ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ ለትግራይ ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሔ እንፈልግ ማለታቸው ተዘገበ

የትግራይ ኃይሎችን እየመሩ እንደሆነ የሚገመተው ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ በድርድር ላይ የተመረኮዘ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናገሩ።
"ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማግኘት እንሻለን። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን እንዲገነዘብ እፈልጋለሁ። አማራጭ ካጣን ግን በወታደራዊ እርምጃ ችግሩን እንፈታለን" ሲሉ ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
ጄነራሉ ይፋ ካልተደረገ ሥፍራ ሆነው ከሮይተርስ ጋር በሳተላይት ስልክ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ለትግራይ ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ መጠቆማቸው ተዘግቧል።
የፌደራል መንግሥት ባለፈው ሳምንት ከትግራይ ክልል አካባቢዎች መከላከያ ሠራዊቱን አስወጥቶ፤ የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁ ይታወሳል።
በሌላ በኩል ህወሓት በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን ቢያስቀምጥም ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላስ የለም።
ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም አገራት የፌደራል መንግሥት የተኩስ አቁምን በአወንታዊ መንገድ እንደሚያዩት ሲገልጹ የቆየ ሲሆን ይህም ተኩስ አቁም ለግጭቱ ማብቂያ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።
ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የህወሓት ኃይሎች የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ለስምንት ወራት በተካሄደ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው ይነገራል።
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል የቀረበን ጥያቄን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ ሠራዊት የትግራይ ክልል ዋና መቀመጫ መቀለን ለቆ የወጣ ሲሆን ይህ ውሳኔም ወታደራዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ቢገልጹም አማጺያኑ ግን በወታደራዊ ጫና ምክንያት ነው ይላሉ።
ለተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔው ቀጣዩን የክረምት (የግብርና ወቅት) ከግምት በማስገባት፣ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲሰራጭ፣ ሠራዊቱ በሌሎች አገር አቀፍ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ስላለበት የሚሉና ሌሎችም ምክንያቶችን መንግሥት አቅርቧል።
የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው ሠራዊቱን ድል አድርገው መቀለን ጨምሮ ሌሎችም የትግራይ ከተሞችን በቁጥጥራቸው ሥር እንዳዋሉ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱም ወገኖች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እያሳሰበ ነው።
ህወሓት ከቀናት በኋላ ይፋ ባደረገው የተኩስ አቁም ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።
ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ ህወሓት የጠየቀ ሲሆን፤ ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል።
ጄኔራል ፃድቃን ከሮይተርስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በትግራይ መሸነፋቸውን ካላመኑ ጦርነቱ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
አያይዘውም መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ክልሉ እንዳይደርስ ሆነ ብሎ እያስተጓጎለ መሆኑን መናገራቸውም ተዘግቧል።
መቀለ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መሆኗ ከተገለጸ ወዲህ እርዳታ ወደ ትግራይ መግባት እንዳልቻለ ቢገለጽም፤ የፌደራል መንግሥት የእርዳታ እንቅስቃሴን እንዳላገደ ተናግሯል።
ጄኔራል ፃድቃን ወደ 8,000 የሚጠጉ የመከላከያ ሠራዊት ወታደሮች በህወሓት ኃይሎች መማረካቸውን ቢናገሩም የአገር መከላከያ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ይህ ቁጥር የተጋነነ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ አስፈላጊ ከሆነ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን በትግራይ እንደሚሰማሩ ጠቅሰው ነገር ግን ሰላማዊ መፍትሔ እንደሚሹ ጠቁመዋል።
"በግጭቱ መግፋት እንችላለን። ውጤቱ ግን መግደል ነው። በሁለቱን ወግን ዶላር ይባክናል። በዚህ መንገድ ማሸነፍ አይቻልም" በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።












