በትግራይ የሸቀጥ እና የምግብ ዋጋ በከፍተኛ መጠን መጨመሩ ተገለጸ

ትግራይ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር (አይሲአርሲ) በትግራይ የመሠረታዊ ሸቀጦች እና የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አስታወቀ።

ቀይ መስቀል ዛሬ ባወጣው መግለጫ በተለይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የምግብ ዋጋ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን አስታውቋል።

በመላው ትግራይ ባንኮች ዝግ በመሆናቸው ሰዎች መሠረታዊ ግብይቶችን ለመፈጸም የጥሬ ገንዘብ እጥረት አጋጥሟቸዋል ብሏል።

"ፋብሪካዎች ተጎድተው ቀርተዋል ወይም እንዲወድሙ ተደርገዋል። በርካታ የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል። በዚህም በርካቶች ከሥራ ውጪ ሆነዋል። ይህም የጤና አገልግሎትን ጨምሮ መሠረታዊ ቁሶች እና አገልግሎቶች እንደማይገኙ አድርጓል" ብሏል ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር።

አብዛኛው የጤና እና የመጠጥ ውሃ ማጣሪያ ተቋማት ኃይል የሚያገኙት ከጄነሬተር በሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል መሆኑን በመጥቀስ፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ቋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የነዳጅ አቅርቦት አለመኖሩን ቀይ መስቀል ገልጿል።

ቀይ መስቀል በዛሬው መግለጫው በሰሜን ኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ የገለጸ ሲሆን፤ በትግራይ እና በአማራ ክልል ለሚገኙ አምስት ሆስፒታሎች የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን አስታውቋል።

ለሰቆጣ እና ላሊበላ አጠቃላይ ሆስፒታሎች፣ ለጎንደር እና አይደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች እንዲሁም ለአይከል የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል። ድጋፉ 250 በጽኑ የተጎዱ ወይም 900 መካከለኛ ጉዳት ያጋጠማቸውን ሰዎች መርዳት ያስችላል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የመቀለ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮቪድ-19 ክፍልን ለመደገፍ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን እና በሸራሮ የሚገኘውን ሆስፒታል መልሶ ለማቋቋም ሥራ መጀመሩን ገልጿል።

ለአይደር፣ ሁመራ፣ ዳንሻ እና ማይካድራ ሆስፒታሎች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሆነም አስታውቋል።

በክልሉ የስልክ እና የኢንተርኔት መስመር መቋረጥን ተከትሎ፤ የቀይ መስቀል ማኅበር ግጭቱን ተከትሎ ከቤተሰብ አባላታቸው ተቆራርጠው የሚገኙ ሰዎችን ለማገናኘት የስልክ ጥሪ እና የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል። ከዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መካከል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሚገኙበት ማኅበሩ አስታውቋል።

ከኢትየጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመተባበር ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ተጋላጭ ለሆነው የማኅብረሰብ ክፍል በውሃ ቦቴ ተሸካሚ ተሽከርካሪዎች ውሃ እያቀረበ እንደሆነ ገልጿል።

በዚህ የክረምት ወቅት ውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ እና የንጹህ ውሃ አቅርቦትን ለማረጋገጥ የኬሚካል ድጋፍ ማድረግ መቀጠሉንም አክሏል።