በኢትዮጵያ ትግራይ እና ሱዳን ድንበር ወንዝ ላይ በርካታ አስከሬኖች ተገኙ

የተከዜ ወንዝ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በጥይት የቆሰሉና እጃቸው ከኋላ የተጠፈሩ አስከሬኖች ኢትዮጵያ በትግራይ በኩል በምትዋሰንበት ተከዜ ወንዝ ላይ መገኘቱን አንድ ዶክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶክተር ቴዎድሮስ ተፈራና ሌሎች የአይን እማኞች እንደሚናገሩት ሟቾቹ ከትግራይ ክልል እንደመጡ ነው።

የሱዳን ፖሊስም እንዲሁም 28 አስከሬኖችን ማግኘቱ ተዘግቧል ።

ዶክተር ቴዎድሮስ ለቢቢሲ እንደገለፁት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች የተበራከተውን የብሔር ግጭት በመፍራት በሁመራ በኩል ወንዙን ለመሻገር እየሞከሩ ነው።

በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት በሐምዴት የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚሰራው ዶክተር ቴዎድሮስ እንዳለው የሴቶችና ወንዶች አስከሬን ቢያንስ ለሰባት ቀናት ውስጥ በውሃ ውስጥ እንደነበሩ ነው።

ውጊያውን አምልጦ ወደ ሱዳን የሸሸው ዶክተር ለቢቢሲ እንደገለፀው ባለፈው ሳምንት 10 ያህል አስከሬኖች ከተከዜ ተጎትተው እንደወጡና መቅበሩን ነው።

ዶክተሩ አክሎም "አስከሬኖቹ የበሰበሱና ማንነታቸው ለመለየት የሚያስቸግር ቢሆንም አንደኛው ግለሰብ ግን የትግርኛ ስም የሆነው 'ግደይ' የሚል ንቅሳት እንዳለው ነው።

በርካቶችም በአማራ ክልል ሚሊሻዎች የጅምላ እስር እየተከናወነ መሆኑንንእመ ወደ ስደተኞች መጠለያ ካምፕ የመጡ አዲስ ስደተኞች ተናግረዋል።

እነዚህ ክሶች በቢቢሲ አልተረጋገጡም።

በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተከዜ ወይም ሰቲት ተብሎ በሚጠራው ወንዝ ላይ 50 የሚሆኑ አስከሬኖች እየተንሳፈፉ የተገኙ ሲሆን አንዳንዶቹም በጥይት የቆሰሉ እንዲሁም እጆቻቸው የታሰሩ መሆናቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

የተከዜ ወንዝ ለዘጠኝ ወራትም ያህል የኢትዮጵያ ወታደሮችና እና አጋር ተዋጊዎች ከህወሓት ኃይሎች ጋር ውጊያ ባደረጉባት ትግራይ ክልል የሚፈስ ነው።

የአሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል አንድ የሱዳን ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገባው ምናልባትም ከትግራይ ጦርነት የሸሹ ናቸው የተባሉ 50 ያህል አስከሬኖችን የከሰላ ግዛት ባለስልጣናት ማግኘታቸውን ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በእነዚህ አስከሬኖች መገኘት ላይ ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም። ነገር ግን መንግሥታዊው የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገጽ ሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ስለዚሁ ጉዳይ አስፍሯል።

"የህወሓት ፕሮፓጋንዳ አራጋቢዎች የሐሰት ምስሎችን እና ስዕላዊ ቅንብሮችን በመጠቀም ሐሰተኛውን 'የሁመራ ጭፍጨፋ' ዘመቻ እንደገና በማነሳሳት ላይ ይገኛሉ" ብሏል።

ሁመራ የተከዜ ወንዝ የሚያልፍባት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የምትገኝ አካባቢ ናት።

ካርታ

ምዕራብ ትግራይ ተብሎ የሚጠራው ስፍራ ጦርነቱን ተከትሎ የአማራ ክልል ቀደም ሲል የተወሰዱብኝ አካባቢዎች ናቸው በማለት ይገባኛል በሚል የተቆጣጠረው ሲሆን በርካታ መፈናቀሎችና ግድያዎችም ተፈጽመዋል የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

የካቲት ላይ ኒውዮርክ ታይምስ ከአሜሪካ መንግሥት አገኘሁት ያለውን የውስጥ ሪፖርት ተመርኩዞ በሰራው ዘገባ "በምዕራብ ትግራይ የአማራ ሚሊሻዎች ስልታዊ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እያደረጉ ነው እንዲሁም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያሉበት እንደማይታወቅና በርካታ ቤቶች ሆን ተብሎ ወድመዋል" ብሎ ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ትግራይ ውስጥ የዘር ማፅዳት ወንጀል እየተፈፀመ ነው ብለው ከማውገዝ በተጨማሪ "ሙሉ ተጠያቂነት እንዲኖር" ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል 'የዘር ማጽዳት' ድርጊት ተፈጽሟል የሚለው ክስ በፍጹም "ተጨባጭ ያልሆነና ሐሰተኛ" ነው ሲል የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውድቅ አድርጎታል።

ለዚሁ ክስ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ ምላሽ ሲሰጥ "በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተሰነዘረ ተጨባጭነት የሌለውና ሐሰተኛ ክስ ነው" ብሎታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር በትናንትናው ዕለት በሱዳን ጉብኝታቸው ከትግራይ ጦርነት ሸሽተው በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች ያሉበትን የስደተኞች መጠለያ ጎብኝተዋል።

ኃላፊዋ 90 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች በረሃብ አፋፍ ላይ በሆኑበት የትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ እንዲፈቀድ ግፊት ለማድረግ በዛሬው እለት አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ኤጀንሲ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት የሻከረ ቢሆን ቢኖርም ለትግራይ በሱዳን በኩል ምግብ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን መግለጹን ኤፒ በዘገባው አስነብቧል።

የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ተዘግቷል የተባለውን የትግራይ ክልል ለመድረስ የሚደረገው ድርድር በጣም አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱን የሱዳን የዓለም የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ማሪያን ዋርድ ተናግረዋል።

ምክትል ዳይሬክተሯ ከዚህ ቀደም በሱዳን በኩል 50 ሺህ ቶን ስንዴ ወደ ኢትዮጵያ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

1px transparent line

የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ተዋጊዎች ተገድለዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ወታደሮቹን ከመዲናዋ መቀለ እንዳስወጣ ቢገልፅም ህወሓት በበኩሉ መቀለን በኃይል እንደተቆጣጠረ ተናግሯል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን በኩል ኢትዮጵያ የተኩስ አቁሙን ለማወጅ የወሰነችበት ሁኔታም ተገልጿል።

ከዚህም መካከል አብዛኛዎቹ የህወሓት የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች በመገደላቸውና በመታሰራቸው እንዲሁም የቀሩትን ጥቂት የህወሓት አመራሮች ለመያዝ ሲባል ጦርነቱን መቀጠል አስፈላጊ ባለመሆኑ ነው ተብሏል።

በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች የግብርና ወቅታቸውን እንዳይስተጓጎል፣ የረድዔት ድርጅቶች የበርካቶችን ህይወት እንዲያድኑ እድል ለመስጠት እንዲሁም የግጭቱ የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የትግራይ ሕዝብ ሰላም የሚያስፈልገው በመሆኑ እና ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ከጠቀሷቸው ምክንያቶች ናቸው።

ህወሓት በስምምነት ላይ የተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚቀበል ያስታወቀ ሲሆን ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።

ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እንዲሁም ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል።