የቀድሞው የአርሰናል አምበል ፓትሪክ ቪዬራ የፓላስ አሠልጣኝ ሆኖ ተሾመ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪዎቹ ክሪስታል ፓላስ የቀድመው የአርሰናል አምበል የሆነው ፓትሪክ ቪዬራን አሠልጣኝ አድርገው መቅጠራቸውን ይፋ አደረጉ።
ቪዬራ፤ ሮይ ሆጅሰንን ተክቶ ነው የፓላስ አሠልጣኝ ሆኖ የተሾመው።
የቀድሞው የአርሰናል አምበል የነበረው ፓትሪክ ቪዬራ ከረዥም ጊዜ ውይይት በኋላ ነው የፓላስ አሠልጣኝ ለመሆን የተስማማው።
ሮይ ሆጅሰን ፓላስን ለመልቀቅ እንደወሰኑ ያሳወቁት ባለፈው ግንቦት ነበር።
የ45 ዓመቱ ፈረንሳዊ ባለፈው የውድድር ዘመን 14ኛ ሆነው ካጠናቀቁት ፓላሶች ጋር ለሶስት ዓመታት የሚያቆየውን ውል ፈርሟል።
"ይህን ዕድል አግኝቼ ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ በመመለሴ እጅግ ደስተኛ ነኝ" ብሏል ቪዬራ።
"ለኔ በጣም ትልቅ ቦታ የምሰጠው ፕሮጀክት ነው። ከክለቡ አለቃና ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ጋር ክለቡ ስላለው ዓላማ ብዙ አውርተናል" ብሏል ቪዬራ።
"ክለቡ በጣም ማራኪ መሠረት ያለው ነው። በፕሪሚዬር ሊጉ በርካታ ዓመታት የዘለቀም ነው። ይህን ተንተርሰን ክለቡን ወደ ተሻለ ቦታ መውሰድ እንደምንችል ተስፋ አለኝ።"
ቪዬራ ከፈረንሳዩ ክለብ ኒስ አሠልጣኝነት የተባረረው ባለፈው ታኅሣሥ ነበር።
ከዚያ በፊት በአሜሪካው ሱፐር ሊግ ሶከር የሚጫወተው ኒው ዮርክ ሲቲ አሠልጣኝ ሆኖ ለሁለት ዓመት ተኩል አገልግሏል።
ቪዬራ የአሠልጣኝነት ዘመኑን የጀመረው በማንቸስተር ሲቲ አካዳሚ ሲሆን የተጫዋችነት ዘመኑንም የቋጨው በሲቲ ነው።
ከኒስ ጋር በነበረው ቆይታ በአንደኛው ዓመት ሰባተኛ በሁለተኛው ደግሞ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሎ ነበር።
የቀድሞው የቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሠልጣኝ ሉሲዬር ፋቭሬ ፓላስን ይረከባሉ ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ከረዥም ውይይት በኋላ ሥራውን ውድቅ አድርገውታል።
ለአራት ዓመታት ከፓላስ ጋር የቆዩት የ73 ዓመቱ ሮይ ሆጅሰን ወጣቱን ቪዬራ ተክተው ወጥተዋል።
ፈረንሳዊው አማካይ ቪዬራ ከአርሰናል ጋር በፈረንጆቹ ከ1996 እስከ 2005 በነበረው ቆይታ 9 ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል።
ከፈረንሳይ ጋር የዓለምና የአውሮፓ ዋንጫን ማንሳት የቻለው ቪዬራ ከኢንተር ሚላን ጋር ሶስት የሴሪ ኤ ዋንጫዎችን በልቷል።
ቪዬራ ማንችስተር ሲቲን የተቀላቀለው በፈረንጆቹ 2010 ሲሆን ከክለቡ ጋር የኤፍ ኤ ዋንጫን ካነሳ በኋላ ጫማ መስቀሉን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።












