የትግራይ ኃይሎች ከአማራ ክልል ጋር ወደሚያዋስኑ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተነገረ

የትግራይ ኃይሎች ከሳምንት በፊት መቀለ ከተማ በገቡ ወቅት

የፎቶው ባለመብት, YASUYOSHI CHIBA

የምስሉ መግለጫ, የትግራይ ኃይሎች ከሳምንት በፊት መቀለ ከተማ በገቡ ወቅት

የትግራይ ክልል ኃይሎች ከአማራ ክልል ጋር ወደሚያዋስነው የድንበር አካባቢ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተነገረ።

በትግራይ የሚገኙ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ የዩናይትድ ኪንግደሙ 'ዘ ጋርዲያ' ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ የህወሓት ኃይሎች በብዙ መኪኖች ተጭነው ወደ ምዕራብ አቅጣጫ አምርተዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዋች በበኩሉ በትግራይ ክልል አዲስ ግጭት ሊቀሰቀስ እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል። ምንም እንኳን የፌደራል መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያውጅም የትግራይ ክልል አማጺ ኃይሎች ግን ለአዲስ ግጭት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ምልክቶች አሉ ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር "የአማራ ክልልን ከማንኛውም ጥቃት ለመመከት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል" ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት ዛሬ በሰጡት መግለጫ ሲሆን፤ "አሸባሪው ትህነግ እዚህ ግባ የሚባል ተፅዕኖ አያደርስም" ማለታቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

የፌደራል መንግሥት መቀለን ለወራት ተቆጣጥሮ ከቆየ በኋላ ከሳምንት በፊት በርካታ የትግራይ አካባቢዎችን ለቅቆ መውጣቱ ይታወሳል። የትግራይ ኃይሎችም መቀለን ጨምሮ በርካታ የትግራይ አካባቢዎችን በቁጥጥራቸው ሥር እንደሆኑ አስታውቀዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተኩስ አቁም እንዲደረግ መጠየቁን ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት ባለፈው ሰኞ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም የተናጥል የተኩስ አቁም ማወጁም ይታወሳል።

ይህን የማዕከላዊው መንግሥት ያለ ቅድመ ሁኔታ የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅን ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና አገራት በአወንታዊ መልኩ መቀበላቸውን ገልጸዋል። ሆኖም ግን ግጭትን ማስቆም የሚችል እንዲሆን አሳስበዋል።

የህወሓት ኃይሎች ግን የተኩስ አቁም አዋጁን ለመቀበል ሰባት ነጥቦችን የያዘ ቅድመ ሁኔታን ባለፈው እሁድ ይፋ ቢያደርጉም ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን የተሰጠ ምላሽ የለም።

ከእነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል፤ "የአማራና የኤርትራ ኃይሎች በወረራ ከያዙት የትግራይ ግዛቶች በመውጣት ከጦርነቱ በፊት ወደነበረው ቦታ እንዲመለሱ" የሚጠይቅ ነው።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሳምንት በፊት ለሮይተርስ የዜና ወኪል "የትግራይ ኃይሎች ጠላትን ለመዋጋት ካስፈለገ ወደ ኤርትራ እና አማራ ክልል ይገባሉ" ብለው ነበር።

"ዋነኛ ግባችን የጠላትን የመዋጋት አቅም ማዳከም ነው። ይህን ለማድረግም ወደ ኤርትራም ወደ አማራ ክልልም እንገባለን" ሲሉም አክለዋል።

ጦርነቱን ተከትሎ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሱባቸው ስፍራዎችን በቁጥጥሩ ሥር ካዋለ በኋላ፤ ክልሉን የሚያስተዳድረው ፓርቲ፤ "ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምትና ራያ በራሳቸው መስዋትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች መሆናቸውን በድጋሚ እናሳውቃችኋለን" ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ከህወሓት ኃይሎች የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመመከት "ብቃትም ችሎታውም አለን" ማለታቸውን እና የፌደራል መንግሥት ጦሩን ከትግራይ ለማስወጣት መወሰኑ በክልሉ መንግሥት እንደሚደገፍም መናገራቸው ተዘግቧል።