ምርጫ 2013፡ የኢትዮጵያን ምርጫ የሚመሩት የቀድሞዋ የፖለቲካ እስረኛ ማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
- ፀሐፊ, በሐይማኖት አሸናፊ፣
- የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ አማርኛ
በርካታ ኢትዮጵያዊያን ብርቱካን ሚደቅሳ ከሚለው ስም ጋር የተዋወቁት በ1993 ዓ.ም ለቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር እና በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባላንጣ ለነበሩት ስዬ አብረሃ የዋስትና መብት የፈቀዱ ዕለት ነው። አቶ ስዬ በወቅቱ ከስድስት የቤተሰባቸው አባላት ጋር የሙስና ክሶች ቀርቦባቸው ነበር።
ብርቱካን በዚያች ታሪካዊ ዕለት በአቶ ስዬ ችሎት ላይ የተሰየሙት መዝገቡን ይመለከቱ የነበሩት የመሃል ዳኛ በህመም ፈቃድ ላይ በመሆናቸው ነበር።
ብርቱካን እና ጓደኞቻቸው በወቅቱ በቀጥታ ከሕግ ትምህርት ቤት ወደ ረዳት ዳኝነት የመጡ የመጀመሪያዎቹ ቅጥሮች ነበሩ። እናም እነዚህ ወጣት ዳኞች በጊዜ ቀጠሮ ምክንያት ያለ አግባብ ተይዘው የሚቆዩ ሰዎችን በመልቀቅ ለፖሊስ ራስ ምታት በመሆናቸው ከምክር እስከ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸውም ነበር።
ብርቱካን ዳኛ ከሆኑ በኋላ የተመደቡበት የወንጀል ችሎት ትልልቅ መዝገቦች ይታዩባበት ስለበር በአስፈጻሚው አይን ውስጥ መግባታቸው አልቀረም። በአንድ ወቅት ፍሪደም ኮሌክሽን ለተባለ ተቋም በሰጡት ቃለ ምልልስልም የዲሲፕሊን ክስ ቀርቦባቸው እንደነበረ ብርቱካን ተናግረዋል።
"የስዬ ጉዳይ ጎልቶ የሚታይ ስለሆነ እንጂ በበርካታ መዝገቦች ሥርዓቱን የሚፈትኑ ውሳኔዎችን ሰጥታለች" ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በወቅቱ የብርቱካን የቅርብ ጓደኛ አቶ ቢኒያም* [ስማቸው የተቀየረ] ይናገራሉ።
የብርቱካን የፖለቲካ ህይወት ከ1997 ምርጫ በኋላ ከፍተኛ እውቅና ላይ ደርሶ ነበር። ነገር ግን በወቅቱ በምርጫው አልተወዳደሩም። ከፍርድ ቤት ለቀው በጥብቅና ሙያ ላይ የነበሩት ብርቱካን በተለይም ፓርቲዎቹን በማማከር ነበር ተሳትፏቸው።
ነገር ግን ቀደም ባለው የ1992ቱ ምርጫ በግላቸው ተወዳድረው ነበር። በዚህም በገዢው ፓርቲ ተሸንፈዋል። በወቅቱ ታዋቂ የምክር ቤት አባል የነበሩትን ሻለቃ አድማሴን ማለፋቸውን ተከትሎ እሳቸውን ለመተካት የተወዳደሩት ብርቱካን ዋና አጀንዳቸው ሙስናን ማጥፋት እንደነበረም የቅርብ ወዳጃቸው ይናገራሉ።
"ብርቱካን በፈረንሳይ አካባቢ በጣም ታዋቂ ነበረች። ነገር ግን የተወዳደረችበት የምርጫ ክልል በጣም ሰፊ ነበር። የምርጫ ምልክቷም የሻለቃ አድማሴ ምልክት የነበረው ጭራ ነበር" ሲሉ አቶ ቢኒያም ያስታውሳሉ።
ሻለቃ አድማሴ የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ጨምሮ የፓርላማ አባላትን በሚያስፈግጉ ቀልዶቻቸው የሚታወቁ እና መንግሥትን መቃወም የማይፈሩ የፓርላማ አባል ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ብርቱካን በ1997 በፕሮፌሰር መስፍን የተመሰረተው የቀስተ ዳመና ፓርቲ አባል የነበሩ ሲሆን፤ ቅንጅትን የተቀላቀሉት በግንቦት ወር ከተካሄደው አወዛጋቢ ምርጫ በኋላ ነበር።
ጥምረቱን ከተቀላቀሉ ሦስት ወር ሳይሞላቸው ነበር ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው የተመረጡት። 'ተቀዳሚ' የምትለው ቃል ምክንያት በቅንጅት አመራሮች መካከል መቃረን ተፈጥሮ እንደነበር ይነገራል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በዚህ ምርጫ ላይ በእንግድነት መታደማቸውን ያስታውሳሉ። በእርግጥ ብርቱካንን የሚያውቋቸው ከ21 ዓመት በፊት በግላቸው ሲወዳደሩ ነበር።
"በደርግ ጊዜ ከነበረው ቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር በኋላ ሴቶች 'እሳት እና ፖለቲካን በሩቁ' ብለው ከፖለተካ ሲሸሹ ነበር። ከዚያ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ሆነው ወደፊት ከመጡ ሴቶች አንዷ መሆኗ ይታወቃል" ሲሉ መረራ ወቅቱን ያስታወሳሉ። "ብርቱካን ጥሩ ሙከራ ማድረጓን አውቃለሁ።"
በቅንጅት አመራርነት ከተመረጡ ሁለት ወር ሳይሞላ ወደ እስር የሄዱት ብርቱካን "ከፍተኛ የአመራር ተግባር ያከናወኑት በእስር ላይ ሆነው ነበር" ሲሉ ሂደቱን በቅርብ የተከታተሉ ወዳጆቻቸው ይናገራሉ።
በልጃቸው እስር ክፉኛ የተንገላቱት ወላጅ እናታቸው አልማዝ ገብረእግዚአብሔር በተለይም በልጃቸው እስር ወቅት በመገናኛ ብዙሃን ብቅ በማለታቸው ብዙዎች ያውቋቸዋል።
ብርቱካን የመጀመሪያ ስማቸው ቤተልሔም ነበር። እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ በዚህ ስም ተጠርተዋል። በኋላ ወላጅ አባታቸው ህልም ማየታቸውን ጠቅሰው ብርቱካን ሲሉ የልጃቸውን ስም ቀየሩ።
ከእስር ባሻገር በልጃቸው ስደት የተጎዱት እናት ብርቱካንን አገሯ ላይ ለማየት በእጅጉ ጓግተው ነበር "እኔ ሁለት ጊዜ ሄጄ አይቻት መጣሁ፤ አሁን ልምጣና ልይሽ ስትለኝ ሳልሞት ልጄን ላያት ነው ብዬ በጣም ተደሰትኩኝ። እግዚአብሔርም ከተፍ አደረጋት ተመስገን" ሲሉ ብርቱካን ወደ አገር ቤት ጠቅልላ መመለሷን ተከትሎ ለቢቢሲ የሰጡት አስተያየታቸው ነበር።
ብርቱካን ወደ አገሯ ከመመለሳቸው ባሻገር በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ላይ ጉልህ ሚና ባለው ተቋም ውስጥ ቁልፍ ኃላፊነትን መያዛቸውን ለመመልከት የበቁት እናታቸው ያረፉት ከምርጫው ከጥቂት ወራት በፊት ነበር።
ጉዞ ወደ ቃሊቲ
በቅንጅት አመራሮች እና በገዢው ፓርቲ መካከል በነበረው መካረር ምናልባት ወደ እስር ሊያመራ እንደሚችል በመረዳት ሕቡዕ ተተኪ የአመራር ቡድን መስርተው ነበር።
ይህ ቡድን አመራሮቹ ከታሰሩ በጥቂት ወራት ውስጥ በመንግሥት ታድኖ ወደ እስር ተጋዘ። የዚህን መዋቅር መፍረስ ተከትሎም ኪክ (Kinijit International Council (KIC) የተሰኘ አዲስ የህቡዕ መዋቅር በመላው ዓለም ያለውን ዳያስፖራ ባማከለ መልኩ ተደራጀ። ይህ የሆነው ማረሚያ ቤት ባሉት አመራሮች መሪነት ነበረ።
"በአብዛኛው ውሳኔዎች የሚሰጡት ወደ ችሎት ሲሄዱ ነበር" ሲሉ አቶ ቢኒያም ይናገራሉ። በመቀጠልም 13 ሰዎች ያሉበት የአመራር ቡደን ተመርጦ ኪክን መምራት ጀመረ።
ነገር ግን በቅንጅት አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በፈጠረው ክፍፍል ኪል (Kinijit International Leadership, KIL) የተሰኘ አዲስ መዋቅር ተፈጠረ።
ኪክ በፕሮፌሰር ብርሃኑ ኪል ደግሞ በኢንጂነር ኃይሉ ሻወል ይመሩ የነበር ሲሆን በውጪ ሁለቱም የተለያዩ መሪዎች ነበሯቸው።
የብርቱካን የአመራር ሚና የሚመጣው እዚህ ጋር እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ቢኒያም፤ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የነበረውን ክፍፍል በማጥበብ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ይናገራሉ።
ከመንግሥት ጋር ተደራድሮ ከእስር የመውጣት ጉዳይ ሲመጣም ብርቱካን ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።
"አንደኛው ጓደኛሽ ምን እንዳለ አታውቂም፤ በዛ ላይ እስር ላይ ስትሆኚ የሚፈጠር የራሱ ውዝግብ አለ፤ ስለዚህ ቀመድሽ ተነጋግረሽ አቋም መያዝ አስፈላጊ ነበር። በዚህ ላይ የብርቱካን ሚና ከፍተኛ ነበር" ሲሉ ያስታውሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሞት ፍርድ
የቅንጅት አመራሮች በተለይም ከመንግሥት ጋር በሚደረገው ድርድር ወጥ እና ተመሳሳይ አቋም ይዘው መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ ቢኒያም ይህ በድንገት የክስ ዝርዝሮች ተቀይረው የሞት ፍርድ የያዙ አንቀጾች እስከሚጠቀሱ ድረስ የቀጠለ መሆኑን ያስታውሳሉ።
በእስረኞቹ ላይ የሞት ፍርድ የጠየቁት ዐቃቤ ሕግም አዲስ ይሁኑ እንጂ ለተከሳሾች ግን እንግዳ አልነበሩም። አቶ ሽመልስ ከማል በተለይም ከአሁኑ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እና ከብርቱካን ሚደቅሳ ጋር የቅርብ ጓደኛ ነበሩ። እንዲያውም ከዳንኤል ጋር አንድ ቤት በጋራ የኖሩ የልብ ወዳጆችም ነበሩ።
በወቅቱ በችሎት ውስጥ የነበረውን ሁኔታ የሚያስታውሱት አቶ ቢኒያም "ክስትቱ ትዕይንታዊ ነበር" ሲሉ በተከሳሾች ፊት ላይ የሚነበበውን ስሜት ገልጸውታል። "ሽመልስ ጓደኞቹ የመረጡት የርዕዮተ ዓለም መንገድን እንደ ክህደት ይቆጥረው ነበር" ሲሉም ያስታውሳሉ።
የሞት ፍርድ ወደ ጠረጴዛው መምጣቱ በድርድር ሂደቱ ላይ የራሱን ጫና አሳድሮ የተወሰኑ አመራሮች ይቅርታ አንጠይቅም ብለው ቢቆዩም ብርቱካንን ጨምሮ 38ቱም በይቅርታ ተፈቱ።
ሁለተኛው እስር
የብርቱካንን ሁለተኛ እስር ከመጀመሪያው ይቅርታ ጋር ነጥሎ መመልከት አይቻልም። ወደ ስዊድን አገር ባመሩበት ወቅት ለተሰበሰበው ዳያስፖራ ያስተላለፉት መልዕክት አዲስ አበባ ደርሶ ለ21 ወራት ለቆየ እስር ዳረጋቸው።
የብርቱካን ሁለተኛው እስር እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ በተደጋጋሚ በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች ላይ ተገልጿል። የመብት ተሟጋች ድርጅቶችም ለሁለት ወር ለብቻቸው ተነጥለው መታሰራቸውን ይፋ አድርገው ነበር።
አሁን የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ በወቅቱ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነበሩ።
ኮሚሽነሩ ብርቱካን ወደ አገር ከተመለሱ በኋላ ፖሊሶች ወደ ቤታቸው ልከው እንዳስጠሯቸው 'አዲስ ነገር' በተሰኘው በወቅቱ እጅግ ታዋቂ በነበረ ጋዜጣ ላይ በፃፉት "ቃሌ" የተሰኘ ጽሁፋቸው ላይ ያስዳስሳሉ።
ኮሚሽነሩ ለሁለተኛ ግዜ ታኅሣሥ 14/2001 ብርቱካንን በድጋሚ ጠርጠው የ72 ሰዓታት የማስተባበያ ገደብ መስጠታቸውን ተክትሎ ነበር 'ቃሌ' የሚለውን ፅሁፋቸውን ያኖሩት።
"በስዊድኑ ንግግር ይቅርታ አልጠየኩም የሚል መልዕክት አስተላልፈሻል እርሱን አስተባብዪ" የሚል ነበር ትዕዛዙ። ይህንን የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ አስተጋብተውታል።
'ቃሌ' በተሰኘው ጽሁፋቸውም "ምን አልባት ይህ የመጨረሻ ቃሌ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ነበር ያሰፈሩት። በዚህ ጽሁፋቸው የይቅርታ የሕግ ሂደትን በማንሳት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ብሎም የፖሊስ ኮሚሽነሩን ሕጋዊ ስልጣንን ጠየቁ። ይህ ጽሁፋቸው ከመልስ ይልቅ ጥያቄዎች ተስጋቡበት።
"ይህ የኔ አነጋገር የተዛባ ነው ቢባልስ ፖሊስ ጣቢያ በመጥሪያም ያለመጥሪያም ለመመላለስ ያበቃል? በፍፁም። ያስጠይቃል ቢባልስ በአገሪቱ ፕሬዘዳንት የተሰጠ ይቅርታ የሚያስነሳው እንዴት ይሆን? ይቅርታን የሚያስነሳስ ቢሆን የፌደራል ፖሊስ በየትኛው ስልጣኑ ነው በጉዳዩ ላይ ምርመራ የሚያደርገው? ማስጠንቀቂያስ የሚሰጠው?" ሲል ጽሁፋቸው ተነበበ።
የተሰጣቸው 72 ሰዓት ሳይጠናቀቅ ብርቱካን ታሰሩ፤ ታስረውም ሁለት ዓመት የሚጠጋ ጊዜ ቆዩ። በድጋሚ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ባለሁለት ገጽ የይቅርታ ደብዳቤ ብርቱካን ከእስር ተለቀቁ። ሁለተኛው ይቅርታቸውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ማረሚያ ቤት ድረስ ሄዶ ነጭ ሹራባቸውን አጥልቀው ባደረገላቸው ቃለ መጠይቅ የተደገፈ ነበር።
ብርቱካን ከቅንጅት መከፋፈል በኋላ ተመሳሳይ ዕጣ የገጠመውን አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲን ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በ2001 ዓ.ም መስርተው ለአጭር ጊዜ በአመራርነት መሥራታቸው አይዘነጋም።
ብርቱካን ከእሰር ከተፈቱ በኋላ ኑሯቸውን በአሜሪካ አድርገው ነበር። ቆይታቸውም በሃርቫርድ የኬኔዲ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ። እዲሁም ብሔራዊ የዴሞክራሲ ተቋም በሆነው ኔድ ውስጥም ለዓመታት ሰሩ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ እጣ ፈንታ የልብ ምት
ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በሕዝብ አመፅ አማካኝነት የኢሕአዴግ የስልጣን ወንበር መነቃነቁን ተከትሎ ከመጣው ለውጥ በኋላ መደረጉ ብዙ ግምት አሰጥቶት ነበር። በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተራዘመው ምርጫ በተለየ አውድ ውስጥ ይካሄዳል።
ከአምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ማግስት የተነሳው የሕዝብ አመፅ ማዕከል የነበረው የኦሮሚያ ክልል ከተጠበቀው ያነሰ ፉክክር ይካሄድበታል።
ትግራይ ክልል የምርጫውን መራዘም ባለመቀበል ምርጫ አካሂዶ ነበር። የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የገባበት ውጥረት ወደ ጦርነት ተሸጋግሮ የሺዎችን ነፍስ የቀጠፈ፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለው ግጭት በመቀጠሉ ምርጫው በትግራይ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል።
በሶማሌ ክልል በመራጮች ምዝገባ ላይ በታየው ችግር ምክንያት ምርጫው ለሁለት ወራት ተራዝሟል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላቶቻችን ታስረዋል ጽህፈት ቤቶቻችን ተዘግተዋል ሲሉ ሰንብተዋል።
በአትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ዕጩዎች እስር ቤት ሆነው ምርጫውን ይወዳደራሉ። በዚህም የባልደራስ ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋን ጨምሮ አራት ዕጩዎች ይመዝገቡልኝ ሲል ቦርዱን ፍርድ ቤት የወሰደው ፓርቲው በመጨረሻ አሸንፏል።
የሕግ ምሁር የሆኑት መሰንበት አሰፋ (ዶ/ር) እንደሚሉት ቦርዱ በውጣ ውረድ ውስጥ ቢሆንም የማይናቁ ተግባራትን እያከናወነ ነው። የቦርዱ ሰብሳቢም በሂደቱ ላሳዩት አመራር ሊመሰገኑ ይገባል የሚታዩት ችግሮችም ከቦርዱ ጋር ብቻ መያያዝ የለባቸውም ይላሉ።
"ችግሮቹን የፈጠሯቸው ቦርዱ ወይም መንግሥት አይደሉም። ፓርቲዎች በርዕዮተ ዓለም እና በሃሳብ ላይ የተመሰረተ ንግግር ማድረግ እንጂ ነፃ አውጪ ግንባርን ተጠቅመው መንግሥትን ለመቀየር መታገል የለባቸውም" ሲሉ ይተቻሉ።
"አንዳንዴ የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያ ችግር መልካም አመራርን አናበረታታም፤ ሁሌም ምዕራባዊያን ከፖለቲካ ቀውሶቻችን እንዲያድኑን መጠበቅ የለብንም" ሲሉ የቦርዱን መሪ እያሳዩ ላለው አመራር ይናገራሉ።
"ብርቱካን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲመጣ ያላትን ጥማት የሚያስረዳ የኋላ ታሪክ አላት" ሲሉ መሰንበት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"አንዳንዴ ግምቶቻችንን ማስተካከል ይገባናል፤ ብርቱካን ስልጣኑን ሲረከቡ አገሪቱ በርካታ ችግሮች ነበሩባት። የተወሰኑት ችግሮችም ከቦርዱ ጋር አይገናኙም" ሲሉ ያክላሉ።
የኦፌኮ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ በበኩላቸው "የሰብሳቢዋን ብሎም የሌሎች የቦርዱን አባላት የአሿሿም ሂደት ላይ ተቃውሞ አሰምቻለሁ" ይላሉ።
"ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው ጠርተው ስለ አራቱ የቦርድ አባላት ምርጫ አስተያየት ጠየቁን፤ እኔ ሦስቱን ነው የማውቀው፤ ማወቅ ብቻ፤ ቢያስ 24 ሰዓት ይስጡን እና የጀርባ ታሪካቸውን አጥንተን እንመለስ አልኩ። አሻፈረኝ አሉ። ተቃውሞዬን መዝግብልኝ ብዬ አስመዝግቤአለሁ" ሲሉ መረራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ምንም እንኳን የቦርዱ ሰብሳቢ ምርጫ ጉዳይን በተመለከተ ሃሳባቸውን ባይጠየቁም የአመራረጥ ሂደቱ ላይ ቅሬታቸውን የገለፁት መረራ እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ ተቃዋሚዎች ከሹመቱ በኋላ በሰብሳቢዋ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ አላሰሙም። ይሄም ከነበራቸው የተቃውሞ ፖለቲካ ልምድ አንጻር የተቃዋሚዎችን ችግር ይረዳሉ በሚል እንደነበረ ያብራራሉ።
"በአሁን ሰዓት ብርቱካን ወጥመድ ውስጥ ገብታለች። እኛ ለገዢው ፓርቲ አዳልተሻል እንላለን፤ ከዚያ ደግሞ ራሱ ገዢው ፓርቲ አለ እንዲሁም ገዢውን ፓርቲ የሚደግፉ ፓርቲዎች አሉ፤ በዚህ መሃል አጣብቂኝ ውስጥ ያለች ይመስለኛል። እንግዲህ ከዚህ ውስጥ መውጣት የራሷ ኃላፊነት ነው" ይላሉ ፕሮፌሰር መረራ።
በብርቱካን መሪነት የሚካሄደውን ምርጫ ካለፈው ጋር የሚያነጻጽሩት መረራ "ከዚህ ቀደም እኮ ፊክሺየስ (የውሸት) የምርጫ ጣቢያ አይተን አናውቅም። ይሄ የኦሮሚያ ጫካ ውስጥ አይደለም፤ አዲስ አበባ ነው የሆነው። የሶማሌ ክልል ዕጩ ጅግጅጋ መመዝገብ ስላልተቻለ አዲስ አበባ እኮ ነው የተመዘገቡት። የቀድሞዎቹ ይሰርቃሉ፤ ግን ደሞ የምርጫ ትርጉም ይገባቸዋል" ይላሉ።
በኦሮሚያ ገዢው ፓርቲ ያለ ጠንካራ ተፎካካሪ መወዳደሩ፤ በሶማሌ ምርጫው በጊዜው ማካሄድ ያለመቻሉ ብሎም ትግራይ በጦርነት ውስጥ ሆና አለመምረጧን በመጥቀስ "ምርጫው በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ እኮ ነው የሚደረገው" ሲሉ ይሞግታሉ።
ነገሮች ከቦርዱ አቅም በላይ ሆነዋል ብለው የሚያምኑት መረራ ለዚህ በዋናነት መወቀስ ያለባቸው "መንግሥት እና ገዢውን ፓርቲ ባላስፈላጊ አቅጣጫ የሚመሩ ፓርቲዎች ናቸው" ይላሉ።
"በግለሰብ ደረጃ ብርቱካን በታሪክ ሚዛን ላይ መቀመጥ አይቀርላቸውም፤ ውጤቱ የሚመዘነው ደግሞ ይሄ ምርጫ በሚያመጣው ውጤት ነው። ይሄ ምርጫም ሦስት ታሪካዊ ፈተናዎች አሉበት" ሲሉ መረራ ይናገራሉ።
"ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ያመጣል ወይ፣ በኢትዮጵያ የ3000 ዘመን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከዚህ ምርጫ ትወለዳለች፣ አትወለድም እና ሕዝቡ ባለው አቅም ፊቱን እውነተኛ ትርጉም ወዳለው ልማት እና ብልጽግና ያዞራል ወይ?" የሚሉት የምርጫውንም የሰብሳቢዋንም ውጤት ይለካሉ ሲሉ ይደመድማሉ።

















