በአፋር ግንባር የተፈጠረው ጦርነት ለምን ይበልጥ አሳሳቢ ሆነ?

ትግራይ

የፎቶው ባለመብት, AFP

    • ፀሐፊ, ቪቪኔ ኑኒስ
    • የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ አፍሪካ

ደም አፋሳሹ የስምንት ወራት የትግራይ ጦርነት ቀስ በቀስ ወደ አፋር ክልል ተስፋፍሯል። ይህም የሆነው ባለፈው ሳምንት ነበር።

አሁን ባለ መረጃ በአፋር በትንሹ 20 ንጹሐን ሰዎች ተገድለዋል። 54 ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ይህ በአፋር የተከሰተው አዲስ ግንባር አድማሱን አስፍቶ ለሌላ የሰብአዊ ቀውስ ምክንያት እንዳይሆን ተሰግቷል።

በርካታ የአካባቢው ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አማጺው ህወሓት በርካታ ንጹሐንን ገድሏል። ይህ ክስ በሌላ ወገን አልተረጋገጠም።

ቢቢሲ በደረሰው ሌላ መረጃ የህወሓትን አማጺ ኃይሎች ዒላማ ያደረጉ የአየር ጥቃቶች ባለፉት ቀናት በአፋር ምድር መደረጋቸውን ነው።

ትግራይን በሚያዋስነው አፋር የኢትዮጵያ መከላከያ እና አጋሮቹ ህወሓትን እየተፋለሙት ይገኛሉ።

የአፋር ክልል ቃል አቀባይ እንደተናገሩት የትግራይ አማጺዎች በአፋር ሦስት አካባቢዎችን ተቆጣጥረዋል።

በአፋር ጉዳይ ላይ የመብት ተቆርቋሪዎች በክልሉ ከፍተኛ የምግብ፣ የመጠጥና የጊዜያዊ መጠለያ ችግር አጋጥሟል ሲሉ ድምጻቸውን አስተጋብተዋል።

ህወሓት በፌዴራል መከላከያ ሠራዊት ተገፍቶ እስኪወገድ ድረስ የትግራይ ክልልን ያስተዳድር ነበር።

አሁን ህወሓት በማዕከላዊው መንግሥት አሸባሪ ቡድን ተብሏል። አማጺዎቹ ግን እኛ ሕጋዊ የክልሉ አስተዳዳሪ ነን ይላሉ።

በአፋር ስለተደረገው ጦርነት እስከአሁን የምናውቃቸው

ከአፋር የደረሱን በርካታ ምንጮች እንደሚሉት የህወሓት አማጺ ኃይሎች በአፋር ክልል በርካታ ንጹሐንን ገድለዋል። ንብረቶችንም ዘርፈዋል። ቤቶችን በእሳት አቃጥለዋል። ይህም በያሎ እና በአውራ የተከሰተ ነው።

ያሎ ከሚባለው የአፋር አካባቢ ሸሽቶ ያመለጠ አንድ ነዋሪ እንደተናገረው ሰዎች የተገደሉት የቀብር ሥነ ሥርዓት እየታደሙ በነበረበት ሰዓት ነው።

በማኅበራዊ ትስስር መድረክ እየተጋራ የሚገኝ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ይህንኑ የሚያጠናክር ነው።

አንድ የአፋር ነዋሪ አጠገቡ የአማርኛ አስተርጓሚ እየተናገረ የሚከተለውን ሲል በተንቀሳቃሽ ምሥሉ ላይ ይታያል፡- "ለ20 ሟቾች መቃብር በመቆፈር ላይ ነበርን። እየተጠጉን ሲመጡ ይህን ጨርቅ ከፍ አድርጌ አሳየኋቸው፤ ንጹሐን ነዋሪዎች እንደሆንን እንዲረዱ ነበር። ነገር ግን ከመሀላቸው አንዱ ተኩስ ከፈተብን።"

ቢቢሲ ይህን ክስተት ከሌላ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

የህወሓት ቃል አቀባይ በበኩሉ "እኛ ከአፋር ሕዝብ ጋር ጦርነት ላይ አይደለንም፣ ከኢትዮጵያ መሪዎች እንጂ" የሚል መልዕክት ያለው ጽሑፍ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ጽፈዋል።

ካርታ

አፋር ለምን የአማጺዎቹ የውጊያ ግንባር እንድትሆን ተመረጠች?

ጦርነቱ ከትግራይ ሲወጣ አፋር የመጀመርያው አይደለችም። ጦርነቶች በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ያውቃል።

የአማራ ኃይሎች በጦርነቱ መጀመሪያ የትግራይ ግዛት ናቸው የሚባሉ አካባቢዎች ተቆጣጥረዋል። የአማራ ኃይሎች እነዚህ አካባቢዎች የኛ ናቸው ይላሉ።

አንዳንድ የፖለቲካ አዋቂዎች ጦርነቱ ወደ አፋር መግባቱ ግጭቱ አገር አቀፍ መልክ ሊሰጠው እንደሚችል ስጋት አላቸው።

ማዕከላቸውን ናይሮቢ ያደረጉትና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ራሺድ አብዲ ክስተቱ "ቸል የሚባል አይደለም፤ አሳሳቢም ነው" ይላሉ።

"አፋር ቁልፍ የሚባሉ ጎዳናዎች ያሉበት አካባቢ ነው። አንዱ ትግራይን ከተቀረው ኢትዮጵያ የሚያገናኝ ነው። ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያን ከጂቡቲ የሚያገናኝ ነው" ይላሉ።

ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት አገር ናት። 95 ከመቶ የሚሆነው የገቢና ወጪ ዕቃ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች የሚመላለሱበት አውራ ጎዳና በዚህ በአፋር በኩል ነው የሚገኘው።

ራሺድ እንደሚሉት "ህወሓት ይህን የምልልስ ኮሪደር መቆጣጠር ከቻለ በተቀረው ኢትዮጵያ ላይ ብዙ መስተጓጎል ሊፈጠር ይችላል።"

በኢንተርሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የኢትዮጵያ ጉዳይ ተንታኝ ዊል ዴቪሰን በበኩላቸው የኢትዮጵያን ዋንኛ ወጪ ገቢ መስመርን መቆጣጠር የህወሓት የአፋር ጥቃት ዋንኛ ግብና ስትራቴጂ እንደሆነ ይገምታሉ።

"ዋናው ግባቸው የነበረው በቅርብ ጊዜ ባገኙት ድል ላይ ተጨማሪ ድል ማስመዝገብና ለአዲስ ጥቃት በአፋር የተከማቸውን የፌዴራልና የክልል ወታደራዊ ኃይሎችን ማጥቃት ነው። ነገር ግን ሌላው ዓላማቸው የጂቡቲ መንገድን መቁረጥ ነው። ቢያንስ ቢያንስ ያን የማድረግ አቅም እንዳላቸው ማሳየት ነው ግባቸው" ይላሉ ዴቪሰን።

የሰብዓዊ ሁኔታው ምን ይመስላል?

እርዳታ ወደ ትግራይ ማድረስ ባለፉት ወራት ውስጥ እጅግ ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል። ይህ የሆነው ሕዝቡ ጊዜ በማይሰጥ ችግር ውስጥ ባለበት ሁኔታ ነው።

ሐሙስ ዕለት የረሃብ ደረጃዎችን የሚያወጣው ዓለም አቀፉ አይፒኤስ፣ 400ሺህ ሰዎች በትግራይ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ለረሃብ ተጋልጠዋል ሲል አስታውቋል።

አይፒኤስ ጨምሮ እንዳለው 4 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር አስቸኳይ የምግብ እርዳታን የሚሻ ነው።

ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም እርዳታ ማቅረቡን አቋርጧል። ይህም የሆነው በአፋር መስመር እሑድ ዕለት 10 ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ መኪናዎቹ ጥቃት ስለተከፈተባቸው ነው።

መኪናዎቹ ጥቃት ሲደርስባቸው ከአፋር ከተማ ሰመራ በ120 ኪሎ ሜትር ርቀው ነበር።

የዓለም ምግብ ድርጅት እንዳለው አሁንም 200 የሚሆኑ ምግብና ሌሎች ሰብአዊ እርዳታዎችን የጫኑ ተሸከርካሪዎች በከተማው ውስጥ ቆመው ይገኛሉ። ለደኅንነታቸው ዋስትና እስካልተሰጠ ድረስ ወደ ትግራይ እንዲንቀሳቀሱ አይደረግም ብለዋል።

እስከአሁን በነዚህ የሰብአዊ እርዳታ አድራሽ ተሸከርካሪዎች ላይ ማን ጥቃት እንደሰነዘረ የታወቀ ነገር የለም። ሆኖም ሰሐን የጥናት ቡድን ውስጥ የሚሰሩት ማት ብራይደን እንደሚገምቱት "መንግሥትን የሚደግፉ የአካባቢው ሚሊሻዎች ናቸው ተጠያቂዎቹ" ይላሉ።

ይህ በእንዲህ እያለ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አንዳንድ ንግግሮቻቸው አሳሳቢ መልክን እየያዙ መጥተዋል።

በሳምንቱ መጨረሻ ዐቢይ ያወጡት መግለጫ ህወሓትን 'ካንሰር' በሚል የገለጸ ነበር። ትናንት ሐሙስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአዲስ አበባ ለመከላከያ ኃይል ድጋፋቸውን ለመስጠት አደባባይ ወጥተዋል። አንዳንዶች ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቃል አንግበው ታይተዋል።

"አንድ የሆነ ተአምራዊ ለውጥ በቅርብ ካልተፈጠረ፣ ኢትዮጵያ ወደ መበታተን እየተጓዘች ይመስለኛል" ይላሉ ብራይደን። ሲቀጥሉም፣ "ከአምስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአካባቢው በጣም ግዙፍና ኃያል ሆኖ ይታይ ነበር፤ አሁን ትግራይን እንኳ መታደግ አለመቻሉ ነገሮች እንዴት እየተበላሹ እንደመጡ ማሳያ ነው" ይላሉ።