የትግራይ ግጭት፡ የተናጠል ተኩስ አቁሙና ያልተመለሱ ጥያቄዎች

የፎቶው ባለመብት, DT
የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረው በህወሓትና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የነበረው የሻከረ ግንኙነት ለይቶለት ወደ ወታደራዊ ግጭት ከገባ በኋላ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ነበር የአገሪቱ ሠራዊት ዋና ከተማዋን መቀለን የተቆጣጠረው።
የህወሓት አመራሮችና ኃይሎች ከመቀለ ሸሽተው ከወጡ ልክ በስምንተኛ ወራቸው ደግሞ ተመልሰው ሰኞ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ከተማዋን መቆጣጠራቸው ተነግሯል።
ሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በውጥረት ውስጥ የነበረችው የመቀለ ከተማ ምሽት ላይ የአማጺው ኃይሎች በከተማዋ መታየታቸውን ተከትሎ የክልሉን ባንዲራ እያውለበለቡ ደስታቸውን የሚገልጹ በርካታ ነዋሪዎች ወደ ጎዳና ወጥተው እንደነበረ ሪፖርቶች አመልክተዋል።
የመቀለ ከተማ ከፌደራል መንግሥቱ ቁጥጥር ውጪ መሆኗን አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን እንዳረጋገጡለት የፈረንሳይ ዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ባለሥልጣኑ እንዳሉት አማጺያኑ "በሁሉም አቅጣጫ" ከተማዋን ሲከቡ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከተማዋን ለቅቆ ለመውጣት መወሰኑንና "ሁሉም ለቅቀው ወጥተዋል። የመጨረሻዎቹም ከሰዓት በኋላ [ሰኞ] ወጥተዋል" ማለታቸው ተገልጿል።
ምንም እንኳ የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች መቀለን እና አካባቢዋን ለቅቀው መውጣታቸው ቢነገርም አሁንም ድረስ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልም ሆነ የኤርትራ ጦር ከአካባቢው ስለመውጣታቸው የተባለ ነገር የለም።
ትናንት ሰኞ፣ አመሻሽ ላይ ደግሞ ከህወሓት ከሥልጣን መባረር በኋላ በፌደራል መንግሥቱ የተሰየመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ያለው ጦርነት "ሰብዓዊነትን መሰረት ባደረገና ተጨማሪ ጉዳት በማያስከትል መልኩ" የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ጥያቄ አቀረበ።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረባቸው በተገለጸ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የፌደራል መንግሥቱ ምላሽ ሰጥቶ ግጭቱ እንዲቆም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሰኞ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የተኩስ አቁም በተናጠል ማወጁን ይፋ አድርጓል።
የተናጠል ተኩስ አቁም
ባለፉት ስምንት ወራት በትግራይ ክልል ውስጥ የተካሄደው ውጊያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የክልሉ ሕዝብ ከመኖሪያ አካባቢው የተፈናቀለ ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ የሚጠባበቁ ሆነዋል።
ባለፉት ወራት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎች የረድኤት ድርጅቶች የሚያወጡትን መረጃ መሠረት በማድረግ ለችግር ለተጋለጡ ነዋሪዎች ድጋፍ ለማቅረብ እንዲቻል የግጭቱ ተሳታፊ ኃይሎች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉና ችግሩን በውይይት እንዲፈቱ ኃያላን አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ነገር ግን በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ ሲሰጥ የነበረው ምላሽ "ከወንጀለኛ ቡድን ጋር ድርድር እንደማይኖር" የሚያመለክት ነበር። በኋላ ላይም የአገሪቱ ምክር ቤት ህወሓትን ሽብርተኛ ቡድን ብሎ ከሰየመ በኋላ ድርድር የማድረጉ ነገር ያከተመለት ጉዳይ ሆኖ ነበር።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከትግራይ ክልል የሚወጡ ሪፖርቶች ሲያመለክቱ እንደነበረው በተለያዩ ቦታዎች ከባድ ውጊያ የተካሄደ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ጦርነቶች እየተካሄዱ እንደነበር አረጋግጠዋል።
አማጺያኑ በኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች ላይ ድል እየተቀዳጁ በሺዎች መግደላቸውንና መማረካቸውን ሲገልጹ በመንግሥት በኩል ደግሞ "ሽብርተኛ" የሚላቸውን የትግራይ ኃይሎች አመራሮችን ለማደን የሚካሄድ ወታደራዊ ዘመቻ መሆኑን ሲገልጽ ቆይተዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ለተወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ በዋናነት የተሰጠው ምክንያት በክረምቱ ወቅት አርሶ አደሩ የእርሻ ሥራውን ተረጋግቶ እንዲከውን የእርዳታ አቅርቦት ሥራው ከወታደራዊ እንቅቃሴ ነጻ ሆኖ እንዲሠራጭና ለማስቻል መሆኑን ገልጿል።
የተኩስ አቁሙም "የእርሻው ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ ያለቅድመ ሁኔታ በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ" ሲሆን "ይህንን ዕድል ለክፉ ዓላማ የሚጠቀሙ ወገኖች ካጋጠሙ ግን አስፈላጊው ሕግን የማስከበር ተግባር እንደ አግባቡ የሚከናወን ይሆናል" ብሏል።
ይህንን ተከትሎ ግን ከአማጺያኑ በኩል የቀረበውን የተኩስ አቁም ጥሪ በተመለከተ የተሰጠ ምላሽ የለም። እንዲያውም የተናጠል ተኩስ አቁሙ ይፋ በተደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዋና ከተማዋን መቆጣጠራቸውን አሳውቀዋል።
ቡድኑ በመንግሥት በኩል የታወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም በተመለከተ በይፋ መቀበል አለመቀበሉን የሚያመለክት መግለጫ አስካሁን አልሰጠም።
የቀድሞው የአገሪቱና የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት አሁን የአማጺው ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ለሲኤንኤን ቡድናቸው ወታደራዊ ዘመቻውን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
"ዓላማችን የጠላትን የመዋጋት አቅም ማዳከም ነው። ትግራይ ከጠላት ኃይሎች ነጻ እስክትሆን ድረስ ዘመቻችንን አናቆምም። የሚያስፈልገውን ሁሉ እናደርጋለን" ሲሉ እንቅስቃሴያቸው እንደማይገታ ገልጸዋል።
ብዙዎች ይህ የተናጠል ተኩስ አቁም ሌላኛው ወገን ተመሳሳይ እርምጃ ካልተደገፈ በክልሉ የሚካሄደው ጦርነትን ለማስቆም አያስችልም የሚል ስጋት አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES
የሰብአዊ ቀውስ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሳምንታት በፊት ባደረገው ግምገማ የክረምቱ ዝናብ ከመጀመሩ በፊት በአስቸኳይ ወደ ተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ድጋፍ እንዲደርስ ካልተደረገ በ1977 ዓ.ም በአገሪቱ የተከሰተው አይነት በርካቶችን ለሞት የሚዳርግ ከባድ የሰብአዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ፣ የአውሮፓ አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መንግሥት "ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እያዋለ ነው" በሚል በመክሰስ ያልተገደበ የእርዳታ አቅርቦት እንዲመቻች፣ የተኩስ አቁም እንዲደረግና በበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚከሰሱት የኤርትራ ወታደሮች እንዲወጡ ሲወተውቱ ቆይተዋል።
በክልሉ አምስት ሚሊዮን ያህል ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሰረት 350 ሺህ ሕዝብ የሚሆነው በረሃብ ቋፍ ላይ ነው።
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት
አየርላንድም ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ በመውሰድ አቋም እንዲያዝበት ጥረት ብታደርግም ሩሲያና ቻይናን ከመሰሉ የምክር ቤቱ ኃያላን ድጋፍ ሳያገኝ ቀርቶ እንዲሁ በእንጥልጥል ቆይቶ ነበር።
ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ተኩስ እንዲቆም፣ ንግግር እንዲጀመርና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ ሲጠይቁ ከነበሩት አገራት መካከል አሜሪካ ለመንግሥት የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ላይ እቀባ አድርጋለች።
በተጨማሪም በግጭቱ ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ባለሥልጣናት እንዲሁም የህወሓት አባላት ላይ የቪዛ ክልከላ መጣሏን አሳውቃለች።
የአሜሪካ ሴኔትም በትግራይ ክልል ባለው ግጭት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ህወሓት እና ሌሎች የግጭቱ ተሳታፊዎች ግጭቱን እንዲያቆሙ፣ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንዲፈቀድ የውሳኔ ሐሳብ አሳልፏል።
በተጨማሪም አሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናቷንና ልዩ መልዕክተኛ በተደጋጋሚ በመላክ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ውይይት ቢያደርጉም ያቀረቡት ሐሳብ እምብዛም ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል።
አንዳንድ ዲፕሎማቲክ ምንጮች እንደሚሉት ከትግራይ ክልል ሁኔታ ጋር በተያያዘ አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀች በመሆኑ መንግሥት ችግሩን ለመቋጨት በማሰብ የተኩስ አቁም ማወጁን ሲናገሩ ይደመጣል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከተኩስ አቁሙ በኋላስ?
የተለያዩ ወገኖች በተደጋጋሚ ሲጠይቁት የነበረው በጦርነት ውስጥ ያሉት ኃይሎች ተኩስ አቁመው ንግግር በመጀመር በክልሉ የሚደርሰውን ሰብአዊ ቀውስ ለማስቆምና አካባቢውን ወደሠላም ለመመለስ ጥረት እንዲደረግ ነው።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የቀረበው የተናጠል የተኩስ አቁም ሃሳብ የእርሻ ጊዜውን ታሳቢ ያደረገ የሚመስል ከመሆኑ በተጨማሪ ንግግር ስለመጀመሩ የሚጠቁም ነገር የለውም።
መንግሥት "ሽብርተኛ" ብሎ የሚጠራው የህወሓት አመራሮች የአማጺው ኃይል አንቀሳቃሽ መሆናቸው ግልጽ ነው። ስለዚህም ከሁለት ወር በፊት ገደማ ሽብርተኛ ተብሎ በአገሪቱ ምክር ቤት ከተሰየመው ቡድን ጋር የመነጋገር ጥሪ ለማቅረብ አዳጋች ሳይሆንበት አልቀረም።
ንግግር ይጀመር ቢባል በአማራና በአፋር ክልሎች ከዚህ በፊት ያለአግባብ ወደ ትግራይ ክልል ተካለዋል የተባሉትና አሁን በተለይ በአማራ ክልል ልዩ ኃይል ቁጥጥር ስር ያሉ ሰፊ አካባቢዎች ጉዳይ ሌላው አነጋጋሪ አጀንዳ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ኃይሎች በፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት እና በጎረቤት ክልሎች ኃይሎች ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር የሚንቀሳቀሱ ከሆነ የተኩስ አቁም ጥሪው ዋጋ አይኖረውም።
በዚህ ሁኔታም ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ በአስቸኳይ የሚፈለገው የእርዳታ አቅርቦት በችግር ላይ ላለው ሕዝብ በቶሎ የመድረሱ ነገር አጠያያቂ ይሆናል።
ቢሆንም ግን ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ይህ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ምንን ተከትሎ የመጣ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ለዚህም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መንግሥት ተገቢውን ማብራሪያ እንዲሰጥ እየጠየቁ ነው።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ
ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ለቀረበው የተናጠል የተኩስ አቁም በትግራይ ኃይሎች የሚሰጠው ምላሽ እንዳለ ሆኖ ለወራት ግጭቱ እንዲቆም ሲጠይቁ የነበሩት ወገኖች በበጎ እንደሚመለከቱት ይጠበቃል።
እንዲሁም ጦርነቱ እየተባባሰ የሚሄድ ከሆነ ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ እየተዘጋጁ እንደነበር ሲነገር ለቆዩት አሜሪካና የአውሮፓ አገራት ሌሎች አማራጮችን እንዲመለከቱ ሊያደርግ ይችላል።
ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና አገራት በትግራይ ውስጥ እየታየ ያለውን ተለዋዋጭ ሁኔታንና የኢትዮጵያ መንግሥት የተኩስ አቁም ውሳኔን በተመለከተ የሚሰጡት ምላሽ በቀጣይ ቀናት የሚታይ ይሆናል።
አሜሪካ፣ አየርላንድና ዩናይትድ ኪንግደም የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ ላይ ይፋዊ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደረግ ጠይቀዋል። ስብሰባውም በመጪው አርብ ሊደረግ እንደሚችል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።














