ተመድ በኢትዮጵያ ስላለው የሰላም ሂደትና የትግራይና የአማራ ክልሎች ጉብኝት

የፎቶው ባለመብት, UN/GETTY
ለአስራ አምስት ወራት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ ወገኖች በቅርቡ ለሰላም ያሳዩትን እርምጃ በበጎ እንደሚያዩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ገለጹ።
ዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይህንን ያሉት ትናንት ሰኞ ጥር 30/2014 ዓ.ም ሲሆን ከዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነት ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን ቀጠናውም ላይ ተፅእኖ አሳርፏል ብለዋል።
ሰላም ለማስፈን ወሳኝ እርምጃ ግጭቱን እንዲሁም ተኩስ ማቆም እንደሆነ የተናገሩት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተፋላሚ ወገኖች ይህንን እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሰፊው ቀጠናም መረጋጋት አደጋ ላይ መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም በግጭቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም አካላት ለተቸገሩ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እንዲቻል እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ አገራዊ እና ዓለም አቀፍ ጥረቶችን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከዚህ ቀደምም ጦርነቱን ለማብቃትና ሰላም ለማውረድ የሚያስችል የሚታይ ጥረት እየተደረገ መሆኑ እንዳስደሰታቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
ዋና ፀሐፊው የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ከሆኑት ከኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት እያደረጉት ስላላው ጥረት ከሕብረቱ ተወካይ መረዳታቸውን በወቅቱ አስታውቀው ነበር።
ዋና ፀሐፊው ባለፈው ቅዳሜ ለ35ኛው አፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የቪዲዮ መልዕክት የላኩ ሲሆን በዚህም በአፍሪካ ሕብረት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መካከል ያለው ትብብር ከምንጊዜውም በላይ ጠንካራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በንግግራቸው "ዓለም በአስጨናቂ ጊዜ ውስጥ ናት" ያሉት ዋና ፀሐፊው ኢ-ፍትሃዊነት በዓለም አቀፍ ሥርዓቶች መስፈንና በዚህም አፍሪካውያን ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው ብለዋል።
የትጥቅ ግጭቶች፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ውጥረቶች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት፣ ሽብርተኝነት፣ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች አህጉሪቷን እያላጓት እንደሚገኙም በቪዲዮ በላኩት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የተመድ ጉብኝት በአማራና በትግራይ ክልሎች
በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ዋና ፀሐፊውን በመወከል የመንግሥታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ የተገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በጦርነቱ የተጎዱ የአማራና የትግራይ ክልል ከተሞችን ጎብኝተዋል። እንዲሁም ከክልል አመራሮች ጋር ተገናኝተዋል።
ምክትል ዋና ፀሐፊዋ አሚና ባለፈው እሁድ ጥር 29/2014 ዓ.ም ጉብኝታቸውን የጀመሩት በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ሲሆን ጦርነቱ በሕዝቡ በተለይም በሴቶችና በህፃናት ላይ ያደረሰውን አስከፊ ጉዳት ማየታቸውን ከተመድ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
በሆስፒታሎች፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በገበያ ስፍራዎች እና በሌሎችም አካባቢዎች ላይ የደረሰውን ዘረፋ እና ውድመት የተመለከቱ ሲሆን የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትንም አግኝተዋል።
ምክትል ዋና ፀሐፊዋ ከኮምቦልቻ ጉብኝታቸው በኋላ ጦርነቱ ብዙ ያስከፈለ መሆኑን ገልጸው ሰላም ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል "የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰላም እንዲያገኝ መርዳት አለብን" ሲሉም ተናግረዋል።
አሚና በመቀጠልም ወደ ትግራይ ክልል መዲና መቀለ ያቀኑ ሲሆን በመቀለም ጉብኝታቸው እንዲሁ ጦርነቱ በሴቶችና በህፃናት ላይ ያደረሰውን አስከፊ ገፅታ ተመልክተዋል።
ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንዲሁም ለኢትዮጵያውን የሚያመጣውን እፎይታን በተመለከተ ከትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) መወያየታቸው ሰፍሯል።
ምክትል ፀሐፊዋ በተመድ የሚደገፈውንና ከወሲባዊ ጥቃት የተረፉ ሴቶችን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚያደርገውን የአይደር ሆስፒታልን ጎብኝተዋል ።
"በግጭት ውስጥ አሸናፊዎች እንደሌሉ" በመጥቀስ ወሲባዊ ጥቃት የተረፉ ሴቶቹ ታሪኮች ሊነገሩ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ምክትል ዋና ፀሐፊዋ በክልሎቹ ከሴቶችና ተማሪዎች ጋር ባደረጉት ቆይታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወሲባዊ እንዲሁም ፆታን መሰረት ላደረጉ ጥቃቶችን እንደማይታገስ አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል።
ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች አጋርነታቸውን የገለጹት አሚና በጦርነቱ ሳቢያ በሴቶች ላይ የደረሰውን ግፍና በደል እንዲሁም አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ለማቃለል ድርጅታቸው መፍትሄ በማፈላለግ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሴቶች ካለባቸው ህመም እንዲፈወሱ በተሃድሶ እና በመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ውስጥ እንዲካተቱም አመራሮቹን አሳስበዋል።
በተጨማሪም ተመድ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የሰላም ጥረትም ይደግፋል ብለዋል።
አሚና በአፋር እና በሶማሌ ክልል ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ጉብኝታቸውን እንደሚቀጥሉም ተነግሯል።
ከአሚና በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ሰኞ ዕለት በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ እንደሚገኙ ተዘግቧል።
ወደ ትግራይ በቅርቡ ሄደው የነበሩት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ከአማራ ክልል በተጨማሪ አፋር ክልልንም ተዘዋውረው እንደሚጎበኙ ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው በትግራይ ክልል ውስጥ 40 በመቶ የሚጠጉ ሰዎች በአስከፊ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልጿል።
ከአስራ አምስት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ ኬንያና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ዴቪድ ሳተርፊልድ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ ሲሆን የአፍሪካ ህሕረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጎ ኦባሳንጆም ከፍተኛ የትግራይ መሪዎችን አነጋግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል (ኤፒ) ዘግቧል።
የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሪ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በህወሓትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።
ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ይህ እየተደረገ ያለው ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት የተወሰነ ውጤት እያሳየ መሆኑንና የመሻሻል ምልክቶች እንዳሉ አመልክተዋል።
ደብረጽዮን (ዶ/ር) እንደተናገሩት በአፍሪካ ሕብረት፣ በተባበሩት መንግሥታት እና በኬንያ አማካኝነት በተዘዋዋሪ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
እየተካሄደ ነው ስለተባለው ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።












