በሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጥፋተኛ የተባለው ጥላሁን ያሚ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ሕግ ጠየቀ

አርቲስ ሃጫሉ ሁንዴሳ

የፎቶው ባለመብት, BBC/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አርቲስ ሃጫሉ ሁንዴሳ

በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጥፋተኛ የተባለው ጥላሁን ያሚ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ሕግ ጠየቀ።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምደብ ችሎት ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎት በአርቲስቱ ግድያ ጥፋተኛ ያላቸው ተከሳሾች ላይ የቅጣት አስተያየት ለመስማት ለዛሬ ቀጠሮ ይዞ ነበር።

በዛሬው ውሎም ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉት ተከሳሾች ማለትም፤ ጥላሁን ያሚ፣ ከበደ ገመቹ እና አብዲ አለማየሁ ችሎት ፊት ቀርበዋል።

ዐቃቤ ሕግ ጥፋተኛ በተባሉት ተከሳሾች ላይ የቅጣት አስተያየቱን በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበ ሲሆን፤ የተከሳሾች ተከላከካይ ጠበቃ ደግሞ በ1996 በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነ ስርዓት አንቀጽ 82/1/ሀ መሠረት ቅጣቱ እንዲቀልላቸው ጠይቋል።

አንቀጽ 82/1/ሀ አንድ ጥፋተኛ የተባለ ተከሳሽ ከዚህ ቀደም መልካም ስነ ምግባር ያለው ከነበረ እና ወንጀሉንም ሆነ ብሎ አለመፈጸሙ ከተረጋገጠ ቅጣቱ ይቀልለታል ይላል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ለሶስተኛ ተከሳሽ አብዲ አለማየሁ ካልሆነ በስተቀር ለ1ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ እና ለ2ኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ የቅጣት ማቅለል ሃሳብ ላይ አልስማምም ብሏል።

ዐቃቤ ሕግ 1ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ "ከዚህ ቀደም ጥሩ ስነ ምግባር ያለው አይደለም" ያለ ሲሆን፤ 2012 ዓ.ም. ላይ በሁለት መዝገቦች ክስ ተመስርቶበት እንደነበረ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

1ኛ ተከሳሽ ከዚህ ቀደም በስርቆት እና በባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ ዘረፋ ክስ ተመስርቶበት እንደነበረ ለፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ አስረድቷል።

ከዚህ በተጨማሪም 1ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ "ሕግን በተጻረረ መልኩ መዝናኛ ቦታ ላይ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ ይገባ ነበር" ብሏል ዐቃቤ ሕግ።

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ለመግደል አስቦ ወንጀሉን በመፈጸሙ 1ኛ ተከሳሽ ላይ የቅጣት ማቅለያ ሊደረግለት አይገባም በማለት ጥላሁን ያሚ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ሕግ ጠይቋል።

የተከሳሾች ተከላካይ ጠበቃ በበኩሉ ዐቃቤ ሕግ የጠቀሳቸው1ኛ ተከሳሽ ከዚህ ቀደም የተመሰረቱበት ሁለት ክሶች ውሳኔ ስላልተሰጠባቸው 1ኛ ተከሳሽ ጥፋተኛ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ ነጻ ሆኖ የመታየት መብት የሚጋፋ ነው ሲል ተከራክሯል።

2ኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹን በተመለከተ፤ ዐቃቤ ሕግ 2ኛ ተከሳሽ በሕገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ መግዛቱን፤ የገዛውን ጦር መሳሪያም ለጥላሁን ያሚ አውሶት ጦር መሳሪያው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ለመግደል ጥቅም ላይ መዋሉን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

2ኛ ተከሳሽ ከጸጥታ ኃይሎች ለመደበቅ ሙከራ ሲያደርግ ቆይቶ አደዓ ድሬ የተባለ ቦታ በቁጥጥር ሥር መዋሉን በመጥቀስ ዐቃቤ ሕግ የቅጣት ማቅለያውን ተከራክሯል።

በዚህም ምክንያት 2ኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ ጥፋተኛ በተባለበት ወንጀል አንቀጽ ቅጣቱን እንዲቀበል ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የተከሳሾች ተከላካይ ጠበቃ 2ኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ የቀረበበት ሪከርድ ሳይኖር 'የቀድሞ ባህሪው መልካም አልነበረም' ማለት ስለማይቻል የቅጣት ማቅለያ ሃሳቡ ተቀባይነት እንዲያገኝ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ እና የተከሳሽ ጠበቆች የቅጣት አስተያየትን ሰምቶ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 20/ 2013 ቀጠሮ ሰጥቷል።