በኢትዮጵያ የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር ዓለም አቀፍ አካል እንዲቋቋም ሁለት የሰብአዊ መብት ተቋማት ጠየቁ

ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በምዕራብ ትግራይ በትግራይ ተወላጆች ላይ በቅርቡ አዲስ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን እና ይህንን የሚመረምር ዓለም አቀፍ አካል እንዲቋቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዋች በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠየቁ።

ሁለቱ የመብት ተቋማት በጋራ ባወጡት ሪፖርት ላይ፣ የአማራ ክልል ኃይሎች በምዕራብ ትግራይ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የተለያዩ ከባድ የመብት ጥሰቶች በአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች እየፈጸሙ ነው ሲሉም ከስሰዋል።

ይህ ሐሙስ ከሰዓት የወጣው ሪፖርት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ሊያካሂደው ካሰበው ልዩ ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ልዩ ስብሰባ ፖለቲካዊ አላማን ያነገበ ነው በማለት አጥብቆ የተቃወመው ሲሆን ሌሎች አገራትም ልዩ ስብሰባውን እንዲቃወሙት ጥሪ አቅርቧል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዋች ያወጡት አዲስ ሪፖርት ትኩረት ያደረገው በምዕራብ ትግራይ ውስጥ ይፈፀማሉ ባሏቸው ከባድ የመብት ጥሰቶችና ግፎች ላይ ነው።

"በምዕራብ ትግራይ በርካታ አካባቢዎች በአማራ ክልል ኃይሎች በትግራይ ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ አዲስ የተቀሰቀሰው ጥቃት አሳሳቢ ነው" ያሉት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የቀውስ ጊዜ ምላሽ ኃላፊ ጆአኒ ማሪነር ናቸው።

"ተጨማሪ ጭፍጨፋዎችን ለማስቆም አስቸኳይ ዓለም አቀፍ እርምጃ ካልተወሰደ፣ በተለይ በእስር ላይ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ከባድ አደጋ ላይ ይወድቃሉ" ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ ከጀመረበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ የአማራና የትግራይ ክልሎች ይገባኛል በሚሉት ሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ የጅምላ ግድያዎች፣ የከባድ መሳሪያ ድብደባዎች እና የትግራይ ተወላጆች ላይ በከፍተኛ ቁጥር መፈናቀሎች ማጋጠሙን ሪፖርቱ ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች ከምዕራብ ትግራይ መፈናቀላቸውን እና በቅርብ ጊዜም ከ10 ሺህ በላይ የትግራይ ተወላጆች መፈናቀላቸውን አመልክቷል። ጨምሮም በአካባቢው ባለ የፀጥታ ስጋት ምክንያት ለእርዳታ ድርጅቶች አመቺ አይደለም ብሏል።

አምነስቲ እና ሂውማን ራይትስ ዋች ላወጡት ሪፖርት በፈረንጆቹ ኅዳርና ታኅሣሥ ወራት 31 ሰዎችን ከመካከላቸውም 25ቱ በአደባይ፣ በሁመራ እና በራውያን ከተፈጸሙ በደሎች የተረፉ እማኞች እንዲሁም የታሰሩና ከአካባቢው የተባረሩ ሰዎች ዘመዶችን በስልክ ማነጋገራቸውን ገልጸዋል።

ሪፖርቱ ጨምሮም ካለፈው ኅዳር ወር ጀምሮ የአማራ ክልል ፖሊስና ሚሊሻ እንዲሁም ፋኖ የተባለው ቡድን በተጠቀሱት ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን በመክበብ ቤተሰቦችን ለያይተው ከ15 ዓመት በላይ የሆኑትን፣ ወንዶችንና ሴቶችን በቁጥጥር ስር አውለዋል ብሏል።

እንዲሁም "ሴቶችንና ታዳጊ ልጆችን፣ የታመሙና በእድሜ የገፉትን ሰዎች ከአካባቢው እንዲወጡ አድርገዋል" በማለት፣ ከእነዚህም መካከል የተወሰኑት ወደ ማዕከላዊ ትግራይ የገቡ ሲሆን ሌሎቹ ግን የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ገልጿል።

የሰብአዊ መብት ድርጅቶቹ ለዚህም የጥቃቱ ሰላባዎችን፣ እማኞችንና የቤተሰቦችን ምስክርነት እንዲሁም የሳተላይት ምስሎችን በመመልከት በአካባቢዎቹ የጎላ የመኪኖች እና የሰዎች እንቅስቃሴ እንደነበር እንደማስረጃ አቅርበዋል።

አምነስቲ እና ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጡት ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም፣ ከሕግ ውጪ የተያዙ ሰዎች እንዲለቀቁ እና የእርዳታ ድርጅቶች ወደ አካባቢው እንዲገቡ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ በደሎችን የሚመረምር ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አካል በአስቸኳይ እንዲያቋቁም ጠይቋል።

የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በሰብአዊ መብት ድርጅቶቹ የቀረበውን ክስ በተመለከተ ለሮይተርስ በሰጡት ምላሽ "መሰረ ተቢስ እና በማስረጃ ያልተደገፈ" ሲሉ ያጣጣሉት ሲሆን፣ የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ደግሞ ለተፈጸሙ የትኛውም አይነት ጥቃቶች የትግራይ ኃይሎች ተጠያቂ ናቸው ብለዋል።

አርብ በአውሮፓ ሕብረት ጠያቂነት ይካሄዳል የተባለው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ፣ በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚያወግዝ የውሳኔ ሐሳብ ያቀርባል ተብሏል።

ይህ የውሳኔ ሐሳብ በምክር ቤቱ ተቀባይነትን ካገኘ የመብት ተቋማቱ እንደጠየቁት ኢትዮጵያ ውስጥ ተጨማሪ ምርመራ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽን እንዲቋቋም ይጠየቃል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ስብሰባውንና የቀረበውን ሃሳብ የተቃወመው ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አማካይነት የተካሄደውን ምርመራ መሠረት በማድረግ መንግሥት እርምጃ እየወሰደ ባለበት ጊዜ ልዩ ስብሰባ መጥራት "ፖለቲካዊ ፍላጎት" አለው ሲል ተቃውሟል።

ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን በትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ አካሂደው ውጤቱን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።