ትግራይ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በትግራይ ረሃብ አሉ የሚሉ ሪፖርቶችን አስተባበሉ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጦርነት በተጎዳችው ትግራይ ክልል ውስጥ ረሃብ አለ የሚሉ ሪፖርቶችን አስተባበሉ።
አገሪቱ ብሔራዊ ምርጫዋን ባደረገችበት በትናንትናው ዕለት በምርጫ ጣቢያ ላይ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ችግር መኖሩን አምነው ይህ ግን መንግሥት የሚፈታው ነው ብለዋል።
ስምንተኛ ወሩን ያስቆጠረው የትግራይ ጦርነት አምስት ሚሊዮን የክልሉን ነዋሪዎች የምግብ እርዳታ ፈላጊ እንዳደረጋቸው የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያስረዳል።
ከ350 ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎች ደግሞ በረሃብ ቋፍ ላይ መሆናቸውን በቅርቡ የወጣ ተባበሩት መንግሥታት ግምገማ ሪፖርት ያሳያል።
"በትግራይ ረሃብ የለም" በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ድምፃቸውን በትውልድ ስፍራቸው ከሰጡ በኋላ ለቢቢሲዋ ካትሪን ባያሩሃንጋ ተናግረዋል።
"ችግር አለ ነገር ግን መንግሥት ይህንንም መቅረፍ ይችላል" በማለት አክለዋል።
ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ በፀጥታው ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ ላይ በትግራይ ረሃብ አለ ብለው ነበር።
ኃላፊው በትግራይ ውስጥ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ እየተዋጋ ያለው የኤርትራ ሠራዊት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሞበታል ብለዋል።
ኤርትራ ይሄንን ውንጀላ አትቀበለውም።
በዚሁ ወቅትም ስለ ኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል መቼ እንደሚወጡ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ የኤርትራ ወታደሮችን ገፍታ እንደማታስወጣና ሁኔታውንም በሰላም ለማጠናቀቅ ከኤርትራ ጋር እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከአስር ቀናት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ የወጣ ኢንተግሬትድ ፉድ ሴኩሪቲ ፌዝ ክላሲፊኬሽን የተባለ ግምገማ መሰረት 350 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች "ካታስትሮፍ" በሚባል ሁኔታ በረሃብ ቋፍ ላይ እንደሚገኙ አትቷል።
በወቅቱም የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ረሃብ የለም እንዲሁም እርዳታ እየተዳረሰ ነው ብለዋል።
ይሄው ግምገማ ተጨማሪ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች በቀውስ ላይ ወይም አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሏል።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በበኩላቸው ምግብ እያዳረሱ እንደሆነና የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች እንዳይገቡ ከልክለዋል የሚለውንም ሪፖርቶች ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
"ምንም የምንበላውነገር የለም"
በምዕራብ ትግራይ ቃፍታ ሁመራ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ለቢቢሲ በቅርቡ እንደተናገሩት መራባቸውን ነው።
"ምንም የምንበላው ነገር የለንም" በማለት አንድ ግለሰብ በስልክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይኸው ግለሰብ ለወራት በዘለቀው ጦርነት እህላቸው እንዲሁም ከብቶቻቸው እንደተዘረፈ ነው።
ጥቅምት 24 የተጀመረው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉን ነዋሪዎች አፈናቅሏል፤ የእርሻ ተግባሩንም አስተጓጉሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ የክልሉ አስተዳዳሪ የነበረውን ህወሓትን ከስልጣን ለማስወገድ ወታደራዊ ዘመቻ ጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሚያደርጓቸው የፖለቲካ ማሻሻያዎች ጋር ተያይዞ ከህወሓት ጋር ያለው ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ የሻከረ ሲሆን ግጭቱንም ያቀጣጠለው የህወሓት የፌደራል መከላከያ ዕዝን መቆጣጠሩን ተከትሎ ነው።
"የሱዳን ወታደሮችም በኢትዮጵያ አሉ"
በዚሀ ጦርነት ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ተባብራለች። የኤርትራ ሠራዊት ድንበሩን አቋርጦ በመግባት የሰብዓዊ ጥሰት ፈፅመዋል ተብለው ይወነጀላሉ።
ከዚህም ውስጥ የምግብ ዕጥረት እንዲፈጠር ሆን ብለው እየሰሩ ነው የሚል ሲሆን ኤርትራ ግን ይህንን አስተባብላለች።
በግጭቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮችም ሆነ ሌሎች አካላት ጥሰቶችን በመፈፀም ተወንጅለዋል።
መጋቢት ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኤርትራ ወታደሮች ይወጣሉ ቢሉም ቀኑን አልጠቀሱም።
በቅርቡም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ አቀባይ በበኩላቸው መከላከያ ሚኒስትርን ዋቢ አድርገው የኤርትራ ሠራዊት ለቀው እየወጡ ነው ብለው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ገፍተን አናስወጣቸውም በሰላም ነው እንዲወጡ የምንፈልገው። ይሄም እርግጠኛ ነኝ ይሆናል" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለቢቢሲ።
"ከኤርትራ ጋር ጉዳዩን በሰላም ለመቋጨት አብረን እየሰራን ነው" በማለትም አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሱዳን ወታደሮችም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንዳሉም ተናግረዋል።
የሱዳን ወታደሮች ሁለቱም አገራት ግዛቴ ነው የሚሉት የአል ፋሽጋ ትሪያንግልን መቆጣጠራቸው ይታወሳል።
ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በብልጽግና ስም ሲወዳደሩ የመጀመሪያቸው ነው።
በስልጣን ማግስት ያሳዩት የለውጥ መንፈስ አገሪቱ ዲሞከራሲያዊና ክፍት እንድትሆን ማድረጋቸው በአገሪቱ ባሉ በርካታ ዜጎች ድጋፍን አስገኝቶላቸው ነበር።
ለሁለት አስርት ዓመታት ተፋጠውበት የነበረውን የኤርትራና የኢትዮጵያን የድንበር ፍጥጫ መቋጨታቸውን ተከትሎ ከሁለት ዓመት በፊት የኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል።
ነገር ግን በትግራይ ያለው ጦርነት ይህንን ምስላቸውን አጠልሽቶታል። በክልሉም ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ምርጫ አይካሄድም።













