ትግራይ፡ ኢትዮጵያ በአንቶኒ ብሊንከን የተሰነዘረውን 'የዘር ማጽዳት' ክስ አጥብቃ ተቃወመች

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

የፎቶው ባለመብት, MoFA-ETHIOPIA

የምስሉ መግለጫ, ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን የሰነዘሩት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል 'የዘር ማጽዳት' ድርጊት ተፈጽሟል የሚለው ክስ በፍጹም "ተጨባጭ ያልሆነና ሐሰተኛ" ነው ሲል የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውድቅ አደረገው።

ብሊንከን ባለፈው ረቡዕ ለአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በሰጡት ማብራሪያ ወቅት ትግራይ ውስጥ "የዘር ማፅዳት ወንጀል" ተፈጽሟል ያሉ ሲሆን ድርጊቱን ከማውገዝ በተጨማሪ "ሙሉ ተጠያቂነት" እንዲኖር ጥሪ አቅርበው ነበር።

ለዚሁ ክስ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ ምላሽ ሲሰጥ "በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተሰነዘረ ተጨባጭነት የሌለውና ሐሰተኛ ክስ ነው" ብሎታል።

መግለጫው ጨምሮም መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ ያካሄደው ዋነኛው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅትና ከተጠናቀቀ በኋላ ሆን ተብሎ በክልሉ ውስጥ ማንንም ኢላማ ያደረገ "ዘር ማጽዳት" ተብሎ የሚጠቀስ ድርጊት አልተጸመም በማለት ክሱን የኢትዮጵያ መንግሥት አጥብቆ እንደሚቃወመው ገልጿል።

አንቶኒ ብሊንከን በትግራይ ክልል ተከሰተ ስላሏቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ግድያዎች ተአማኒ መረጃዎች እንዳሉ አመልክተው የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን እንዲያስቆም ጠይቀዋል።

በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ሲልም በመስሪያ ቤታቸው በኩል መግለጫ ያወጡ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ አጋሮች ጋር በመሆን ጥልቅ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቋሙን ግልጽ ባደረገበት ጊዜ "ነገሮችን ከሚገባቸው በላይ ማግዘፍ ጉዳዩን በማያስፈልግ ሁኔታ ፖለቲካዊ ከማድረግ ውጪ ፍትሕ ለማስፈን አይጠቅምም" ብሏል።

መግለጫው አክሎም የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎችን በተመለከተ የሚቀርቡ ክሶችን ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቅሶ፤ ለዚህም ነው አጥፊዎችን ለፍርድ ለማቅረብ በቀረቡ ክሶች ዙሪያ አስፈላጊው ምርመራ እንዲደረግ አፋጣኝ እርምጃ የወሰደው ሲል ገልጿል።

ለዚህም እንደማሳያ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተወከሉ መርማሪዎች ወደ ትግራይ ክልል ሄደው ምርመራ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክቷል።

በተጨማሪም መንግሥት ከተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን ትግራይ ክልል ውስጥ ተፈጽመዋል ስለተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለመመርመርና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "ተፈፅመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር መንግሥታቸው እርምጃዎችን መውሰዱን" በመግለጽ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በጋራ ለመስራት በራቸው ክፍት መሆኑን ገልጸው ነበር።

አምነስቲና ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዋች እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ውስጥ የኤርትራ ወታደሮች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያዎችን፣ አስገድዶ የመድፈር ድርጊቶችንና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል በማለት ሪፐፖርቶችን ማውጣታቸው ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኃላፊ ሚሼል ባሽሌት በክልሉ እየተፈፀመ ያለው ጥሰት "የጦር ወንጀልና በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል" ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል መናገራቸው የሚታወስ ነው።

በዚህም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉትንና እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ሪፖርት የተደረጉ የጅምላ ግድያዎችን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ወሲባዊ ጥቃቶችን ለመመርመር እንዲችል ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በትግራይ ክልል ግጭት ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ግድያዎችን በተመለከተ መንግሥት ምርመራ በማድረግ በሚገኘው ውጤት መሠረት ጥፋተኞችን ወደ ፍትህ እንደሚያቀርብና በምርመራው ላይ ተጨማሪ እርዳታ ካስፈለገ መንግሥት የውጭ አካል ሊጋብዝ እንደሚችል ገልጸዋል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት በመፈፀሙ መንግሥት "ሕግ የማስከበር" ወታደራዊ ዘመቻን ማካሄዱን ገልጿል።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን ቢገልጽም በአንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወታደራዊ ግጭቶች እንዳሉና ነዋሪዎች ጉዳትና መፈናቀል እንዳጋጠማቸው በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።