ወደ ትግራይ እርዳታ እንዳይደርስ እያገደ ያለው ምንድን ነው?

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በትግራይ ክልል ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በትግራይ ክልል ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል
    • ፀሐፊ, ፒተር ሙዋይ
    • የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ሪያሊቲ ቼክ

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በትግራይ ክልል ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል።

በትግራይ አማጺያን እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ጦርነት ዳግመኛ ካገረሸ ወዲህ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ለመድረስ ከፍተኛ መሰናክል እየገጠማቸው ነው።

እርዳታ ለማድረስ ፈታኝ የሆነው ለምንድን ነው?

በትግራይ ክልል አፋጣኝ የእርዳታ አቅርቦት ቢያስፈልግም ባለፉት ጥቂት ወራት ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እጅግ ፈታኝ ሆኗል።

መነሻው ለስምንት ወራት የዘለቀው የህወሓት አማጺያን እና የመከላከያ ሠራዊት ጦርነት ነው። ግጭቱ አሁን ላይ ወደ አጎራባች ክልል አፋር ደርሷል።

አፋር ወደ ትግራይ እርዳታ ለማጓጓዝ ሁነኛው መንገድ ስለሆነ፤ የግጭቱ መስፋፋት የእርዳታ ስርጭትን ጥያቄ ውስጥ ከቷል።

ያገረሸው አለመረጋጋት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል። ይህም የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ፍላጎትን ከነበረውም በላይ ጨምሮታል።

እርዳታ የሚሹ ዜጎችን መድረስ የተቻለባቸው የትግራይ አካባቢዎች አሉ። በተለይም አሁን ላይ የተረጋጉና በህወሓት ቁጥጥር ሥር ባሉ ቦታዎች እርዳታ ማድረስ ተችሏል።

የተባበሩት መንግሥታት፤ በዚህ ወቅት ከትግራይ ክልል 75 በመቶ የሚደርሱ እርዳታ የሚሹ ነዋሪዎችን መድረስ እንደሚቻል ግምት አስቀምጧል።

ይህ ቁጥር ያሳለፍነው ግንቦት ላይ 30 በመቶ ብቻ ነበር።

ሆኖም ድርጅቱ "የተከማቸው እርዳታ በፍጥነት እየተመናመነ ነው" ሲል አስጠንቅቋል። እርዳታ ለመስጠት ቀጥተኛና አመቺ መንገድ እንደሌለም ያክላል።

በዚህ ወር መቀለ መድረስ የቻለው አንድ ዙር የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እርዳታ ነው።

54 ምግብ እንዲሁም ሌሎችም አስፈላጊ መሠረታዊ ቁሳቁሶች የጫኑ የጭነት መኪኖች "ለቀናት በመንገድ መዘጋጋት ከተስተጓጎሉ በኋላ" ሐምሌ 12 ትግራይ እንደደረሱ የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።

የእርዳታ መስተጓጎል

ከግንቦት ጀምሮ ማንኛውም ወደ ትግራይ የሚደረግ በረራ ታግዷል። በአየር እርዳታ ማድረስ ስላልተቻለ ሁሉንም የሰብዓዊ እርዳታ በየብስ ከማጓጓዝ ውጪ አማራጭ አልነበረም። ሆኖም ግን የመንገዶች መዘጋጋት ጉዞውን አስተጓጉሏል።

በደቡብ በኩል አማራ ክልል ውስጥ የፌደራል መንግሥቱ ደጋፊዎች የሆኑ ኃይሎች እርዳታ እንዳይጓጓዝ አግደዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታ የጫኑ 29 ከባድ ተሽከርካሪዎች ሰኔ 29 ላይ እንዲመለሱ መደረጉን የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት አድርጓል።

ከሱዳን ወደ ምዕራብ ትግራይ በየብስ እርዳታ ለማስገባትም አልተቻለም። አካባቢው በፌደራል መንግሥቱ ደጋፊ ቡድኖች ቁጥጥር ሥር ነው።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ብቸኛው እርዳታ ማድረስ የሚቻልበት መንገድ በምሥራቅ ትግራይ በኩል ማለትም በአፋር ክልል ነበር።

ሆኖም ግን ግጭቱ ወደ አፋር በመስፋፋቱ በዚህ መንገድ መጓዝ ከባድ ይሆናል።

ባለፈው ሳምንት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከአፋር ወደ ትግራይ የሚደረግ የእርዳታ ጉዞ ማቋረጡን ገልጿል። ይህ ውሳኔ የተላለፈው 10 የድርጅቱ የጭነት መኪኖች ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ነው።

ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ ግልጽ ባይሆንም፤ የመንግሥት ደጋፊ ሚሊሻዎች ጥቃቱን እንደሰነዘሩ የጠቆሙ አሉ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከ200 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ አሁን ላይ በአፋር፣ ሰመራ ከተማ እንደሚገኙና የደኅንነት ሁኔታው ካልተሻሻለ ወደ ትግራይ እንደማይሄዱ አስታውቋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከ200 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ አሁን ላይ በአፋር፣ ሰመራ ከተማ እንደሚገኙና የደኅንነት ሁኔታው ካልተሻሻለ ወደ ትግራይ እንደማይሄዱ አስታውቋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከ200 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ አሁን ላይ በአፋር፣ ሰመራ ከተማ እንደሚገኙና የደኅንነት ሁኔታው ካልተሻሻለ ወደ ትግራይ እንደማይሄዱ አስታውቋል

መንግሥት ምን አለ?

የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኃላፊ አቶ ምትኩ ካሳ፤ ወደ ትግራይ እየተጓጓዘ የነበረውን እርዳታ አፋር ላይ ያስቆመው ህወሓት ነው ይላሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድም የእርዳታ አቅርቦት ወደ መቀለ እንዳይደርስ የትግራይ አማጽያን አፋር መንገድ ላይ ከፍተኛ የመሣሪያ ድብደባ እንደፈጸሙ ተናግረዋል።

ህወሓት ከመንግሥት ስለቀረበበት ውንጀላ አስተያየት አልሰጠም። ሆኖም ግን ከዚህ ቀደም "የእርዳታ ሠራተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ማንኛውንም አይነት ድጋፍ እንሰጣለን" ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ወደ ትግራይ በሚወስደው መንገድ ላይ ያሉት የፍተሻ ጣቢያዎች የእርዳታ ጉዞውን እያጓተቱ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የረድኤት ድርጅቶች ላይ በተደጋጋሚ ጥርጣሬውን አሰምቶ ማንኛውም እርዳታ ከመላኩ በፊት ፍተሻ እንደሚደረግ አስታውቋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን አንዳንድ የእርዳታ ሰጪ ተቋሞች ለህወሓት መሣሪያ እያቀረቡ ነው ብለው ከሰዋል። የትኞቹ ተቋሞች እንደሆኑ ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ሚንስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ ለአማጽያኑ መሣሪያ ሲያቀብሉ መንግሥት የያዛቸው እርዳታ ሰጪዎች አሉ።

"እርዳታን እንደ ሽፋን በመጠቀም ለአማጽያኑ መሣሪያ በማቀበል ግጭቱና ነውጡ እንዲራዘም አድርገዋል" ብለዋል።

የህክምና እርዳታ ሰጪው ዶክተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ በበኩሉ፤ የረድኤት ድርጅቶች ላይ ጥርጣሬ የሚያጭሩ መግለጫዎች እርዳታ ሰጪዎችን ደኅንነት አደጋ ውስጥ እንደሚጥል አሳስቧል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፤ ጦርነቱ ጥቅምት ላይ ከተነሳ ወዲህ 12 እርዳታ ሰጪዎች ተገድለዋል።

በትግራይ ክልል አፋጣኝ የእርዳታ አቅርቦት ቢያስፈልግም ባለፉት ጥቂት ወራት ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እጅግ ፈታኝ ሆኗል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በትግራይ ክልል አፋጣኝ የእርዳታ አቅርቦት ቢያስፈልግም ባለፉት ጥቂት ወራት ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እጅግ ፈታኝ ሆኗል

የግንኙነት መስመር መቋረጥ

መንግሥት ሐምሌ 5 ላይ ለሰብዓዊ እርዳታ በረራዎች ፍቃድ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ሆኖም ጠንካራ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል። ከእነዚህ መካከል ሁሉም በረራዎች አዲስ አበባ አርፈው መፈተሽ አለባቸው የሚለው ይገኝበታል።

እስካሁን ድረስ እነዚህ በረራዎች የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎችን እንጂ የምግብ እርዳታን ያካተቱ አይደሉም።

ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪዎች የገንዘብ እጥረትም ገጥሟቸዋል። የተባበሩት መንግሥታት እስከ ቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ድረስ 435 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልጿል።

በአብዛኛው የትግራይ አካባቢዎች እንደ ስልክና ኢንተርኔት ያሉ መገናኛ መስመሮች ተቋርጠዋል። የኤሌክትሪክ አቅርቦት መቋረጡም ቁልፍ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ላይ ጫና አሳድሯል።

የተባበሩት መንግሥታት "የነዳጅ እና ገንዘብ እጥረት እንዲሁም የመገናኛ መስመሮች መቋረጥ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ እያስተጓጎሉ ነው" ብሏል።