ወደ ትግራይ የሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎችን በተመለከተ መመሪያ ይፋ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሠሜናዊ ኢትዮጵያ ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎች አዲስ አበባ ሊያርፉ እንደሚገባና ፍተሻም እንደሚደረግባቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ገለጸ።
የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ ወደ ትግራይ የሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎችን በተመለከተ ዛሬው ሐምሌ 2/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ነው መመሪያው ይፋ የተደረገው።
በትግራይ ክልል ከግንቦት 22/2013 ዓ.ም ጀምሮ ምንም አይነት በረራዎች እንዳይኖሩ ቢከለከልም መንግሥት ከሰሞኑ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ለሚፈልጉ ሁሉ ልዩ ፈቃድ እንደሚሰጥና በረራዎችም ከሰኔ 28/2013 ዓ.ም እንደሚጀመሩ ተገልጿል።
በረራዎች ፈቃድ ቢሰጥም የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን እስካሁን ድረስ በረራ አለመጀመሩን አስታውቆ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት በልዩ ሁኔታ የፈቀደውን የሰብዓዊ እርዳታ በረራ አለመከልከሉንና በአሁኑም ወቅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም መንገደኞችን ወደ ትግራይ ክልል ለማጓጓዝ ሁለት በረራዎች እንዲፈቀዱለት መጠየቁን ተገልጿል።
እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎችን በተሻለ ለማመቻቸት የፌደራል መንግሥቱ የሰብዓዊ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ፈቃድ ለማግኘት በጥብቅ መከተል ያለባቸውን መመሪያዎችንና መረጃዎችን የያዘ ዝርዝር አውጥቷል።
በዚህም መሰረት ከውጭ ወይም ከአገር ውስጥ አየር ማረፊያዎች የሚመጡ በረራዎች ሁሉ ወደ ትግራይ ከመሄዳቸው በፊት በመጀመሪያ በአዲስ አበባ አየር ማረፊያ ማረፍ እንዳለባቸው ተቀምጧል።
ከተከለከለው የአየር ክልል የሚመጡ በረራዎች እንዲሁ ወደ ውጭ ከመሄዳቸው በፊትም ሆነ በአገር ውስጥ አየር ማረፊያዎች ከመሄዳቸው በፊት በአዲስ አበባ አየር ማረፊያ ሊያልፉ እንደሚገባም ተገልጿል።
በመመሪያው ውስጥ በዝርዝር እንደተገለፀው በረራዎች ከመከናወናቸው በፊት እንደ የበረራ ቁጥር፣ የአውሮፕላኑን ዓይነት፣ የበረራ ዓላማ፣ የተሳፋሪዎች ዝርዝር እና የጭነት ዓይነት ዝርዝር መረጃዎችን ማቅረብና ማረጋገጫ ማግኘት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚነሱ እና በሚመጡት አውሮፕላኖች፣ በካርጎዎች፣ በተሳፋሪዎች፣ በሠራተኞች ፍተሻና ምርመራ እንደሚደረግም በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።
እንዲሁም ግዙፍ ካርጎዎችንም በተመለከተ መከፈት የሚያስፈልጋቸውም ከሆነ ይህም ተግባራዊ እንደሚሆንና መደበኛና ደረጃውን የጠበቀ ፍተሻ ይደረጋል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የፌደራል መንግሥቱ ሁሉም የመንገደኞች እና የጭነት አውሮፕላን በረራዎች ከሰብዓዊ እርዳታ ተልዕኮዎች ጋር ብቻ የተገናኙ ሰዎችን ወይም ቁሶችን ብቻ እንዲጭኑም ጠይቋል።
የፌደራል መንግሥቱ ከሰብዓዊ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ፈቃደኛ ቢሆንም "አንዳንድ ዘገባዎች በስህተትም ይሁን በሌላ መንገድ ወደ ትግራይ የሚገቡ በረራዎችን መንግሥት እያስተጓጓለ ያለ ይመስል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ ነው" ሲልም አንዳንድ ድርጅቶችን ከሷል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) አገሪቷ ከአውሮፓ 1986 ጀምሮ ከድርጅቱ ጋር ከገነባችው ፍሬያማ ግንኙነት ጋር የማይመጣጠኑ ተግባራትን እየፈፀመ ነው ሲልም ለተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ደብዳቤ መላኩም ተገልጿል።
የፌደራል መንግሥቱ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) የትግራይ ክልልን በተመለከተ "የተሳሳቱ ዘገባዎችና መግለጫዎችን" እያቀረበ እንደሆነና ይህም አጋዥና ገንቢ አይደለምም ሲል ወቅሷል።












