበኩሉ በተፈፀመው ዘረፋ እና ውድመት ሳቢያ 3.7 ሚሊየን በላይ ዜጎች ለሕክምና እጦት መዳረጋቸውን ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
በጤና ተቋማቱ ላይ በተፈፀመው ዘረፋ እና ውድመት ሳቢያ የተቋረጠውን የጤና አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለመስጠት ተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድኖችን እያሰማሩ መሆናቸውንም ሚኒስትሯ አክለዋል።
ተቋማቱን ለመጠገንም የተጀመሩ ሰፊ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም ዶ/ር ሊያ ጠቁመዋል።
የላሊበላ አየር ማረፊያ
ጥንታዊ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ያሉባትና በየጊዜው ከዓለም ዙሪያ በርካታ ቱሪስቶችን የምታስተናግደው ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማና አካባቢዋ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ለወራት በቆየችበት ጊዜ በተለያዩ ተቋማት ላይ ዝርፊያና ውድመት እንደተፈጸመ ክልሉ ገልጿል።
በተለይ የበርካታ ቱሪስቶች መግቢያ በር የነበረው በከተማዋ የአውሮፕላን ማረፊያ ላይ ሆን ተብሎ ከባድ ውደመት እንደደረሰበት ከተማዋ በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በገባችበት ወቅት ተገልጾ ነበር።
ይህንን ጥፋት የሚያሳዩ ምስሎችና ቪዲዮዎች በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ሲቀርቡ የነበረ ሲሆን፣ በአየር ማረፊያው ውስጥ የነበሩ የተለያዩ ቁሳቁሶች ተዘርፈው የቀሩት ደግሞ አገልግሎት በማይሰጡበት ደረጃ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ገልጿል።
አየር ማረፊያውን መልሶ አገልግሎት ለማስጀመር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የተነገረ ሲሆን፣ በአካባቢው እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ ታሪካዊቷ ከተማ ተመልሳ በአማጺያኑ እጅ መግባቷ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ተነግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Sm
የደረቅ ወደብ
በኢንደስትሪ ከተማዋ ኮምቦልቻ በህወሓት ኃይሎች ዘረፋ እንደተፈፀመበት የተነገረው በከተማዋ የሚገኘው ደረቅ ወደብ ነው።
በወደቡ በነበሩ ከ100 በላይ እቃዎችን በያዙ ኮንቴይነሮች ላይ ዘረፋ እና ውድመት መፈፀሙን የኢትዮጵያ ባሕር፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
ውድመት የደረሰባቸው እቃዎች ለሕዳሴ ግድብና ሌሎች ፕሮጀክቶች አገልግሎት ላይ የሚውሉ እንደነበሩም ዘገባው አመልክቷል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት
የወሎ ዩኒቨርስቲ በህወሓት ኃይሎች ውድመትና ዝርፊያ እንደተፈጸመበትና በቢሊዮን ብሮች የሚገመት ጥፋት እንዳጋጠመው ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።
በደሴ እና በኮምቦልቻ ካምፓሶች ላይ በተፈጸመው ጥፋት የመማር ማስተማር ሥራውን ያቆመው ዩኒቨርስቲው፤ የመማሪያ ክፍሎቹ፣ ቤተ ሙከራዎቹ፣ የላብራቶሪ ግብዓቶች፣ የመኝታ ክፍሎቹና ሌሎች ለዕለት ከዕለት ሥራው የሚያስፈልጉት ክፍሎቹ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት እንደደረሰባቸው ዶክተር አማረ ምትኩ፣ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊው ጥገናና ቁሳቁሶች ተሟልተውለት ሙሉ ለሙሉ ወደ ማስተማር ሥራው ለመመለስ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት እንደሚያስፈልገውም ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል።
ንብረቶቹን መልሶ ለመተካት ባለው የገበያ ዋጋ ግምት "የራሱ የዩኒቨርሲቲው ብቻ፤ ከ10 ቢለዮን ብር በላይ ሊደርስ ይችላል" ሲሉ የጉዳቱን መጠን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ የሚገኘው የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲም ከፍተኛ ዘረፋ እና ውድመት እንደተፈፀመበት ተገልጿል።
ቅርስ
በደሴ ከተማ የሚገኘውን የደሴ ሙዚየም ዘረፋና ውድመት እንደተፈፀመበት የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
ሙዚየሙ ባህልን፣ ታሪክንና ማንነትን የሚያሳዩ ሰነዶች ተሰድረው ይገኙበት የነበረ ነው።
በንጉሥ ሚካኤል ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበረው ይህ ሙዚየሙ፤ በ1973 ዓ.ም አሁን ወደሚገኝበትና ዲቪዥን ተብሎ ከሚጠራው ኮረብታማ ቦታ ላይ ተዛውሮ አገልግሎት እየሰጠ ነበር።
አማጺያኑ ከተማን ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ጊዜያት ከሙዚየሙ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች እንዲሁም መረጃዎች መዘረፋቸውን የወጣው መረጃ አመልክቷል።
በሙዚየሙ ውስጥ አፄ ሚኒሊክ ከጂቡቲ እና ከፈረንሳይ አገራት ጋር ግንኙነት ያደረጉበት የስልክ ቀፎ፣ በአደዋ ጦርነት ጊዜ ያገለገሉ የጦር መሣሪያዎች፣ በ1890 ከፈረንሳይ የተበረከተ መድፍ፣ በኢትዮ ጣሊያን ጦርነት ጊዜ የተማረከ የአየር መቃወሚያ፣
በተጨማሪም ከ450 ዓመት በላይ ያስቆጠሩ የሸክላ ውጤቶች፣ አፄ ሚኒሊክ የተጠቀሙባቸው የጦር ሜዳ መነጽሮች፣ ከወርቅና ከብር የተሰሩ ታሪካዊ ቅርሶች በሙሉ መዘረፋቸውና መውደማቸው ተነግሯል።

ከአንድ ወር ገደማ በፊት የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ የደሴ እና ኮምቦልቻ አካባቢዎችን እንዲሁም ሰሜን ሸዋን ሳያካትት በህወሓት ኃይሎች ተይዘው በተለቀቁና አሁንም ተይዘው ባሉ የክልሉ ዞኖች ውስጥ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ለቢቢሲ ማስታወቁ ይታወሳል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አንሙት በለጠ እንዳሉት በአምስቱ ዞኖች ማለትም በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎንደር፣ በዋግ ኽምራ እና በደቡብ ወሎ በከፊል በሚገኙ 45 ወረዳዎች ውስጥ 280 ቢሊዮን ብር የሚገመት ዘረፋና ውድመት በአማጺያኑ ተፈጽሟል ብለዋል።
የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ከተለያዩ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ጋር በጥምረት የተሰራው ይህ የዳሰሳ ጥናት በተለይ በግብርናው ዘርፍ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ መሆኑን ማመላከቱን ኃላፊው መናገራቸው ይታወሳል።














