ጎረቤት በድምጽ ረበሸች በሚል ትዘጋ የተባለችው የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ይግባኝ ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, The Ethiopian Evangelical Church
በኢትዮጵያ የመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን የፈረንሳይ ለጋሲዮን አጥቢያ የሚወጣ ድምጽ ረብሾኛል ባሉ አንድ ግለሰብ በቀረበባት አቤቱታ እንድትዘጋ መወሰኑን በመቃወም ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ጠየቀች።
ቤተክርስቲያኒቷ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ የፍትሃ ብሔር ችሎት የአመልካችን እና የቤተሰባቸውን በሰላማዊ እና በምቹ አካባቢ የመኖር መብትን ነክታለች ሲል ውሳኔ ሰጥቶ ነበር።
ቤተ ክርስቲያኗ ለአምልኮ የምትጠቀመው ግቢ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት በሚል ካርታ የወጣበት በመሆኑ ቤቱ በማስተር ፕላኑ መሰረት ለወጣበት አላማ ይዋል ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
ይህንን ውሳኔ በመቃወም ሰኔ 25/2013 ዓ.ም ለሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታውን ማቅረባቸውን የቤተክርስቲያኗ የሽማግሌዎች ሰብሳቢ አቶ በፍርዱ መሰረት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክለውም የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ የሕግ ስህተት አለው በማመለቱ ነው ለችሎቱ አቤት ያሉት። እስካሁን ድረስም ይግባኝ ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም የሚል ውሳኔ አለመሰጠቱን እና ይህንን እየተጠባበቁ እንደሆነም ተናግረዋል።
የፈረንሳይ ለጋሲዮን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከተመሰረተች 26 ዓመታትን እንዳስቆጠረች እና ከ700 በላይ ቋሚ ቆራቢ አባላት እንዳሏት አቶ በፍርዱ ተናግረዋል።
አሁን ክርክር ባስነሳው ይዞታ ላይም ከ1997 ጀምሮ መንፈሳዊ ግልጋሎት እየሰጠች ትገኛለች። በዚሁ ቅርንጫፍ 260 ህጻናትን በቋሚነት እየረዳች እንደምትገኝም አቶ በፍርዱ ተናግረዋል።
የቤተ ክርስቲያኗ ድምጽ ረበሸኝ ያሉት አመልካች ከመኖሪያ ቤታቸው በ36 ሜትር ርዝመት እና በግማሽ ሜትር ርቀት ወሰን እየጨመረ የሚመጣ ድምፅ በእርሳቸው ላይ እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው ላይ ሁከት መፍጠሩን ጠቅሰው አመልክተዋል።
አመልካች ከነ ቤተሰባቸው የጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው እና ቤቱም ለመኖሪያ ቤት ግልጋሎት ብቻ እንዲውል ይወሰንልኝ ሲሉ አቤት ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ በበኩሏ ከሳሽ ጥያቄያቸውን "በማስረጃ አላስደገፉም፤ አመልካች የድምጽ ብክለት ተፈጸመ ያሉትም ደሃ ህፃናት የሚረዱበትን መርሃ ግብር ነው" ስትል በችሎት ተከራክራለች።
ጉዳት መድረሱ ባልተረጋገጠበት ካሳ መጠየቃቸው አግባብ አይደለም ስትልም ቤተ ክርስቲያኗ ሞግታለች።
የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱም ሁለቱን ካከራከረ በኋላ ይዞታው በማስተር ፕላኑ መሰረት ለመኖሪያ ቤት ይዋል የአመልካችን እና የቤተሰቡን መብት ከመንካት ተከሳሽ ይቆጠብ ብሎም ከሳሽ ለፍርድ ሂደቱ ያወጣውን ወጪ ቤተክስርቲያኗ ትመልስ ሲል ፈርዶ ነበር።
የክሱን በይግባኝ የተመለከተው ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም ቤተክርሲያኒቷ ከሳሽ ላወጣው የክስ ወጪ እና ኪሳራ 5000 ብር ትክፈል በሚል ፍርዱን ያሻሻለ ሲሆን ቀሪው የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ግን እንዲጸና ሰኔ 18/2013 ወስኗል።
አቶ በፍርዱ ቤተ ክርስቲያኗ ድምጽ እንዳይወጣ የተለያየ ሥራዎችን አከናውና ማሻሻያዎች ማድረጓን እና ማስተር ፕላኑም ቅይጥ እንጂ መኖሪያ ብቻ ባልሆነበት የተሰጠን ውሳኔ ቅር ስላስባለን አቤት ብለናል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የክስ ሂደቱ በ2009 የጀመረ ሲሆን ከሳሽ የቤተክርቲያኗን ቄስ ከሰው ነበር። በወቅቱ ችሎቱ ተቋሙን እንጂ ግለሰቡን መክሰስ አይችሉም በሚል መዝገቡን ዘግቶት ነበር። በሁለኛው ክስ የቤተ ክርስቲያኗ መሪ ናቸው የተባሉ አምስት ሰዎች ተከሰዋል።
የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከሰጠ በኋላም አንድ አመራር ለአንድ ቀን ታስረው ቆይተው ነበር። ግለሰቡ ታሰሩትም ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ግለጋሎት አልተቋረጠም በሚል ሲሆን ቤተክርስቲያኒቱ 10 ሺህ ብር በማስያዝ ግለሰቡ እንዲፈቱ እና ውሳኔው ታግዶ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤት ብላ ነበር።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም መዝገቡን ተመልክቶ የሰበር ችሎት ይግባኙን ይመለከተዋል ወይም አይመለከተውም የሚለው ላይ ውሳኔ ይሰጣል።
ቢቢሲ ከሳሽን አግኝቶ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
የኢትዯጵያ የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክስርሰቲያን በኢትዮጵያ ከተመሰረተች በርካታ ዓመታት የሆናት ሲሆን ከ10.4 ሚሊዮን በላይ ቋሚ አባላት እንዳሏት ይነገራል።
ከሐይማኖት ተቋማት ከሚወጣ ድምጽ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ወገኖች ቅሬታዎች ሲሰሙ የቆየ ቢሆንም ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት እስካሁን በድምጽ ብክለት ምክንያት እስካሁን ድረስ የተሰጠ ተመሳሳይ ፍርድ የለም።












