ሻሸመኔ ከተማ ከገጠማት ውድመት ከአንድ ዓመት በኋላ

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ተፈጥሮ በነበረው ተቃውሞ እና ብጥብጥ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ በንብረት እና በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አስከትሎ ማለፉ ይታወሳል።
በተከሰተው ሁከት የበርካቶች ሕይወት አልፏል፣ አካላቸው ጎድሏል። ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት በእሳት ወድሟል፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በሺዎች የሚቆጠሩም ለእስር ተዳርገዋል።
የአርቲስቱን ግድያ ተከትሎ በተከሰተው ነውጥ ከፍተኛ ጉዳት ከተከሰተባቸው ከተሞች መካከል ሻሸመኔ እና ባቱ ከተሞች ተጠቃሽ ናቸው።
ወ/ሮ ሙሉ ንጉሤ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ ሲሆን ቤት ንብረታቸው ከተቃጠለባቸው ዜጎች መካከል አንዷ ናቸው።
ወ/ሮ ሙሉ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ፤ "ንጋት 12 ሰዓት ላይ ግር ብለው መጡ። የነበረኝን ንብረት በሙሉ ለቅመው አውጥተው አቃጠሉ። እኔ አሮጊት ነኝ አትግደሉኝ ብዬ ለመንኳቸው። ከዚያ ጎትተው ወደ ውጪ አወጡኝ። ለብሼ ከወጣሁት ውጪ ልብስ አልነበረኝም። በዚያን ወቅት የተፈጠረውን ነገር ሳስብ እንቅልፍ ይነሳኛል" ይላሉ።

የሻሸመኔ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ ገመዳ ከአንድ ዓመት በፊት የተከሰተው እጅት አስደንጋጭ ነበር ይላሉ።
"ትልልቅ 27 ሆቴሎች፣ ከ818 በላይ የግል መኖሪያ ቤቶች፣ 85 መኪኖች በእሳት ወድመዋል። ከንብረት ውድመት በተጨማሪ በሰዎች አእምሮ ላይ ጥሎ ያለፈው ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይደለም" ብለዋል።
የአትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ንበረት የሆነው ሆቴልን ጨምሮ በሻሸመኔ ከተማ በጥቃቱ ከወደሙት ተቋማት አሁንም ከእነ ጉዳታቸው በእሳት ነበልባል ያጠቆራቸው ሕንጻዎች በስፋት ይታያሉ።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በሻሸመኔ የሞቀ የንግድ እንቅስቃሴ ይስተዋልባታል።
ከተማዋ ከደረሰባት ውድመት ለማገገም ዓመታት ይወስድባታል ተብሎ የነበረ ቢሆንም የከተማዋ እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዋ በፍጥነት እያገገመች እንደሆነ መረዳት ይችላል።
የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አባ ገዳ ቡሹሼ ቡታ የሻሸመኔን የአንድ ዓመት ጉዞ እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ።
"ይህች ከተማ ከዚያ የእሳት ነበልባል ተርፋ ትመለሳለች ብለን አላሰብንም። ነዋሪው በፍርሀትና በስጋት ውስጥ በጥርጥሬ ውስጥ ነበሩ። ሰዉ ከዚያ በኋላ ተግባባቶ መኖር ይቀጥላል ብለን አላሰብንም ነበር። ፈጣሪ ግን ሁሉንም ማድረግ ይችላል። የአገር ሽማግሌዎች የእርቅ ሥራ ሰርተናል። በ10 ዓመታት ውስጥ አታገግምም የተባለችው ከተማ በአንድ ዓመት ውስጥ እያገገመች ነው" ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ እንደሚለው ከሆነ የአርቲስት ሃጫሉ ሙት ዓመት በሚታሰብበት ወቅት የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ከደረሰባቸው ሆቴሎች መካከል ከሁለቱ ውጪ ሁሉም ወደነበሩበት ሁኔታ ተመልሰዋል።
"ከወደሙት ንብረቶች ውስጥ ሁለት ሆቴሎች በግል ችግር ምክንያት አልታደሱም እንጂ የተቀሩት ወደነበሩበት ተመልሰዋል። 21 መኖሪያ ቤቶችን እንደ አዲስ ገንብተናል። 818 የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች ደግሞ መልሰን አድሰናል። አሁን ከተማችን ከዚያ አደጋ አገግማ የሞቀች ከተማ ሆናለች" ብለዋል አቶ ሙስጠፋ።
ምንም እንኳ ሻሸመኔ ከተማ ወደ መረጋጋት ብትመለስም የተከተውን በማሰብ አሁን ተመሳሳይ አደጋ ሊከሰት ይችላል ብለው የሚሰጉ ነዋሪዎች አልጠፉም።
"አሁን የዛሬ ዓመት የሆነው ነገር የተመለከተ ሰው በሰላም ያድራል? መዋሸት አያስፈልግም አሁንም እናስባለን። ስጋትም አለን። ፈጣሪ ደግሞ አለ" ይላሉ የከተማዋ ነዋሪ ወ/ሮ ሙሉ።
ከአርቲስ ሃጫሉ ግድያ በኋላ በኦሮሚያ እና በአዲስ አበባ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ 180 ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ መግለጹ ይታወሳል።
ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ስለመውደሙም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቆ ነበር።
ከሁከቱ ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ የተባሉ ሰዎች ከአንድ ዓመት እስከ 22 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።












