ክልሎች ልዩ ኃይሎቻቸውን ወደ ግጭቱ አካባቢ እየላኩ መሆኑ ተነገረ

የመከላከያ ሰራዊት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የትግራይ ኃይሎች የኮረም እና አላማጣ ከተሞች መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የተለያዩ የአገሪቱ ክልልሎች ወደ አካባቢው ሠራዊት እያንቀሳቀሱ ነው።

የአማራ ክልል በህወሓት ወረራ ተፈፅሞብኛል ያለ ሲሆን ክልሉም ወረራውን "ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግሯል" ብሏል።

የአማራ ክልል ባለስልጣናት በትግራይ ኃይሎች ላይ አዲስ ጥቃት እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

የትግራይ ኃይሎች ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ቁልፍ የሚባሉ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።

የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው እንዳሉት ትዕግስታቸው እንደተሟጠጠና "ከዛሬ ጀምሮ በግልፅ ጥቃት እንጀምራለን" ብለዋል።

ከክልሉ በጡረታ የተሰናበቱ የፀጥታ ኃይሎች ጥሪ የተደረገ ሲሆን ፈቃደኛ የሆኑ ሚሊሻዎችም እንዲሰባሰቡ ክልሉ ጠይቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሚያ፣ የሲዳማ እና የደቡብ ክልሎች የልዩ ኃይል አባሎቻቸውን ወደ ግጭቱ አካባቢ መላካቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ይህም ረቡዕ እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ሌፍተናንት ጄነራል ባጫ ደበሌ ሕዝቡ ለሠራዊቱ እና ለመንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቀረባቸውን ተከትሎ ነው።

የትግራይ ኃይሎች በጦርነቱ ወቅት ወደተያዙ ግዛቶች የገፉ ሲሆን ደቡባዊ ትግራይ የሚባሉትን ኮረምና አላማጣን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ መቆጣጠራቸውንም አሳውቀዋል።

የትግራይ ኃይሎች ምዕራብና ደቡብ ትግራይ ናቸው የሚሏቸውን ግዛቶች በአማራ ክልል በኩል ቀደም ሲል የተወሰዱብኝ አካባቢዎች ናቸው በማለት ግዛቶቹ ይገቡኛል ይላል።

ትግራይ ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰንበት አካባቢ ግጭቶች እንዳሉ እየተነገ ሲሆን ከክልሎቹ ኃይሎችና ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በተጨማሪ የኦሮሚያ፣ የሲዳማ እና የደቡብ ክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ስፍራው እያመሩ ነው።

የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይል በትናንትናው ዕለት ሽኝት የተደረገለት ሲሆን የደቡብ ክልል ልዩ ኃይልም በዛሬው ወደ ጦርነት ግንባር መድረሱን ኢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።

በአሁኑ ወቅት የጦርነት አታሜ በየቦታው በሚጎሰምበት ወቅት ወደ አዲስ እና እንዲያውም ይበልጥ ወደ ደም አፋሳሽ የግጭት ምዕራፍ ሊያመራ ይችላልም ተብሏል።

በዚህም አዲስ ውጊያ ሊቀሰቀስ ይችላል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን ከሳምንታት በፊት በመንግሥት በኩል የታወጀው የተናጠል የተኩስ አቁም ማብቂያ ሊሆን ይችላል።

በአሁኑ ወቅት ያለውን የውጊያ መፋፋምም አስመልክቶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ለአላስፈላጊ ስቃይ እና ሞት የሚዳርግ ነው በማለት ያላቸውን ስጋት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

አምባሳደሯ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት በድርድር የተመሰረተ የተኩስ አቁም እና ፖለቲካዊ ውይይት ሊስማሙ ይገባል ብለዋል።