የትግራይ ግጭት፡ ለተኩስ አቁሙ የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎችና የያዙት አንድምታ

የፎቶው ባለመብት, YASUYOSHI CHIBA
በፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ፣ ህወሓት፣ መካከል የነበረው ውዝግብና ፍጥጫ፣ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ወደ ወታደራዊ ግጭት ካመራ በኋላ ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትን ያስከተለ ጦርነት በክልሉ ተካሂዷል።
ምንም እንኳን የኢትጵያ መንግሥት ኃይሎች በሦስት ሳምንት ውስጥ የህወሓት ኃይሎችን ከክልሉ ዋና ከተማ መቀሌና ከሌሎች አካባቢዎች አስወጥተው ዘመቻው መጠናቀቁን ቢገልጹም ግጭቱ ለስምንት ወራት ቀጥሎ ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
ህወሓት ከክልሉ የመሪነት ቦታ ከተወገደ በኋላ በፌደራል መንግሥቱ የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ማዕከላዊው መንግሥት "ሰብዓዊነትን መሰረት ባደረገና ተጨማሪ ጉዳት በማያስከትል መልኩ" የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።
የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ የክረምት ወቅት እየገባ በመሆኑ፣ አርሶ አደሮች የግብርና ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍ ለተረጂዎች ያለችግር እንዲደርስ በክልሉ ላለው ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት የተኩስ አቁም እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ይህንንም ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ ውስጥ የተኩስ አቁም እንዲደረግ መስማማቱን በመግለጽ የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን አስታውቋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በወጣው መግለጫ ላይ እንደተገለጸው በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ግጭት እንዲቆም መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የተኩስ አቁም በተናጠል ማድረጉን ገልጿል።
ማዕከላዊው መንግሥት ያለቅድመ ሁኔታ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ቀደም ሲል በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ ለማስቆም የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሲጠይቁ የነበሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና አገራት እርምጃውን በአወንታዊ መልኩ ተቀብለውታል።
መንግሥት የወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ በይፋ ከተነገረ ከቀናት በኋላ ዕሁድ ሰኔ 27/2013 ዓ.ም ከአማፂያን ቡድኑ በኩል የወጣው መግለጫ የተኩስ አቁምን በመርኅ ደረጃ እንደሚቀበሉት በመግለጽ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበዋል።
የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች ግን የፌደራል መንግሥቱን ጨምሮ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑት ኃይሎች ተቀባይነቱ አጠያያቂ በመሆኑ በክልሉ ውስጥ በጉጉት የሚጠበቀውን ሠላም ማምጣቱን ብዙዎች ይጠራጠራሉ።
ቅድመ ሁኔታዎቹ ምንድን ናቸው?
ከቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ በቀዳሚነት የተቀመጠው "የአማራና ኤርትራ ኃይሎች በወረራ ከያዙት የትግራይ ግዛቶች በመውጣት ከጦርነቱ በፊት ወደነበረው ቦታ እንዲመለሱ" የሚጠይቀው ሐሳብ ከዚህ በፊት ብዙ የተባለለትና የአማራ ክልልም ሆነ የኤርትራ መንግሥት አወንታዊ ምላሽ የሚሰጡት አይመስልም።
የጦርነቱን መጀመር ተከትሎ ትግራይና አማራ ክልል በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙና ለረጅም ጊዜ ከአማራ ክልል ተወስደው ወደ ትግራይ ክልል ተካትተዋል ሲባሉ የቆዩ አካባቢዎችን የአማራ ክልል ኃይሎች ተቆጣጥረውት ቆይተዋል።
የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም እነዚህ አካባቢዎች ካለ ሕጋዊ መሠረት ተወስደው የቆዩ መሆናቸውንና አሁን መመለሳቸውን በመግለጽ የሚለወጥ ነገር የለም በማለት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ከቀናት በፊት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርም በማኅበራዊ መገናኛ መድረክ ላይ የእነዚህ ቦታዎች ጉዳይ "የተዘጋ ፋይል መሆኑን ደግመን ደጋግመን እናረጋግጣለን" ሲሉ ጽፈዋል።
በኤርትራ በኩል ያለውንም በተመለከተ የትኞቹ አካባቢዎች እንደሆነ በግልጽ ባይጠቀስም፣ በድንበር ጦርነቱ ጊዜ ተይዘው የቆዩትና ለኤርትራ ይገባሉ የተባሉት አካባቢዎች ከሆኑ ሌላ ዙር ውዝግብን የሚያስከትል ይሆናል።
ጦርነቱን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት በተለያዩ የሰብዓዊ ጥሰቶችን በመፈፀም የሚከሰሱት የኤርትራ ኃይሎች እግረ መንገዳቸውን ይገቡናል ያሏቸውን የድንበር አካባቢዎች በእጃቸው ማስገባታቸውን የኤርትራ ባለሥልጣንት ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻር ከሁለቱም ወገኖች በኩል በይዞታቸው ውስጥ የገቡትን ቦታዎች በመልቀቅ ንግግር ለማድረግ ፈቃደኝነቱ መኖሩ አጠያያቂ ነው።
"የትግራይ መንግሥት" በሚል የተሰራጨው የተኩስ አቁም ቅድመ ሁኔታ በአብዛኛው የፌደራል መንግሥቱን ሚና የሚተካና የማዕከላዊ መንግሥት ሚና የሆኑ ጉዳዮችን በራሱ እንደሚከውን ያመለክታል።
በዚህም "ትግራይን የሚመለከት የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ከትግራይ መንግሥት ጋር መደረግ አለበት፤ ትግራይን በሚመለከት ከኤርትራ ጋር ያሉ ጉዳዮችም በትግራይ መንግሥት ብቻ የሚፈታ ይሆናል" ይላል።
ከዚህ አንጻር የውጭ ግንኙነቶችን በሚመለከት ሥልጣን ያለው የፌደራል መንግሥቱ የቀረበውን ቅድመ ሁኔታ የሚቀበለው አይሆንም፤ የኤርትራ መንግሥትም ወዳጅ ከሆነው ማዕከላዊው መንግሥት በተቃረነ ሁኔታ ከክልሉ አስተዳደር ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም።
ቅድመ ሁኔታው በትግራይ ክልል ውስጥ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ እንዲሁም መብራት፣ ቴሌኮምዩኒኬሽንስ፣ የባንክ፣ የአየር ትራንስፖርት፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የትራንስፖርት፣ ንግድ የመሳሰሉ አገልግሎት እንዲጀመሩ ጠይቋል።
የፌደራል ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት እንዲከበርና ይህም ለሚደረጉ ማናቸውም ድርድሮች ዋነኛ መሠረት እንዲሆን ከመጠየቁ በተጨማሪ የዚህ ዓመት የክልሉ በጀት እንዲለቀቅለት ጠይቋል።
ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ በመቃወም በትግራይ ክልል ውስጥ የተደረገውን የተናጠል ምርጫ ተከትሎ የፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫውን ውድቅ በማድረግ ከክልሉ መንግሥት ጋር የቀጥታ ግንኙነት እንዳይደረግና በጀትም እንዳይሰጠው መከልከሉ ይታወሳል።
መነጋገሪያ የሆኑ ጉዳዮች
በቅድመ ሁኔታዎቹ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ሐሳቦች በስፋት መነጋጋሪያ እየሆኑ ነው። ከእነዚህም መካከል "ያለ ቅድመ ሁኔታ ዓለም አቀፍ በረራዎች በትግራይ ከሚገኙ አየር ማረፊያዎች በቀጥታ ጉዞ እንዲያደርጉ መፈቀድ" እንዲሁም "የትኛውም የፌደራሉ መንግሥት ወታደራዊና የጸጥታ ኃይል ወደ ክልሉ እንዳይገባና እንዳይንቀሳቀሱ" የሚሉት ዋነኞች ናቸው።
እነዚህና ሌሎች የፌደራል መንግሥቱን የሥልጣን ድርሻ የሚገዳደሩ በቅድመ ሁኔታው ውስጥ የተካተቱት ሐሳቦች በትግራይ በኩል በአንዳንድ ወገኖች ሲነሳ የነበረውን ነጻ አገርነት የመመስረት ፍላጎት በይፋ ለማስታዋወቅ የታለሙ የሚመስሉ ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ ከመስከረም ወዲህ ያለው መንግሥት ሕጋዊ አይደለም ሲል የቆየው ህወሓት፤ አሁንም ይህንኑ በመድገም ሁሉም በፌደራል መንግሥቱ ተቋማት የትግራይ ክልልን በሚመለከት የተላለፉ ውሳኔዎች "ሕጋዊ ስላልሆኑ ተፈጻሚነት የሌላቸው እንዲሆኑ" ጠይቋል።
ይህ ደግሞ በህወሓትና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ለነበረው አለመግባባት ምክንያት ከሆኑት አንዱ የሆነው እውቅና የመንፈግ ሐሳብ የንግግርን በር የሚዘጋ ይመስላል።
ባለሰባት ነጥቡን የተኩስ አቁም ቅድመ ሁኔታውን በተመለከተ ከፌደራል መንግሥቱም ሆነ ከሚመለከታቸው ከሌሎች ኃይሎች በይፋ የተሰጠ ምላሽ ባይኖር፤ ከተነሱት ጉዳዮች አንጻር ከዚህ በፊት የተያዙ አቋሞችን ስንመለከት ሁለቱን ወገኖች የሚያቀራርብ አይመስልም።














