የኬንያው ፕሬዚዳንትና የተመድ ዋና ፀሐፊ የኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጥሪ አቀረቡ

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተፋላሚ ወገኖች ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጥሪ አቀረቡ።

አስራ አምስት ወራት ያስቆጠረው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቆምና ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ የጠየቁት ፕሬዚዳንቱ ረቡዕ ጥር 25/2014 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ ነው።

የፕሬዚዳንቱ የሰላም ጥሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የፊታችን አርብ የሚጀመረውን የዓለም የክረምት ኦሊምፒክን መንፈስ ታሳቢ በማድረግ ተኩስ እንዲቆም ያቀረቡት መልዕክትን ያስተጋባ ነው።

የተመድ ዋና ፀሐፊ ከቀናት በፊት ባስተላለፉት መልዕክት በቀጠለው ጦርነት እና ደም መፋሰሰስ ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ሰቆቃ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ለብዙ ሺህ ዓመታት ባህል የሆነውን የኦሊምፒክ የሰላም መንፈስ ታሳቢ በማድረግ ኢትዮጵያን ጨምሮ በየትኛውም አገራት ተኩስ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በነገው ዕለት አርብ በቻይናዋ ቤጂንግ የሚጀመረውን የክረምት ዓለም አቀፍ ኦሊምፒክን ጠቅሰው በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ተኩስ አቁም በአስቸኳይ እንዲያደርጉ "ጠንከር ያለ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል።

ይህም ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ ለተጎዱ ሕዝቦች ሁሉ ውጤታማ የሆነ የሰብዓዊ አገልግሎት እርዳታ እንዲደርስና እፎይታም ይፈጥራል ብለዋል።

ግጭቶቹን የማስቆም እርምጃም ለአገሪቱ በጣም መሠረታዊ የሆነውን ሁሉን አካታች ብሔራዊ ውይይት መንገድ ለመጥረግም እንደሚረዳ ጠቁመው በዚህም ሕይወትን ማዳን፣ ልዩነቶችን ማቻቻልና እና ለእውነተኛ ሰላም መንገድ መፈለግም እንደሚያስችል አፅንኦት ሰጥተዋል።

ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው "እንደ ኬንያ ፕሬዚዳንት እንዲሁም አንደ ኢትዮጵያ ወንድም ሕዝብ አጋርነቴ "የተኩስ አቁም ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።

በጎረቤት አገር ኢትዮጵያ የቀጠለው ጦርነት "በዚች ታላቅ አገር ባህል እና ስልጣኔ የተሳሰረውን ክብርና ሞገስ ከሕዝቡ ላይ መንጠቁን ቀጥሏል" በማለት ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

የአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም፣ ፀጥታ እና መረጋገት ሊረጋገጥ የሚችለው በአገሪቱ ያሉ ተፋላሚ ወገኖች ፈተናዎችን ዘላቂና እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተቀባይነት ባለው መንገድ ለመወጣት ባላቸው ችሎታ እንደሆነም ኡሁሩ ገልጸዋል።

የተለያዩ ሃሳቦችን በማስተናገድና በማቻመች መንፈስ የሚደረግ ሁሉን አካታች ብሔራዊ ውይት በግጭቱ ለተጎዱ ማኅበረሰቦች ጫናቸውን በማቃለል ረጅም መንገድ ይጓዛል ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብም መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን በኦሊምፒክ መንፈስ ሰላምን ለመቀበል እና ለእውነተኛ እርቅም መንገድ እንዲከፍቱ ጥሪ አድርገዋል።

"የኢትዮጵያ፣ የቀጠናችን እና በእርግጥም የአህጉራችን ብልፅግና ዘላቂ በሆነ ሰላም እና ደኅንነት ላይ መቆም አለበት። አንድ ላይ ሆነን የተሻለ ዓለም መፍጠር እንችላለን" በማለት እምነታቸውን ገልጸዋል።

በያዝነው ዓመት ታኅሣሥ ወር 193 አባላት ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ሁሉም አገራት "በግልም ሆነ በጋራ" ለኦሊምፒክ ግጭቶችንና ጦርነትን እንዲቆም የሚያደርገውን ስምምነት አፅድቋል።

በዚህም ውሳኔ መሰረት የኦሊምፒክ ተኩስ አቁም የ24ኛውን የቤጂንግ የክረምት ኦሊምፒክስና ፓራሊምፒክስ ወቅቶችን ያጠቃልላል። ኦሊምፒክስ ከጥር 27 አስከ የካቲት 13 እንዲሁም ፓራሊምፒክስ ከየካቲት 25 እስከ መጋቢት 4 ይካሄዳሉ።

ጉባኤው የጥንቱን የግሪክ ባህል ኢከቼሪያ መነሻ በማድረግም ሰላማዊ አካባቢን በማበረታት ተሳታፊዎች ለጨዋታዎቹ በአስተማማኝ መልኩ እንዲያልፉና እንዲሳተፉ ለማድረግም የኦሊምፒክ ትሩስ (የኦሊምፒክ ተኩስ የማስቆም) ጥሪ አቅርቧል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው በትግራይ ክልል ውስጥ 40 በመቶ የሚጠጉ ሰዎች በአስከፊ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልጿል።

ከአስራ አምስት ወራት በላይ ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ ኬንያና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ዴቪድ ሳተርፊልድ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ ሲሆን የአፍሪካ ህሕረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጎ ኦባሳንጆም ከፍተኛ የትግራይ መሪዎችን አነጋግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል (ኤፒ) ዘግቧል።

የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሪ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በህወሓትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ይህ እየተደረገ ያለው ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት የተወሰነ ውጤት እያሳየ መሆኑንና የመሻሻል ምልክቶች እንዳሉ አመልክተዋል።

ደብረጽዮን (ዶ/ር) እንደተናገሩት በአፍሪካ ሕብረት፣ በተባበሩት መንግሥታት እና በኬንያ አማካኝነት በተዘዋዋሪ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

እየተካሄደ ነው ስለተባለው ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።