የኢትዮጵያ ፖሊስ የትግራይ ተወላጆችን እያዋከበ ነው የሚል ክስ ቀረበበት

የፎቶው ባለመብት, Sean Gallup
በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በባለሥልጣናት መዋከብ እየደረሰባቸው እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ሪፖርቶች እየተሰሙ ነው።
ቢቢሲ በማንነታችን ኢላማ ተደርገናል እንዲሁም በዘፈቀደ እየታሰርን ነው ያሉ የትግራይ ተወላጆችንም አናግሯል።
በተለይም በፖሊስ መዋከብ እየደረሰብን ነው የሚሉ ሪፖርቶች መሰማት የጀመሩት የኢትዮጵያ የፌደራል ሠራዊት መቀለን ለቆ መውጣቱን ካሳወቀ በኋላ ነው።
ህወሓት በትግራይ ያሉ ቁልፍ ከተሞችን እንደገና መቆጣጠሩንም አሳውቋል።
የፖሊስ ቃለ አቀባይ በበኩሉ ማንም ሰው ቢሆን በማንነቱ ኢላማ አይደረግም ሲል ክሱን አጣጥሎታል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ከትናንት በስቲያ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ በአክቲቪስቶች፣ በጋዜጠኞች እና የትግራይ ተወላጅ በሆኑ ሰዎች ላይ እስር እየተፈፀመ እንዲሁም የንግድ ቤቶችም እየታሸጉ እንደሆነ መረጃዎች ደርሰውኛል ብሏል።
"እስራትን ጨምሮ ሌሎች በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎች በበቂ ምክንያት የተደገፉ እና ሕጋዊ ሂደትን በመከተል ለጉዳዮቹ ፈጣን እልባት በሚሰጥ መልኩ እንዲሆኑ ሰብዓዊ መብቶችን መርህ ያደረጉ መሆነ አለባቸው" ሲል ኢሰመጉ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም እንዲሁ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎች እንዲሁም ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታም እየተከታተለ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ይህም ሁኔታ በነዋሪዎች ላይ ማንነትን መሰረት ባደረገ ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይሆንም ስጋት እንዳሳደረበት ኮሚሽኑ አስታውቋል።
"ማንኛውም አይነት እስር ሁልጊዜም ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል" በማለትም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ መናገራቸውን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በፌደራል መንግሥት የተሾመው ጊዜያዊ የትግራይ አስተዳደር ህወሓት በበርካታ አካባቢዎች የእነሱ ተባባሪ ናቸው የተባሉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የበቀል ግድያ እየፈፀመ ነው ሲል ከሷል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ይህ ነው የሚባል ውጊያ እንደሌለ የተገለፀ ቢሆንም በሁለቱም ወገን በኩል ወታደሮችን በምዕራብ ትግራይ በኩል እያሰባሰቡ መሆኑን ሪፖርቶች መሰማታቸውን ተከትሎ ጦርነቱ እንዳላለቀ አመላካች ሆኗል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ተዋጊዎች ተገድለዋል።
ባለፈው ሳምንት የፌደራሉ መንግሥት ወታደሮቹን ከመዲናዋ መቀለ እንዳስወጣ ቢገልፅም ህወሓት በበኩሉ መቀለን በኃይል እንደተቆጣጠሩ ተናግሯል።
የፌደራል መንግሥት ባለፈው ሳምንት ከትግራይ ክልል አካባቢዎች መከላከያ ሠራዊቱን ማስወጣቱንና የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን አስታውቋል።
በሌላ በኩል ህወሓት በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን ቢያስቀምጥም ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።












