በትግራይ ጦርነት የተሳተፉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሰላም አስከባሪነት እንዳይሰማሩ ተጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
በትግራይ ጦርነት የተሳተፉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሰላም አስከባሪነት ከመሰማራት እንዲታገዱ የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ጠየቁ።
የኮሚቴው ሊቀ መንበር ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ በትግራይ ክልል ጦርነት የተሳተፉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ አለመሳተፋቸው በአስተማማኝ የማጣራት ሂደት እስኪታወቅ ድረስ በተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ሥራዎች እንዳይሳተፉ በሚል ጥሪ አቅርበዋል።
ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ ይህንን የጠየቁት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በትናንትናው ዕለት በፃፉት ደብዳቤ ነው።
ዘጠኝ ወራት ያህል ባስቆጠረው አስከፊው የትግራይ ጦርነት የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አባላት ከኤርትራና ሌሎች ታጣቂ አካላት በጅምላና መዋቅራዊ በሆነ መልኩ መድፈር፣ ንፁሃንን በማስራብ፣ በዘፈቀደ ግድያዎች፣ ጭፍጨፋዎችና ሌሎች እንደ ጦር ወንጀሎችና በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ስለመሳተፋቸው ማስረጃዎች አሉ ብለዋል።
"በኢትዮጵያ ውስጥ አሰቃቂ በሚባለው የትግራይ ግጭት የተሳተፉ ሁሉም አካላትና የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ወታደሮች በሰላማዊ የትግራይ ነዋሪዎች ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል" በማለት ሊቀ መንበሩ ደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።
አክለውም "አንድ ወታደር ቀድሞ የሰራው ነገር በሰላም አስከባሪነት ሲሳተፍ ምን ዓይነት ባህርይ እንደሚኖረው አመላካች ነው። እንዲህ አይነት ጥሰቶችን መፈፀም የለመዱ ወታደሮች የተባበሩት መንግሥታትን መለዮ ስለለበሱ ባህርያቸው ይቀየራል ማለት አይደለም። በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ ወታደሮች በሰላም አስከባሪነት ሲያገለግሉ የሚያመጣውን አስከፊ ውጤቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት በትግራይ ጦርነት የተሳተፉ ወታደሮች ከሰላም አስከባሪነት ሊታገዱ ይገባል" ብለዋል።
ሴናተሩ እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በመሳሰሉ ገለልተኛ ተቋማት የማጣራት ሂደት እስኪታወቅ ድረስ እግዱ ሊፀና ይገባል በማለት አስፍረዋል።
በደብዳቤያቸው ላይ አክለውም ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮች የምታዋጣ እንደመሆኗ መጠን የተባበሩት መንግሥታት በሰላም ማስከበሩ ላይ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በትግራይ ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ስለመሳተፋቸው ጠንከር ያለ የማጣራት ሂደት እንዲከናወን መጠየቃቸውም ሰፍሯል።
ሊቀ መንበሩ እንዳሉት በሄይቲ የተሰማሩ የሲሪላንካ የሰላም አስከባሪዎች ያደረሱትን ወሲባዊ ጥቃት ዋቢ በማድረግ የተባበሩት መንግሥታት ጥሰት ፈፃሚዎች በሰላም አስከባሪነት እንዳያገለግሉ ተመድ ቁርጠኝነቱን ማረጋገጥ አለበት ብለዋል።
በብሔራዊ ደረጃ ማጣሪያ ተደርጎ በክልሉ በግለሰቦች ወይም በተወሰኑ አካላት ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸው እስኪረጋገጥ ድረስ በክልሉ ወታደራዊ ዘመቻዎች በተሳተፉ ግለሰቦችም ይሁን አካላት ላይ ከወደፊቱ የሰላም የማስከበር ተግባራት ሊታገዱ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ እንደዚህ አይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አድርሰዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ወታደሮች በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪነት ዘመቻዎች "ለማገልገል ብቁ አይደለም" በማለት አስምረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሴናተሩ ለፃፉት ደብዳቤ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ወሲባዊ ብዝበዛ እና በደል ለመከላለል በሚል ውሳኔን በአውሮፓውያኑ 2003 ውሳኔ አሳልፏል።
ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰብዓዊነት ሕግ እና በሰብዓዊ መብት ሕጎች ላይ ከባድ ጥሰቶች ተፈፅመዋል የተባሉ የሰላም አስከባሪዎችን ማሰማራት የሚከለክል ፖሊሲም በአውሮፓውያኑ 2011 ማውጣቱን በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።
የመንግሥት ወታደሮች እንዲህ ሰፋ ባለ ጥሰት ፈፅመዋል ተብለው በሚጠረጠሩበት ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ከዚህ ቀደም ብሩንዲና ሲሪላንካ ላይ እንዳደረገው 'ስክሪን ፕላስ" (እንደገና የማጣራት) ሂደት በሚል ባወጣው መሰረት የማጣራት ስራ እንደተሰራ ጠቅሷል።
በዚህም መንግሥታት የራሳቸውን ወታደሮች ተሳትፎ እንዲያጣሩ የሚያደርግበት ሂደት ነው።
ነገር ግን መንግሥታት ለዚህ ፈቃደኛና ግልፅ ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሶ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ተፈጸሙ በተባሉ የጦር ወንጀሎችና በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ክስ የቀረበበት በመሆኑ ይህንን ለማድረግ ብቁ አይደለም ተብሏል።
በዚህም ምክንያት ይህንን ተግባር በዋነኝነት መስራት ያለበት የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በስምምነት ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም አስፈላጊነትን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ መወያየታቸው ተጠቁሟል።
አሜሪካ አስቸኳይ፣ ዘላቂና በስምምነት ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ እንዲሁም የኤርትራና የአማራ ሚሊሻ ከትግራይ ክልል እንዲወጡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል መናገሯ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ያልተገደበና ደኅንነቱ የተጠበቀ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ጠይቃለች።
አሜሪካ በዚህ መግለጫዋ ላይ የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ ድንበሮች በኃይል ወይንም ሕገ መንግሥቱን ባላከበረ መልኩ ሊጣስ እንደማይገባውም አፅንኦት ሰጥታለች።
በትግራይ ክልል ላይ የሰብዓዊ መብቶችን የፈፀሙ አካላትን ተጠያቂ ከማድረግ በተጨማሪ በአገሪቱ ላይ የተጋረጠውን የብሔርና የፖለቲካ ልዩነቶችን መፍታት የሚቻልበት ሁሉን አካታች ውይይትም አስፈላጊነትንም አስምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ስላደረጉት ውይይት ያሉት ነገር የለም።
የፌደራል መንግሥት ባለፈው ሳምንት ከትግራይ ክልል አካባቢዎች መከላከያ ሠራዊቱን ማስወጣቱንና የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን አስታውቋል።
በሌላ በኩል ህወሓት በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን ቢያስቀምጥም ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።












