የትግራይ ኃይሎች አላማጣና ኮረምን መቆጣጠራቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, YASUYOSHI CHIBA
የትግራይ ኃይሎች በደቡባዊ ትግራይ የምትገኘውን ኮረም ከተማን መቆጣጠራቸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።
ክልሉ ከጦርነቱ በፊት የነበረ ግዛቶችን በሙሉ ለማስመለስ እየተካሄደ ነው የተባለውም ጦርነት ወደ ደቡብ ክፍል መቀጠሉንም ሮይተርስ በዘገባው አስነብቧል።
ሮይተርስ የህወሓት ቃለ አቀባይ ጌታቸው ረዳን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የትግራይ ኃይሎች ከመቀለ በስተደቡብ በኩል 170 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ኮረም ከተማ መቆጣጠራቸውን ነው።
ሰኞ ዕለት አመሻሽ ላይ የወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው በደቡባዊ ትግራይ ዋነኛዋ ከተማ የሆነችውና ከኮረም 20 ኪሎሜትር ርቀት የምትገኘውን አላማጣንም መቆጣጠራቸው እየተነገረ ነው።
ሁለት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአላማጣ ነዋሪዎች የትግራይ ኃይሎች ከትናንት ምሽት አምስት ሰዓት ጀምሮ የአላማጣ ከተማን መቆጣጠራቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የዓይን እማኞቹ እንደሚሉት ከከተማ ወጣ ብሎ በሶስት የገጠር መንደሮችም ከፍተኛ የሆነ ውጊያ መስማታቸውን አስረድተዋል።
ከአይን እማኞቹ በተጨማሪ የትግራይ ኃይል ተዋጊዎችም ኮረምና አላማጣ ከተሞችን እንደተቆጣጠሩ ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት በአላማጣ ከተማ የስልክ አገልግሎት የሚሰራ ሲሆን፤ በከተማዋም መረጋጋት እየታየ እንደሆነና በርካታዎችም በጎዳናዎች ወጥተው ደስታቸውን እየገለፁ እንደሆነ አኚሁ እማኞቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መንግሥት እነዚህ ከተሞች በትግራይ ኃይሎች ስር ቁጥጥር ስለመሆናቸው የሰጠው ይፋዊ መግለጫ የለም።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ከሮይተርስ የኮረም ከተማ በማን ቁጥጥር ስር ነው ያለችው ተብሎ የቀረበላቸውን ጥያቄ ቀጥታ ባይመልሱም "የተኩስ አቁም አውጀናል" የሚል የጽሁፍ መልዕከት ልከዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮቹን ከመቀለ እንዳስወጣና የተናጠል ተኩስ አቁም እንዳወጀ ይታወሳል። በወቅቱም ህወሓት የተኩስ አቁሙን "ቀልድ ነው" ብሎ ነበር።
ሮይተርስ የኮረምን በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋል በግል ባያረጋግጥም በአዲስ አበባ የሚገኙና የኮረም የቀድሞ ነዋሪ ከሆኑ ሰው ውጊያ እንደነበር ሰምቷል።
በአሁኑ ወቅት ኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት ቢቋረጥም የእኚህ የቀድሞ ነዋሪ የቤተሰብ አባል የሆኑ ግለሰብ ውጊያውን ሸሽተው ስልክ ወዳለበት ቦታ ደርሰው ነግረውኛል ብለዋል።
በትግራይ ክልል ጦርነቱ የተነሳው በማዕከላዊ መንግሥትና በክልሉ አስተዳዳሪ ህወሓት መካከል ከስምንት ወራት በፊት ነበር።
የማዕከላዊ መንግሥቱ ከሦስት ሳምንታት በኋላ መቀለን መቆጣጠሩን ተከትሎ ድል መቀዳጀቱን በማወጅ ውጊያው ቆሟል ብሎ ነበር። ህወሓት በበኩሉ ውጊያውን እንደቀጠለ በተደጋጋሚ ሲናገር ነበር።
ህወሓት የክልሉን መዲናን ጨምሮ በርካታ የክልሉ ግዛቶችን ቢቆጣጠርም በምዕራብና በደቡብ በኩል ያሉ ግዛቶች በአማራ ክልል ኃይሎች በመያዛቸው ጦርነቱ መፋፋሙ እየተነገረ ነው።
ህወሃትና የአማራ ክልል ከሰሞኑ ምን አሉ?
የህወሓት ቃለ አቀባይ ጌታቸው እንደሚናገሩት የትግራይ ክልል ከጦርነቱ በፊት የነበራት ወሰን እንዲከበርና ሰዎችና ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ የትራንስፖርት መንገዶች ክፍት እንዲሆኑ በማለት መናገራቸውን ሮይተርስ አስነብቧል።
ከሰሞኑ ህወሓት ምዕራብ ትግራይ የሚላቸውን ግዛቶች በተመለከተ የአማራ ክልል ቀደም ሲል የተወሰዱብኝ አካባቢዎች ናቸው በማለት የሚነሳው ጥያቄ ተቀባይነት የሌላቸውና የአማራ አካባቢዎች ናቸው የሚል ምላሽ ተሰጥቷል።
የአማራ ብልጽግና ጽ/ቤት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ "ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምትና ራያ በራሳቸው መስዋዕትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች መሆናቸውን በድጋሚ እናሳውቃችኋለን" በማለት አስፍሯል።
ህወሓት በበኩሉ የትግራይ መንግሥት በሚል ባወጣው መግለጫ "በትግራይ መሬት እና የትግራይ ክልል ያሉ የአማራ ልዩ ኃይል ይሁኑ ሚሊሻዎችና ታጣቂዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ባስቸኳይ ከትግራይ ለቀው እንዲወጡ" ብሏል።
ይህ ካልሆነ ግን አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም ገልጿል።
የአማራ ክልል መንግሥት "የአማራን ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ደም ለማቃባት በሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሕዝቡን እያነሳሳሱ ይገኛሉ። የአማራ ሚሊሻዎችንም ወደ ትግራይ መሬት እያስጠጉ ነው" ብሏል።
የአማራ ክልል በበኩሉ "ለህልውና የማስከበር ዘመቻ" በሚልም የክልሉ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ በከፈታቸው የባንክ ሂሳብ ቁጥሮችም ነዋሪዎች የተቻላቸውን እንዲረዱ ጥሪ ቀርቧል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አገኘሁ ተሻገር በትናንትናው ዕለት "የህልውና ዘመቻ" ብለው የጠሩትን እንዲደግፉ ለሕዝቡ ጥሪ አቅርበዋል።
"ኢትዮጵያውያንና የአማራ ተወላጆች በአሁኑ ጊዜ ህወሓት በአማራ ሕዝብ ላይ ግልፅ ጦርነት አውጆብን የህልውና ትግል በማካሄድ ላይ እንገኛለን ይህንን ዘመቻ በቻላችሁት ሁሉ እንድትደግፉ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ" በማለት በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
አሜሪካ የውጊያው መቀጠል ያሳደረባት ስጋት
የአሜሪካ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ቃለ አቀባዩ ኔድ ፕራይስ በኩል በሰጠው መግለጫ በምዕራብ ትግራይ የቀጠለው ውጊያ ሪፖርቶች ስጋት እንዳጫሩባቸው ገልጸዋል።
የውጊያዎች መቀጠል በክልሉ ያሉ በረሃብ የተጎዱ ነዋሪዎችን ለመድረስ የሚደረገውን የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያደናቅፈውም ቃለ አቀባዩ ተናግረዋል።
ቃለ አቀባዩ የትግራይ መከላከያ ኃይል፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይልና የአማራ ልዩ ኃይል ለንፁሃኑ ሕዝብ ጥቅምና የአገሪቱን አንድነት ለመጠበቅ በስምምነት ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጠይቀዋል።
ሁሉም የታጠቁ አካላት ንፁሃንን መጠበቅን ጨምሮ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተጣለባቸውን የሰብዓዊ ሕግጋዊ ግዴታ እንዲወጡም አሳስበዋል፥።
በዚህም መግለጫ የሰብዓዊ እርዳታ መብቶችን የጣሱና ሰብዓዊ መብት ጥሰትን የፈፀሙ አካላት ሊጠየቁ ይገባል ተብሏል።
"ከዚህ ቀደም ደጋግመን እንዳልነው የኢትዮጵያን ውስጣዊ ወሰኖችን በኃይል ለመቀየር መሞከር ተቀባይነት የለውም። እንዲህ አይነት ጉዳዮችን የመሰሉ ብሔራዊ ጥያቄዎች ሊፈቱ የሚገቡት በሕዝቡ ነው። ሕዝቡ ብሔራዊ ውይይትና መግባባት ላይ ሲደርስ ነው። በጠመንጃ አፈሙዝ አይደለም" ብለዋል።
በክልሉ ያለው ቀውስና የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት
በትግራይ ክልል የተነሳው ጦርነት 2 ሚሊዮን ነዋሪውን ከክልሉ ሲያፈናቅል 400 ሺህ ደግሞ ለረሃብ ተጋልጠዋል።
በያዝነው ሳምንት ሰኞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለትግራይ ክልል የላካቸው ሰብዓዊ እርዳታ ጭነት መቀለ መግባታቸው ተገልጿል።
በሁለት ሳምንት ውስጥ ለመጀሪያ ጊዜ የደረሰው ይህ እርዳታ በ50 የጭነት መኪኖች የተጓጓዘ ነው። በመቀለ የደረሰው እርዳታ 900 ሜትሪክ ቶን ምግብና አስፈላጊ ቁሳቁስ ቢሆንም በክልሉ ካለው ችግር አንፃር ይህ ቁጥር በእጥፍ ማደግ አለበት ተብሏል።
ከአራት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አስቸኳይ እርዳታ በሚፈልግባት ትግራይ 10 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብና 150 ሺህ ሊትር ነዳጅ በየሳምንቱ መድረስ አለበት በማለት ድርጅቱ አፅንኦት ሰጥቷል።
በትግራይ ያሉ ዋነኛ መንገዶች የተዘጉ ሲሆን ሁለት ድልድዮችም ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
መቀለ በትግራይ ኃይሎች ከተያዘች ጀምሮ መብራት የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ባንክና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።
ህወሓት ማዕከላዊው መንግሥት እርዳታን እያገደ ነው በሚል የሚወቅስ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ መሰረተ ልማቶችን እየገነባሁ ነው ብሏል።
በትግራይ ክልል ከግንቦት 22/2013 ዓ.ም ጀምሮ ምንም አይነት በረራዎች የተቋረጡ ቢሆንም መንግሥት ከሰሞኑ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ለሚፈልጉ ሁሉ ልዩ ፈቃድ እንደሚሰጥና በረራዎችም ከሰኔ 28/2013 ዓ.ም እንደሚጀመሩ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በልዩ ሁኔታ የፈቀደውን የሰብዓዊ እርዳታ በረራ አለመከልከሉንና በአሁኑም ወቅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም መንገደኞችን ወደ ትግራይ ክልል ለማጓጓዝ ሁለት በረራዎች እንዲፈቀዱለት መጠየቁን ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ተዋጊዎች ተገድለዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ወታደሮቹን ከመዲናዋ መቀለ እንዳስወጣ ቢገልፅም ህወሓት በበኩሉ መቀለን በኃይል እንደተቆጣጠረ ተናግሯል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን በኩል ኢትዮጵያ የተኩስ አቁሙን ለማወጅ የወሰነችበት ሁኔታም ከሰሞኑ ተገልጿል።
ከዚህም መካከል አብዛኛዎቹ የህወሓት የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች በመገደላቸውና በመታሰራቸው እንዲሁም የቀሩትን ጥቂት የህወሓት አመራሮች ለመያዝ ሲባል ጦርነቱን መቀጠል አስፈላጊ ባለመሆኑ ነው ተብሏል።
በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች የግብርና ወቅታቸውን እንዳይስተጓጎል፣ የረድዔት ድርጅቶች የበርካቶችን ህይወት እንዲያድኑ እድል ለመስጠት እንዲሁም የግጭቱ የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የትግራይ ሕዝብ ሰላም የሚያስፈልገው በመሆኑ እና ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ከጠቀሷቸው ምክንያቶች ናቸው።
ህወሓት በስምምነት ላይ የተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚቀበል ያስታወቀ ሲሆን ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።
ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እንዲሁም ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል።















