ኢትዮጵያ ያለፈቃዷ የተላለፈውን የተመድ ውሳኔ እንደማትቀበልና እንደማትተባበር አስታወቀች
![የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት [ቆየት ያለ ፎቶ]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/13DB9/production/_122273318_017747a9-faba-4dfa-aab3-69b8fca629d7.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, UN HUMAN RIGHTS COUNCIL
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በድምጽ ብልጫ የተላለፈውን ውሳኔን እንደማትቀበለው አስታወቀች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ዓለም አቀፍ መርማሪ እንዲቋቋም መወሰኑን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ አንዳንዶች የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔን ለፖለቲካ ዓላማ ማራመጃነት ሲጠቀሙበት በድጋሚ ማየቷ እንዳሳዘናት በመግለፅ በውስጥ ጉዳይዋ ለመግባት የሚደረግ ሙከራን እንደማትቀበል፤ እንደማትተባበርም ገልጻለች።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ትናንት አርብ ታኅሣሥ 08/2014 ዓ.ም ባደረገው ልዩ ስብሰባ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ዓለም አቀፍ መርማሪ አካል ለማቋቋም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ማጽደቁ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ገንቢ በሆነ መንገድ ከሚመለከተው አካል ጋር በትብብር ለመሥራት በማሰብ ምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ እንዳያደርግ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቧን ያስታወሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መግለጫ፤ "አንዳንዶች በምክር ቤቱ አብላጫ ድምጽ በማግኘታቸው ዓላማቸውን ማሳካት ችለዋል" ብሏል።
መግለጫው አክሎም ውሳኔው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ፕሬዚደንት ካቀረበው ምክረ ሐሳብ ጋር የሚጻረር ነው ሲልም ኮንኖታል።
ይህ በአንዳንድ ምክር ቤት አባላት የተወሰደው እርምጃ በአንዲት ሉዓላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበትን አማራጭ መንገድ ለመፈለግ የሚደረግ ሙከራ እንጂ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ከማባባስ ያለፈ ጥቅም እንደሌለውም መግለጫው አትቷል።
"ከሁሉም በላይ የሚያሳስበው ግን በአብዛኞቹ ጉዳዮች ዓላማቸው ያልተሳካላቸው፣ በምክር ቤቱ በኩል ሌሎች የአሰራር ዘዴዎችን በመፍጠር በውስጣዊ ጉዳያቸው ጣልቃ እንዳይገባ ፈቃደኛ ባልሆኑ አገራት ላይ የማስገደጃ መሣሪያ መሆኑ ነው" ሲልም አክሏል።
ኢትዮጵያ ልዩ ስብሰባውንና ፖለቲካዊ ይዘት ያለውን የምክር ቤቱን ውጤት ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ ብሔራዊ ሉዓላዊነት እና ፖለቲካዊ ነጻነትን የሚጻረር ውሳኔን ውድቅ ያደረገችው ለዚህ ነው ብሏል መግለጫው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ከፈቃዷ ውጪ ከተጫነባት እና ከተቋቋመው አሠራር ጋር እንደማትተባበር ደጋግማ መግለጽ ትፈለጋለች ሲልም አጽንኦት ሰጥቷል።
በአውሮፓ ሕብረት የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እና በኢሰመኮ አማካይነት የተካሄደውን ምርመራ መሠረት በማድረግ እርምጃ እየወሰደ ባለበት መቅረቡ "ፖለቲካዊ ፍላጎት" አለው ስትል ተቃውማው ነበር።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም (ኢሰመኮ) በበኩሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በጦርነቱ ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች አዲስ የመርማሪ ቡድን ለማቋቋም ማቀዱ እንዳሳሰበው ለድርጅቱ በላከው ደብዳቤ ላይ ገልጿል።
ኢሰመኮ የምክር ቤቱ የልዩ ስበሰባ አካሄድ የጦርነቱ ተሳታፊዎች የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ቀደም ሲል የተደረገውን ዓለም አቀፍ ምርመራን ውድቅ አድርገው ሌላ የምርመራ ውጤትን እንዲቀበሉ "አደገኛ ሁኔታን ይፈጥራል" ሲል ነበር ስጋቱን የገለጸው።
የውሳኔ ሐሳቡ በድምጽ ብልጫ የጸደቀ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በምክር ቤቱ ድጋፋቸውን እና አጋርነታቸውን ያሳዩትን ያመሰገነ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግ የሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና ማስጠበቅ ግዴታዎችን ለመወጣት ጥረቷን አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን ገልጿል።
"ፍትሃዊ ያልሆነ፣ አንድ ወገንን ብቻ የማስገደድ እርምጃዎች፣ በሰብዓዊ መብቶች ሰብብ በውስጥ ጉዳይ መግባትም በቃ" ብሏል መግለጫ በማጠቃለያው ላይ።
በአውሮፓ ሕብረት ጠያቂነት በተካሄደው የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተውበታል።
በልዩ ስብሰባው ላይ የታደሙ የአፍሪካ አገራት "ሂደቱ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ አደጋን የሚጋብዝ ነው" ሲሉ ልዩ ስብሰባውንና የውሳኔ ሐሳቡን ተቃውመዋል።
በውሳኔ ሐሳቡ ላይ በተሰጠው ድምጽ መሠረት 21 አገራት ውሳኔውን ደግፈው ድምጽ ሲሰጡ፣ 15 አገራት የተቃወሙት ሲሆን 11 አገራት ደግሞ ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።
ሐሳቡን የደገፉት አገራት አርጀንቲና፣ አርሜኒያ፣ ኦስትሪያ፣ ባሃማስ፣ ብራዚል፣ ቡልጋሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ፊጂ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ የማርሻል ደሴቶች፣ ሜክሲኮ፣ ኔዘርላንድስ፣ ፖላንድ፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ፣ ዩክሬን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ኡራጓይ ናቸው።
በምክር ቤቱ ውሳኔውን የተቃወሙት ደግሞ ቦሊቪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሩን፣ ቻይና፣ ኮትዲቯር፣ ኩባ፣ ኤርትራ፣ ጋቦን፣ ሕንድ፣ ሊቢያ፣ ናሚቢያ፣ ፓኪስታን፣ ፊሊፒንስ፣ ሩሲያ፣ ሶማሊያ እና ቬንዙዌላ ናቸው።
በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉት 11 አገራት ባህሬን፣ ባንግላዲሽ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ሊቢያ፣ ማላዊ፣ ሚሪታኒያ፣ ኔፓል፣ ሴኔጋል፣ ሱዳን፣ ቶጎ እና ኡዝቤክስታን ናቸው።












