የተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ዓለም አቀፍ መርማሪ እንዲቋቋም ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባደረገው ልዩ ስብሰባ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ዓለም አቀፍ መርማሪ አካል ለማቋቋም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ አፀደቀ።
በአውሮፓ ሕብረት አማካይነት የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የፀደቀው በብልጫ ድምጽ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በልዩ ስብሰባው የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ 21 አገራት ሲደግፉት፣ 15 አገራት ደግሞ ተቃውመውታል፣ ሌሎች 11 አገራት ደግሞ ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።
ውሳኔውን ደግፈው ድምጽ የሰጡት አገራት 21 አገራት አርጀንቲና፣ አርሜኒያ፣ ኦስትሪያ፣ ባሃማስ፣ ብራዚል፣ ቡልጋሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ፊጂ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ የማርሻል ደሴቶች፣ ሜክሲኮ፣ ኔዘርላንድስ፣ ፖላንድ፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ፣ ዩክሬን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ኡራጓይ ናቸው።
የአውሮፓ ሕብረት ልዩ ስብሰባው እንዲካሄድና የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር አዲስ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም ሰኞ ዕለት ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በኩል ባወጣው መግለጫ ልዩ ስብሰባውንና የቀረበውን ሐሳብ የተቃወመው ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አማካይነት የተካሄደውን ምርመራ መሠረት በማድረግ እርምጃ እየወሰደ ባለበት ጊዜ ልዩ ስብሰባ መጥራት "ፖለቲካዊ ፍላጎት" አለው ሲል ተቃውሞት ነበር።
በልዩ ስብሰባው ላይ የታደሙ የአፍሪካ አገራት ልዩ ስብሰባውንና የውሳኔ ሐሳቡብ የተቃወሙ ሲሆን ሂደቱ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ አደጋን የሚጋብዝ በመሆኑ አጥብቀው እንደሚቃወሙት ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ ውሳኔውን የተቃወሙት አስራ አምስት አገራት ቦሊቪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሩን፣ ቻይና፣ ኮትዲቯር፣ ኩባ፣ ኤርትራ፣ ጋቦን፣ ሕንድ፣ ሊቢያ፣ ናሚቢያ፣ ፓኪስታን፣ ፊሊፒንስ፣ ሩሲያ፣ ሶማሊያ እና ቬንዙዌላ ናቸው።
በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉት 10 አገራት ደግሞ ባህሬን፣ ባንግላዲሽ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ማላዊ፣ ሚሪታኒያ፣ ኔፓል፣ ሴኔጋል፣ ሱዳን፣ ቶጎ እና ኡዝቤክስታን ናቸው።
በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በተለያየ ደረጃ እየፈጸሙ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዛሬው እለት ባደረገው ስብሰባ በድጋሜ አስጠንቅቋል።
ተመድ በጄኔቫ ባደረገው የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ጦርነቱ በቀጣናው ስጋት እንደደቀነና ተሳታፊ ወገኖች ከጦርነቱ ሊታቀብ ይገባል ሲል አሳስቧል ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ በመንግሥት የሚካሄደው የጅምላ እስራት መቀጠሉ በዚህ ስብሰባ የተጠቀሰ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞችን ጨምሮ ከ5 ሺህ- 7 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ታስረዋል ብሏል።
ባለፈው ዓመት ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ የአፋርና የአማራ ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች በተለያየ ደረጃ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግና የስደተኛ ህግ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
በአውሮፓ ሕብረት የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እና በኢሰመኮ አማካይነት የተካሄደውን ምርመራ መሠረት በማድረግ እርምጃ እየወሰደ ባለበት መቅረቡ "ፖለቲካዊ ፍላጎት" አለው ሲል ተቃውሞት ነበር።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም (ኢሰመኮ) በበኩሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በጦርነቱ ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች አዲስ የመርማሪ ቡድን ለማቋቋም ማቀዱ እንዳሳሰበው ለድርጅቱ በላከው ደብዳቤ ላይ ገልጿል።
ኢሰመኮ የምክር ቤቱ የልዩ ስበሰባ አካሄድ የጦርነቱ ተሳታፊዎች የግጭቱ ተዋናይ ወገኖች ቀደም ሲል የተደረገውን ዓለም አቀፍ ምርመራን ውድቅ አድርገው ሌላ የምርመራ ውጤትን እንዲቀበሉ "አደገኛ ሁኔታን ይፈጥራል" በማለት ስጋቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከመነሻው የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የጠራው ልዩ ስብሰባ እንደማይቀበልና በዚህ ስብሰባ ላይ የሚተላለፍ ማንኛውም ውሳኔ በኢትዮጵያ ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ቀደም ብሎ በይፋ ማስታወቁ ይታወሳል።
ስብሰባው የትግራይ አማፂያንን የሚያበረታታ ነው ሲሉ በተመድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ማኅሌት ኃይሉ ለድርጅቱ የመንግሥታቸውን አቋም በገለጹበት ጊዜ እንዳሉት፣ የተጠራው ልዩ ስብሰባ የምክር ቤቱን የአሠራር ደንብ ያልተከተለና የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትን ከተቋቋመለት ዓላማ ውጭ ለፖለቲካዊ ፍላጎቶች መጠቀሚያ የሚያደርግ ነው ብለውታል።
"በምክር ቤቱ በልዩ ስብሰባ ውሳኔ እንዲሰጥበት ተብሎ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ጋር በቀጥታ የሚጣረስ በመሆኑ ስብሰባውም ሆነ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡ እንዲሰረዝ" ጠይቀው ነበር።
ይህ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም የሚጠይቀው የውሳኔ ሐሳብ በአውሮፓ ሕብረት አማካይነት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነበር የቀረበው።
ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን በትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ አካሂደው ውጤቱን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።














