በትግራይ የመገናኛ፣ የመብራትና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ጥሪ ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, YASUYOSHI CHIBA
በጦርነት የተጎዳችው ትግራይ ለአስቸኳይ እርዳታ ክፍት እንድትሆንና የመገናኛ፣ መብራትና የትራንስፖርት አገልግሎቶች አንዲቀጠሉም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየጠየቁ ነው።
መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያውጅም ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎችን ህወሓት መቆጣጠሩን ተከትሎ ስልክ ተቋርጧል እንዲሁም የአየርና የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎቶችም ተቋርጠዋል።
የኢትዮጵያ የፌደራል ሠራዊት መውጣት እንዲሁም የተናጠሉ የተኩስ አቁም አዋጅ በችግር ላይ ያሉትን ነዋሪዎች ሁኔታ አላቀለለውም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ የመቀለና የሽረ አየር ማረፊያዎች ክፍት እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
ኮሚሽነሩ በትግራይ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ "እየከፋ ነው" በማለት በትዊተር ገፃቸው አስፍረው አስቸኳይ የሆነ እርዳታ ለማድረስም መደረግ ይገባዋል ያሉትንም አስፍረዋል።
የተቸገሩ ሰዎችንም ለመድረስ ከአየር ማረፊያዎች በተጨማሪ የመብራትና የመገናኛ ዘዴዎች እንዲቀጠሉ ጠይቀዋል።
የአውሮፖ ሕብረት የውጭ እና የደኅንነት ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው "የተኩስ አቁም ማለት የክልሉን መብራት መቁረጥ እና አስፈላጊ የሚባሉ መሰረተ ልማትን ማውደም አይደለም" ብለዋል።
ታማኝ የሆነ የተኩስ አቁም ማለት አስቸኳይ እርዳታ የሚፈልጉ ሚሊዮኖች ህፃናት፣ ሴቶችና ወንዶች እንዲደርሳቸው የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ነው ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም ህይወትን ማዳን የሁሉም ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ አስቸኳይ እርዳታን አግዷል የሚለውን ክስ አይቀበለውም።
"የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በማገድ የትግራይን ሕዝብ ለማፈን እየሞከራችሁ ነው እንዲሁም ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀማባችሁት ነው የሚሉ አስተያየቶች ተቀባይነት የሌላቸውና ከእውነታው የሚቃረን ነው" በማለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአዲስ አበባ ተቀማጭ ለሆኑ ዲፕሎማቶች ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን በበከሉላቸው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት መንግሥታቸው የተባበሩት መንግሥታት እርዳታ ከመዲናዋ አዲስ አበባ ወደ ትግራይ ሁለት አየር ማረፊያዎች እንዲደርሱ ለማድረግ ለማሳለጥ ፍቃደኛ ነው ብለዋል።
ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ክልሉ ውስጥ ከገባ በኋላ ለሚፈጠሩ ነገሮች መንግሥት ኃላፊነቱን አይወስድም ብለዋል።
የሮይተርስ የዜና ወኪል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ ቶሚ ቶምሰንን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የእርዳታ አቅርቦት በቅርቡ ይጀመራል ብሏል።
አስተባባሪው እንዳሉት በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ለ40 ሺህ ሰዎች እርዳታ ይደርሳል ተብሏል።
"መሬት ላይ ያለው እውነታ ሰዎች ሞተዋል፣ እየሞቱ ነው ይህንን መከላከል ካልቻልንና እርዳታ ማቅረብ ካልቻልን የበለጠ ሰዎች ይሞታሉ" በማለት ቶሚ ቶምሰን በጄኔቫ በተደረገው ስብሰባ ላይ በሳተላይት ስልክ ከመቀለ ተናግረዋል።
ለስምንት ወራት ያህል የተደረገው ጦርነት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ያለውን የክልሉ ነዋሪ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ጠባቂ አድርጎታል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሰረት 350 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች በረሃብ ቋፍ ላይ ናቸው።
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦሩን ከክልሉ መዲናዋ መቀለ እንዳስወጣና የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጁን አስታውቋል።
የተኩስ አቁሙ አርሶ አደሩ በዚህ ክረምት ወቅት ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲያርስ መሆኑን ከቀናት በፊት አሳውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በማዕከላዊ መንግሥት ላይ ጫና መደረግ የለበትም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም እንዲሁ ወታደራዊው ዘመቻ ተሳክቷል ካሉ በኋላ የመቀለ ከተማ የወታደራዊ ስበት ማዕከል መሆኗ እንዳቆመ በመግለፅ ጦሩ የወጣበትን ምክንያት አስረድተዋል።
ጦሩ ተገዶ ነው የወጣው በማለት ለሮይተርስ የተናገሩት የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ መላው ክልሉ በቁጥጥሩ ውስጥ እስኪገባ ድረስ ውጊያው እንደማይቆም ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ያቋረጣቸውን የኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮምዩኒኬሽን፣ ትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶች ሳይለቅ ድርድር አይኖርም ማለታቸውንም ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የተቋረጠውን የቴሌኮም አገልግሎት በአስቸኳይ እንዲመልስ ጥሪ አቅርቧል።












