ህወሓት ኃይሎቹ ወደ ትግራይ እንዲመለሱ ማዘዙን ለተመድ በደብዳቤ ገለጸ

የህወሓት ተዋጊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ህወሓት በሊቀመንበሩ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በኩል ለተባበሩት መንግሥታት በጻፈው ደብዳቤ ኃይሎቹ ወደ ትግራይ ክልል እንዲመለሱ ማዘዙን ገለጸ።

የህወሓት ኃይሎች ካለፈው ዓመት ሰኔ ወዲህ ከትግራይ ክልል ባሻገር ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በመግባት በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረው ውጊያ ሲደረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

ኅዳር ላይ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊቱን፣ የክልል ልዩ ኃይሎችንና ሚሊሻዎችን በማቀናጀት ባካሄደው መጠነ ሰፊ ዘመቻ በርካታ አካባቢዎችን መልሶ ለመቆጣጠር ችሏል።

በህወሓት መሪዎች በኩል ግን ኃይሎቻቸው እንዲወጡ የተደረገው "በስልታዊ ውሳኔ" መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የሆኑት ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ለቢቢሲ "አማጺው ሽንፈት ገጥሞት" ይዟቸው ከነበሩ ቦታዎች እንዲወጣ መደረጉን ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማን ጨምሮ በርካታ የሰሜን ወሎ አካባቢዎችን ከአማጺያኑ ስር በማውጣት መቆጣጠሩን መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን፤ የቀሩ አካባቢዎችን መልሶ ለመያዝ ዘመቻው እንደቀጠለ በተነገረበት ጊዜ ነው የህወሓት ሊቀ መንበር ደብዳቤ መጻፋቸው የተሰማው።

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ለመንግሥታቱ ድርጅት ትናንት እሁድ ታኅሣሥ 10/2014 ዓ. ም. ጻፉት በተባለው ደብዳቤ ላይ ኃይሎቻቸው ከትግራይ ክልል ውጪ ከነበሩባቸው አካባቢዎች "ለሰላም ዕድል ለመስጠት" ለቀው እንዲወጡ ማዘዛቸውን አመልክተዋል።

ይህም ውሳኔ "ወዲያው ተግባራዊ" እንደሚሆን በደብዳቤያቸው ላይ አመልክተው፤ በአስቸኳይ ግጭቶች ቆመው ድርድር እንዲጀመር ጠይቀዋል።

ደብረጽዮን (ዶ/ር) በደብዳቤያቸው ላይ በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሲቪል አገልግሎትና ለእርዳታ አቅርቦት ከሚደረጉ በረራዎች ውጪ ትግራይ ከበረራ ነጻ የሆነ ክልል እንዲደረግ እንዲሁም በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል።

ከህወሓት በኩል ተጻፈ ስለተባለው ደብዳቤ ከተባበሩት መንግሥታትም ሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ይህ ደብዳቤ በደብረጽዮን (ዶ/ር) ለመንግሥታቱ ድርጅት እንደተጻፈ የተነገረው የመንግሥት ሠራዊት በወሰደው መጠነ ሰፊ የማጥቃት እርምጃ የህወሓት ኃይሎች ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ ሲያደርጉ የነበረው ግስጋሴ ተገትቶ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በርካታ ቦታዎችን መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ ነው።

ካለፈው ዓመት ሐምሌ ጀምሮ በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ለማስለቀቅ የአገሪቱ ሠራዊት ከክልል ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ባካሄዳቸው ዘመቻዎች ትላልቅ ከተሞችንና በርካታ ቦታዎችን ከአማጺያኑ በማስለቀቅ ሰሜን ሸዋን፣ ደቡብ ወሎንና ሰሜን ወሎን በቁጥጥሩ ስር ማስገባቱን መንግሥት ማስታወቁ አይዘነጋም።

ነገር ግን ደብረጽዮን (ዶ/ር) ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጻፉት በተባለው ደብዳቤ ላይ ኃይሎቻቸው "ከነሙሉ አቅማቸው" መሆናቸውንና ሽንፈትም እንዳልገጠማቸው ጠቅሰዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ላይ ተጀምሮ ትግራይ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ሰኔ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ሲያስወጣ፣ ህወሓት ተኩስ ለማቆም ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ወደ አጎራባች ክልሎች ተዋጊዎቹን ማስማራቱ ይታወሳል።

የህወሓት ኃይሎች በአማራ እና አፋር ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር እስከ ሰሜን ሸዋ ለመድረስ ችለው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በኅዳር ወር የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት፣ ከአፋርና ከአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ሚሊሻዎች ጋር በመቀናጀት ባካሄዱት የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የህወሓት ኃይሎችን ከአፋር ክልል ሙሉ ለሙሉ እንዲሁም ከአብዛኛው የአማራ ክልል ለማስወጣት ችለዋል።

ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ጦርነት እንዲያበቃ በርካታ አገራት፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ድርድር እንዲጀመር በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቢቆዩም እስካሁን ምንም አይነት ውጤት አልታየም።

በተለይም የአፍሪካ ሕብረት የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሰንጆን እንዲሁም አሜሪካ ታዋቂውን ዲፕሎማቷን ጄፍሪ ፌልትማንን በማሰማራት ሰላም እንዲወርድ ጥረት ቢያደርጉም ስኬት ሳይገኝ ጦርነቱ ቀጥሏል።