የትግራይ ኃይሎች መቀለን ተቆጣጠሩ፤ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አወጀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰኞ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም የትግራይ ኃይሎች የክልሉን መዲና መቀለን መቆጣጠራቸውን ሲያሳውቁ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በጦርነት በተጎዳችው ትግራይ ክልል የተናጥል ተኩስ አቁም አውጇል።
ይህንንም ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሰንደቅ አላማ በማውለብለብና ርችት በመተኮስ ደስታቸውን ሲገልፁ እንደነበር ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት መቀለ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር መግባትን በተመለከተ የሰጠው አስተያየት የለም።
መንግሥት የትግራይ አማፂ ኃይልን አስወጥቶ መቀለን በመቆጣጠር አሸንፌያለሁ ካለም ስምንት ወራት ተቆጥረዋል።
ጦርነቱ ክልሉን ከፍተኛ ወደ ሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ከትቶታል።
በክልሉ አምስት ሚሊዮን ያህል ነዋሪዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሰረት 350 ሺህ ሕዝብ የሚሆነው በረሃብ ቋፍ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ ክልሉን ያስተዳድር የነበረውን ህወሓት ከስልጣን ለማስወገድ ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ህወሓት ግንኙነታቸው በዋነኝነት የሻከረው በአገሪቱ ላይ ባሉ ፖለቲካዊ ለውጦች በተለይም ብሔርን መሰረት ባደረገው የፌደራል ሥርዓት ጋር በተገናኘ ነው።
ህወሓት የሰሜን ዕዝ መቆጣጠሩን ተከትሎ ጦርነቱን አቀጣጣጥሎታል ተብሏል።
በክልሉ ውስጥ በጦርነቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላት የጅምላ ጭፍጨፋ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈፀም ይወነጀላሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎችም ተገድለዋል።
በትናንትናው ዕለት ከመቀለ ውጭ በህወሓትና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ውጊያዎች እንደነበረ የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
ሰኞ እለት ባልተጠበቀ ሁኔታ የትግራይ ኃይሎች ክልሉን የተቆጣጠሩ ሲሆን ይህም በባለፈው ወራት የነበረው ጦርነት ሁኔታዎችን ይቀይራል ብሏል።
የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት መቀለን ተቆጣጥረናል ብለዋል።
ሮይተርስ ከሁለት የዓይን እማኞች እንደሰማው የትግራይ ወታደሮች መቀለ ውስጥ እንደታዩ ነው።
ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ የመንግሥት ባለስልጣን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ለቆ እንደወጣና አማፂያኑም ሁሉንም መውጫዎች እንደተቆጣጠሩት ነው።
ባለስልጣኑ እንዳሉት የከተማዋን የተለያዩ መውጫዎች አማፂያኑ መዝጋቱን ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለመውጣት ወስኗል ብለዋል።
"ሁሉም ለቀው ሄደዋል። ክልሉ አስተዳዳሪ የለውም" በማለት ስማቸው ያልተጠቀሰ እኒሁ ባለስልጣን ተናግረዋል።
ነዋሪዎች የፌደራሉ ሠራዊት መውጣቱን ተከትሎ ደስታቸውን እየገለፁ ነበር። አንድ የዓይን እማኝ ለኤኤፍፒ እንደተናገረው "ሁሉም ሰው ከቤቱ ወጥቶ ጎዳና ላይ ነው። ሕዝቡ ሁሉ ሙዚቃውን ከፍቶ እየተደሰተ ነው። ሰንደቅ አላማቸውን አውጥተዋል ሙዚቃም ከፍ ብሎ ይሰማል" ብሏል።
ህወሃት ክልሉን ከተቆጣጠረ በኋላ ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል አስተዳደር በሚል ሲሆን "አስደናቂ ድል" ካለ ተገኝቷል ብሏል። መቀለም "በትግራይ መከላከያ ኃይል በሙሉ ቁጥጥር ስር ናት" ብሏል።
ለህዝቡና ለሃይሉም "ንቁ ሆነው እንዲከታተሉ ትግራይ ከወራሪ ኃይሎች ነፃ እስክትሆን ድረስም እንዲታገሱ" በሚል በመግለጫው አካቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊቱ ወጥቷል ስለመባሉ ምንም አስተያየት አልሰጠም። ነገር ግን በብሔራዊ ቴሌቪዥን በተሰጠው መግለጫ የተኩስ አቁም "የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ" እንደሚቆይና እርዳታ በአግባቡ እንዲደርስና ለፖለቲካዊ መፍትሄም ቦታ ለመስጠት ነው ብሏል።
ህወሓት በተኩስ አቁሙ ላይ አስተያየት አልሰጠም። የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር እንደተወያዩና ተኩስ አቁም ሊፈፀም እንደሚችል "ተስፋ አለኝ" ብለው ነበር።
"ሰላማዊ ዜጎች ሊጠበቁ ይገባል። ሰብዓዊ እርዳታዎች ለሚያስፈልጋቸው በሙሉ ሊረዱ ይገባል እንዲሁም ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል" በማለት በመግለጫቸው አትተዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካና አየርላንድ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ጉባኤ አስቸኳይ ክፍት ስብሰባ በትግራይ ላይ እንዲያደርግ ጠርተዋል።
ሰንደቅ አላማና ደስታ
ባልታሰበ ፍጥነት የክልሉ የመንግሥት ተወካዮች ፈልገውም ባይሆን በሰላማዊ ሁኔታ መቀለን ለቀው እየወጡ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ፌደራል ወታደሮች ቢሯቸው በኃይል ገብተው የሳተላይት ቁሳቁሶችን አውድመዋል በማለት አውግዟል።
ቢቢሲ ከመቀለ ነዋሪዎች እንደሰማው በርካቶች ደስታቸውን በጎዳና ላይ እየገለፁ ሲሆን በርካቶችም ለትግራይ አማፂያን ያላቸውን ድጋፍ ሰንደቅ አላማ በማውለብለብ ሲያሳዩ ነበር።
ይህም ሁኔታ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በወጡ ፎቶዎች ታይቷል።
ህወሓት ከተማዋን መቆጣጠሩን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲረጋጉና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።
የኖቤል አሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጦርነቱ በኅዳር ወር ተጠናቋል ቢሉም ውጊያው ቀጥሏል።
ህወሓት ከሌሎች ኃይሎች ጋር በመጣመር የትግራይ መከላከያ ኃይልን መስርቷል።
በያዝነው ወር የተባበሩት መንግሥታት በትግራይ ክልል ረሃብ አለ ያለ ሲሆን ሁኔታውንም "ካታስትሮፍ" በማለት የረሃቡ ሁኔታ በክልሉ በሰፊው ሊዛመት እንደሚችል አስጠንቅቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ምግብ ድርጅት፣ የተመድ የምግብ እና እርሻ ድርጅት እና ዩኒሴፍ በክልሉ ያለውን ቀውስ ለመግታት አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።
ነገር ግን ይህንን ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት አይቀበለውም። በክልሉም ረሃብ እንደሌለና እርዳታም እየተከፋፈለ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል።












