የሩሲያ እና ዩክሬን ፍጥጫ በመባባሱ የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩክሬን እና ሩሲያ ቀውስ በዓለም ዙሪያ የነዳጅ አቅርቦትን ያደናቅፋል በሚል ስጋት የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ነው።
የዓለም አቀፍ የገበያ መለኪያ በሆነው የብሬንት የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ዛሬ ማክሰኞ በበርሜል 97.76 ዶላር ደርሷል። ይህም በሰባት ዓመት ውስጥ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
ሩሲያ በምሥራቅ ዩክሬን በአማፅያን ቁጥጥር ስር ለሚገኙ ሁለት ክልሎች እውቅና ከመስጠት ባለፈ ወታደሮቿ ወደ አካባቢዎቹ እንዲገቡ ፈቅዳለች።
የእስያ የአክሲዮን ገበያዎች ዝቅተኛ ሲሆኑ የአሜሪካ እና የአውሮፓ የአክሲዮን ሽያጮች ለኪሳራ ተጋልጠዋል።
ከሳዑዲ አረቢያ ቀጥላ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ላኪ በሆነችው ሩሲያ ላይ ዩናይትድ ኪንግደም እና በርካታ የምዕራባውያን አገሮች ማዕቀብ ሊጥሉ እንደሚችሉ እየዛቱ ነው። ሩሲያ በተፈጥሮ ጋዝን ምርት ደግሞ ቀዳሚ ናት።
ሩሲያ ወታደሮቿ ራሳቸውን የዶኔስክ እና ሉሃንስክ ሕዝቦች ሪፐብሊኮች ብለው ባወጁት አካባቢዎች "የሠላም ማስከበር" እንደሚሰማሩ አስታውቃለች።
አሜሪካ ደግሞ የሠላም አስከባሪ መባላቸውን "ከንቱ" ስትል ገልጻ፣ ሩሲያ ለጦርነት ሰበብ እየፈጠረች ነው ስትል ተናግራለች።
የማኑላይፍ ኢንቬስትሜንት ማኔጅመንት ባልደረባ የሆኑት ሱ ትሪን የዩክሬን እና የሩሲያ ቀውስ በነዳጅ ዋጋ ላይ "ከፍተኛ እንድምታ" አለው ብለዋል።
ሩሲያ አነስተኛ ድፍድፍ ወይም የተፈጥሮ ጋዝ እንድታቀርብ የሚያስገድድ ማዕቀብ "በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ይኖረዋል" ሲሉ አክለዋል።
በፊደልቲ ኢንተርናሽናል የኢንቨስትመንት ዳይሬክተር የሆኑት ማይኪ ከሪ በበኩላቸው በዩክሬን ቀውስ፣ በአሜሪካ ያለው ቀዝቃዛ ክረምት እና በዓለም ዙሪያ በነዳጅ እና ጋዝ አቅርቦቶች ላይ ባለው የኢንቨስትመንት እጥረት ምክንያት ነዳጅ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ ሊወጣ ይችላል ብለዋል።
"ሩሲያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ ከሚውለው 10 በርሜል ነዳጅ ዘይት አንዱን ታቀርባለች። በመሆኑም በነዳጅ ዋጋ ላይ ዋና ተዋናይ በመሆኗ የነዳጅ ተጠቃሚዎችን ይጎዳል" ይላሉ።
አሜሪካ እና አውሮፓ ሕብረት ሩሲያ ላይ ጥለውት ለዓመታት የዘለቁት ማዕቀቦች በሩሲያ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድረዋል።
በገንዘብ ተቋማት፣ በቴክኖሎጂዎች እና በግለሰቦች ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦች "ሊጠናከሩ" እንደሚችሉ ከሪ ተናግረዋል።












